2009-09-14 15:44:11

የጤና ጥበቃው ጉዳይ በምን የተመራ ነው


በፖላንድ ፖንዛን ከተማ የዓለም አቀፍ የካቶሊክ የመድሃኒት ቀማሚያን ማኅበር “የመድኃኒት ዋስትና፣ ስነ ምግባር እና ኅሊና ለመድሃኒት ቅመማ” በሚል ርእስ ሥር ተሸኝቶ እያካሄደው ባለው ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ የተገኙት RealAudioMP3 እና ንግግር ያሰሙት የጤና ጥበቃ ሃዋርያዊ ኖልዎ ጉዳይ የሚከታትለው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ኣቡነ ዝይግሙንት ዞሞውስኪ፣ የስነ መድኃኒት እና የጤና ጥበቃው ጉዳይ በስነ ምግባር ሳይሆን ሃብት ማካበት በሚል አስተሳሰብ መርህ በሚያደርገው የኢንዳስትሪ ኤኮኖሚ የተመራ ነው ብለዋል።

ብፁዕነታቸው፣ መድኃኒት እና ህክምና የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ መሆኑንም በማብራራት ማንም ፍጡር ይህ አገልግሎት ሊነፈገው ኣይገባም በማለት በተለይ ደግሞ በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ያለው ኮሳሳው የጤና ጥበቃው ጉዳይ እንዲሻሻል እና የሕጻናት ጤና እንክብካቤ እንዲስፋፋ አቢይ ጥረት ይደረግ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።

መድኃኒት የመፈልሰፍ እና አምርቶም ለንግድ የማቅረቡ ጥረት በስነ ምግባር ሳያሆን ትርፍ በማካበት እቅድ ላይ የጸና በመሆኑ ይህ ዓይነቱ አሠራር የመድኃኒት ዋጋ በጣም ውድ እንዲሆን የሚያደርግ ከመሆኑም አልፎ ተጠቃሚው ሕዝብ ድኻው ሳይሆን ሃብታሙ ዓለም ብቻ እንዲሆን እና በጤና ጥበቃው ሂደት አቢይ አድልዎ እንዲፈጸም እያደረገ ነው፣ በአሁኑ ወቅት የክትባት እና የተለያዩ ቀላል መድኃኒት የሚባሉትን አስመስሎ በማምረት ለድዃው ሕዝብ በማሰርጨት ወይንም በዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ የሚፈጸመው በደል ለሌላ በሽታ እያጋለጠው ነው ብለዋል። በናይጀሪያ እና በሃይቲ አበይት ኅብረ ዓለም አቀፍ የመድኃኒት ቅመማ ኢንዱስትሪዎች ያስከተሉት የጤና መታወክ የቅርብ ትውስት ነው ብለዋል። ወደ ደቡባዊው ያፍሪካ ሰሃራ አገሮች ወደ ደቡባዊው ምስራቅ እስያ እና ወደ ላቲን አሜሪካ ከሚላከው መድኃኒት ውስጥ 30% ፍቱን ያልሆነ የሓሰት መድኃኒት መሆኑ እና ይባስ በአንዳንድ ያፍሪካ አገሮች የሚገኘው መድኃኒት 60% ተምሳይ ከመሆኑ አንጻር ፍቱንነቱ ያልተረጋገጠ እንደሆነም ዓለም አቀፍ የጤና ጥበቃ ድርጅት ያካሄደው ጥናት ጠቅሰው፣ የካቶሊክ የመድኃኒት ቀማሚያን ማኅበር ትርፍ በማካበት አስተሳሰብ ሳይሆን በሥነ ምግባር የተመራ አሠራር ይከተል ዘንድ አደራ ብለዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.