2009-08-21 15:58:09

ዝክረ ቅዱስ በርናርዶስ ዘኪያራቫለ


ትናንትና በሥርዓተ ላቲናዊ ሥርዓተ አምልኮ የቤተ ክርስትያን ሊቅና አበምኔት የነበሩና የሲታውያን መነኮሳን ኣባት የሆኑ ቅዱስ በርናርዶስ ዘኪያራቫለ የተዘከረበት ዕለት ነበር።

ቅዱስ በርናርዶስ በ1091 ዓም በዲጆን የሚባል የፈረንሳይ መንደር ተወለዱ፣ ገና ወጣት እንዳሉ የቤተ ክርስትያን ትምህርትንና የዓለም ትምህርት አጠናቀቁ። የአቡነ ቡርክ መነኮሳን አባል ለመሆን ይሰማቸው የነበረን ጥሪ ለመቀበል ብዙ ከታገሉ በኋላ በ1112 ዓም የአቡነ ቡሩክ መነኮሳን አባል ለመሆን ገዳመ ሲቶ ገብተው መነኰሱ፣ የሲታውያን ማኅበር ጸሎት ጥናትና የጉልበት ሥራ በማዘውተር የሚኖር የአስተንትኖ ሕይወት ሆኖ መሪ አሳቡ ‘ጸሎትና ሥራ’ በሚል ሓረግ ይጠቃለላል። ቅዱስ በርናርዶስ ይህንን ወርቃዊ ሕግ በመጠቀም ቅዱሳት መጻሕፍትንና የቅዱሳን ኣባቶች ትምህርትን ጠንቅቀው አጠኑ፣ የገዳሙ አባል ሆነው 3 ዓመት ሲመላቸው በኪያራቫለ አዲስ ገዳም እንዲከፍቱ በአበምኔት ታዘው፣ በ25 ዓመት ዕድሜያቸው የኪያራቫለ ገዳም አበምኔት ሆኑ። እመቤታችን ድንግል ማርያምን የአዲሱ ማኅበር ጠበቃ በማድረግ ገዳሙን ለ38 ዓመታት አስተዳደሩት።

የአቡነ ብሩክን የገዳም ደንብ ጠንቅቀው ካጠኑ በኋላ በ1118 ዓም ‘መጽሓፈ ፍቅር’ የተሠየመ ሕገ ገዳም ጻፉ፣ ይህንን ሕገ ገዳም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ካሊስቶ 2ኛ አጸደቁላቸው።

በ20 ነሐሴ 1153 ዓም ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት ቀን ድረስ የኪያራቫለ ግዳም 700 መነኮሳንን በገዳሙ ከተከፈቱት 165 ገዳማት 68ቱ ቅዱስ በርናርዶስ ራሳቸው የከፈትዋቸው ነበሩ፣ የሲቶ ገዳምና የኪያራቫለ ገዳማት በጠቅላላ 350 ገደማ እንደነበሩ ታሪክ ያወሳል።

ቅዱስ በርናርዶስ ጾም ጸሎትና ተጋድሎ የሚያዘወትር መንኮስና አበምኔት በመኖራቸው፣ በረሃብና በእርዛት የሚሞቱትን ድሆችና መስኪኖች እያመለከተ መንኮሳቱ በሚያሳዪት ቅብጠት በኃይል ይወቅስዋቸው ነበር። የገዛ ራሳቸው ድካምም አይደብቁም ነበር፣ ትዕግሥት ያንሳቸው ስለነበረ ራስን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ትግል በትሕትና ይገልጹ ነበር።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ የዚህ ቅዱስ መንፈሳዊ ሕይወት ዓቢይ ኃይል ፍቅር ነበር ሲሉ ይገልጹታል፣ እንዲሁም የመህከለኛ ዘመን መንኮሳንና ሥራቸውን አስመልክተው ‘የኤውሮጳ ሥልጣኔ የመንኮሳን የሥራና የጸሎት ባህል ቢጐድለው ኑሮ እውን ሊሆን አይችልም ነበር’ ብለዋል። ቅዱስነታቸው የዚህ ቅዱስ ኃይል ፍቅር መሆኑን ሲገልጹ ‘ፍቅር የሆነ እግዚአብሔር የሰው ልጅን በፍቅር ፈጠረው በፍቅርም አዳነው፣ በአባታችን አዳም ኃጢአት እስከ ሞት የቆሰለና ራሱ በሠራው ኃጢአት ክብደት ሥር የነበረው የሰው ልጆች ደኅንነት እውን የሆነው በተሰቀለውና ከሞት ተለይቶ በተነሣው ክርስቶስ በሙላት የተገለጸልን መለኮታዊው ፍቅርን በመቀበል ነው። እግዚአብሔር በፍቅሩ ከእርሱ ጋር አንድ እንድንሆን ለቅድስናና ተምስጦአዊ ውህደት ከፍ በማድረግ የታመመውን ፍላጎታችንና አእምሮአችንን ይፈውሳል’ ሲሉ የምንኵስና ጥሪ ምን ያህል ክቡር መሆኑን አስተምረው ነበር።








All the contents on this site are copyrighted ©.