2018-07-08 12:19:00

የሐምሌ 1/2010 ዓ.ም የዘመነ ክረምት የመጀመሪያው እሁድ ቅዱስ ወንጌል እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ


የሐምሌ 1/2010 ዓ.ም የዘመነ ክረምት የመጀመሪያው እሁድ ቅዱስ ወንጌል እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

የዕለቱ ምንባባት

1ቆሮ 15፡ 33-50, ያዕ 5፡16-20, ሐዋ 27፡11-20,

ሉቃ 8፡1-21

የዘሪው ምሳሌ

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ በየከተማውና በየመንደሩ አለፈ። ዐሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ እንዲሁም ከርኩሳን መናፍስትና ከደዌ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣ የሄሮድስ ቤት ኀላፊ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና፣ ደግሞም ሌሎች ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህም በግል ንብረታቸው የሚያገለግሉት ነበሩ።

ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስቦ ሳለ፣ ደግሞም ሰዎች ከተለያዩ ከተሞች ወደ እርሱ በሚጐርፉበት ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ዐራሽ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር፤ ወደቀ በእግርም ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት። አንዳንዱም ዘር በድንጋያማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ እንደ በቀለም ርጥበት አልነበረውምና ደረቀ። ሌላው ዘር ደግሞ እሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አብሮት አደገና አንቆ አስቀረው።ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ ዕጥፍም አፈራ።

ይህን ብሎ ሲያበቃም ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማአለ።

ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጒም ጠየቁት። 10እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቶአል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣እያዩ ልብ እንዳይሉ፣ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።

 “እንግዲህ የምሳሌው ትርጒም ይህ ነው፤ ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳር የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ፣ ነገር ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው። በድንጋያማ ቦታ ላይ የወደቀውም ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር ስለሌላቸው በፈተና ጊዜ ፈጥነው የሚክዱ ናቸው። በእሾኽ መካከል የወደቀውም ቃሉን የሚሰሙት ናቸው፤ እነዚህም ውለው አድረው በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ ታንቀው በሚገባ አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።

በመቅረዝ ላይ ያለ መብራት

መብራትን አብርቶ ጋን ውስጥ ወይም በዐልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁንም ወደ ቤት የሚገቡ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። 17የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅ ወደ ብርሃን የማይወጣ፣ የተደበቀ ነገር የለምና። 18እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ይጨመርለታልና፤ ከሌለው ሁሉ ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።

የኢየሱስ እናትና ወንድሞች

ከዚህ በኋላ የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ እርሱ ወዳለበት መጡ፤ እነርሱም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ሊቀርቡ አልቻሉም። በዚህ ጊዜ፣እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋልየሚል ወሬ ደረሰው።እርሱም መልሶ፣ “እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት ናቸው” አላቸው።

 

የሐምሌ 1/2010 ዓ.ም የዘመነ ክረምት የመጀመሪያው እሁድ ቅዱስ ወንጌል እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

የዘመነ ክረምት የመጀመሪያው እሁድ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ! ዛሬ በቤተክርስቲያናችን ስርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር ቀመር መሰረት የዛሬ ሰንበት የዘመነ ክረምት የመጀመሪያው ሰንበት በመባል ይታወቃል።የምንጀምረውም ዘማሪው ዳዊት “እርሱ ደመናትን በሰማይ ላይ ይዘረጋል ለምድር ዝናምን ይሰጣል፣ ተራራዎችንም በለምለም ሳር ይሸፍናል”  (146(147) ፡8) እንደዘመረ እኛም በዚህ መንፈስ ሆነን ነው ዘመነ ክረምትን የምንጀምረው፡፡ የዕለቱ ምንባባት የሚያስተላልፉልን ቁም ነገርም ከጊዜው ጋር በተያያዘ የሚከናወኑትን ተግባራት  በመጠቆም ነው ከነዚህም መካከል ዘር መዝራትን ይጠቅሱልናል፡፡

ሐዋ. ቅዱስ ጳውሎስ 1ኛው ቆሮ. 15፡33-50 ላይ ከሞት ስለተነሳ የአካል ሁኔታ ይናገራል ምንአልባት  ከአማንያን አንዱ “የሞቱ ሰዎች የሚነሱት እንዴት ነው? ከሞት ሲነሱ የሚኖራቸው አካልስ ምን ዐይነት ነው”? ብሎ ይጠይቅ ይሆናል ብሎ የጀምርና ራሱ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ይመልሳል አንተ ሞኝ የምትዘራው እህል ካልሞተ ሕይወት አይኖረውም አንተ ስትዘራም ስንዴ ወይም ሌላ እህል ብቻ ትዘራለህ እንጂ በኃላ የሚበቅለውን ተክል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ግን ለዘሩ እንደፈለገ አካልን ይሰጠዋል ለእያንዳንዱም ዘር ልዩ ልዩ አካል ይሰጠዋል በማለት ሞኙን ሰው ያስተምረዋል፡፡

ያዕቆብ በመልዕክቱም ስለ ምድር ፍሬ እንድንጸልይ ሲመክረን “እያንዳንዱ ለሌላው ይጸልይ የጻዲቅ ሰው ጸሎት ብዙ ውጤት የሚያስገኝ ታላቅ ኃይል አለው” እያለ የሚያጽናናን ቃል በመጥቀስ ያስተምረናል እንደዚሁም ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ ነገር ግን ዝናም እንዳይዘንብ በጸለየ ጊዜ ለሦስት አመት ተኩል በምድር ላይ ምንም ዓይነት ዝናም  አልዘነመም፡፡ እንደገና በጸለየም ጊዜ ሰማይ ዝናም ሰጠ ምድርም እንደገና ፍሬ ሰጠች፡፡

የተከበራችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች ጸሎት አማራጭ የሌለው ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን እውነተኛው መንገድ ነው። በጸሎት የማይፈታ ቋጠሮ የለም፣ ዛሬ ብዙ ጸሎት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ። እንቆቅልሽ ሆነውብን አልፈታ ያሉን፣ አልገለጽ ያሉን፣ የተቆላለፉብን መንገድ ሁሉ በጸሎት ብቻ ነው በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉት ምክንያቱም ጸሎት ኃይል አለውና፡፡

ብዙ የሚነፍሱ አቅጣጫቸው በውል የማየታወቅ ነፋሶች አሉ። ልክ በሐዋሪያት ስራ 27፡11-20 ከጳውሎስ ጋር ሲጋዙ የነበሩ መንገደኞች ያጋጠማቸው ዓይነት ነፋስ በአራቱም አቅጣጫ እንደመጣባቸው በዘመናችንም ይከሰታል ስለዚህ በሌላ በምንም ኃይል ልናስቆማቸው አንችልም ማቆሚያ መሳሪያችን ጸሎት ነው፡፡

የዕለቱ ወንጌል የሚተርክልን ያለው ስለ ዘሪውና ስለ ዘሪው ምሳሌ ነው

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ትምህርት በሚያስተምርበት ጊዜ ብዙ ሰዎች ነበሩ፣ እስከ 5ሺህ ይጠጉ ነበር ይላሉ ሊቃውንቶቹ ማቴዎስና ማርቆስ ስለዚሁ ትምህርት ሲጽፉ እንደገለጹት። እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ስለተሰበሰቡ ወደ ባሕር ገብቶ በጀልባ ላይ ተቀምጦ በኮረብታማው የባሕር ዳር ደረቅ ምድር ላይ የተቀመጡትን ሕዝብ ያስተምር ጀመር፡፡

ሕዝብ ወደ ጌታ ስለምን ተሰበሰበ፡› ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ህሙማንን ስለፈወሰ እውራንን ስላበራ፣ ለምጻሞችን ስላነጻ፣ ሽባዎችን ስላዳነ፣ በአጋንንት የተያዙትን ስለፈወሰና፣ ዲዳዎች እንዲናገሩ ስላደረገ . . . ወዘተ ተዐምራቱን ለማየትና የፈውሱም ተካፋዮች ለመሆን ነበር የተሰበሰቡት፡፡ የተሰበሰቡትም የተለያዩ ሰዎች ነበሩ

1. ብዙዎቹ ታምራቱን አይተውና ስለ ድኅነት ያስተምር የነበረውን ትምህርት ሰምተው የነበረባቸውን የመንፈስ ጭንቀት ያስወግድልናል እንዲሁም ያድነናል ብለው ያምኑ ነበር

2. ሌሎች ደግሞ ህመምተኞቻቸውን ብቻ ለማስፈውስ የመጡ ነበሩ

3. ጥቂቶች ደግሞ ጌታ የሚሰራውን አይተው ለሌሎች ለማውራት ለወሬ ብቻ የተሰበሰቡ ነበሩ

4. በጌታችን ላይ ወንጀል ለመፈለግና እርሱን ለማጥፋት የመጡ ነበሩ ለምሳሌ የፈሪሳውያን የጸሐፍት የሰዱቃውያንና የካህናት ወገኖች የሆኑ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ጌታችን ይህንን የዘሪውን ምሳሌ ሲያስተምር በታላቅ የኃዘን ስሜት ነበር ያስተማረው፡፡

“እነሆ ዘሪ ገበሬ ሊዘራ ወጣ ሲዘራም እንዳንዱ ዘር በመንገድ ላይ ወደቀ ተረገጠም ወፎችም መጥተው ዘሩን ለቀሙት” በማለት ይጀምራል። የፍልስጤማዊያን የእርሻ ማሳዎች ቀጫጭን ነበሩ በመካከላቸው የእግር መተላለፊያ መንገድ አለ ይህም የብዙ ተላላፊዎች እግር ስለሚረጋግጠው የጠነከረ እንጂ ለስላሳ ምድር አልነበረም፡፡ በዚህ ላይ የሚወድቀውን ዘር ወፎች በቀላሉ ይለቅሙታል፡፡ የሰውም ልብ በብዙ ነገሮች የተጠቀጠቀና የጠነከረ በመሆኑ የእግዚአብሔር ቃል ቢነገረውም አይገባውም፡ መሬቱ ደረቅ በመሆኑ ዘሩ ስር ሰዶ ሊበቅል ፈጽሞ እንደማይችል የሰውም ልብ በልዩ ልዩ ኃጢአትና ከንቱ ምኞት በገንዘብ ፍቅር በዝሙትና በስልጣን ፍቅር ምክንያት የተነገረው የእግዙአብሔር ቃል ሊገባው አይችልም፡፡

ሌላው ዘር በጭንጫማ ምድር ላይ ወደቀ ይህ መሬት ጥቂት አፈር አለው ውስጡ ግን ድንጋይ አለት ነው፡፡ ተክልና ዘር ደግሞ ምግብና ውሃ የሚያገኘው በስሩ አማካኝነት ከምድር ስለሀነ ጭንጫው ስሩን ወደ ምድር ስለማያሳልፈው በምግብና በውሃ እጦት የተዘራው ዘር ይደርቃል፡፡ ይህ ዘር ወዲያው በቅሎ ጸሐይ በወጣ ጊዜ ወዲያውኑ ይደርቃል ወይም ይጠወልጋል፡፡ ይህም የሚያመለክተው የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰሙ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበሉትን አንዳንድ ሰዎችን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ችግር ወይም ስደት በደረሰባቸው ጊዜ ወዲያው ተሰናክለው ይወድቃሉ፡፡

ሌላው ዘር ደግሞ በእሾህ ቁጥቋጦ መካከል ወደቀ፡፡ ነገር ግን ማደግ ሲጀመር እሾህ አብሮ አደገና ፍሬ እንዳያፈራ አንቆ አስቀረው፡፡ ይህም የሚያመለክተው በዚህ ዓለም አሳብና ሀብት በምድራዊ ምቾትም ውስጥ ያሉ ሰዎችን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማሉ ነገር ግን በምድራዊ ምቾት በዚህ ዓለም አሳብና ሀብት ተጠምደው ምንም ፍሬ ሳያፈሩ ይቀራሉ፡፡

አብዛኞቹ የዘመናችን ሰዎች ይህን የሶስተኛውን ክፍል ሰው ይመስላሉ፣ ስንቶች ናቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ለመጸለይ ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ ጊዜ የለንም የሚሉት፡፡

እኛም ራሳችንን መጠየቅ አለብን፣ የእውነት መጽሐፍ ቅዱስን እናነባለን እንጸልያለን እንዳንዶቻችን ስንጠየቅ ምን ጊዜ አለኝ እንካንስ ይህን  ላደርግ ይቅርና ቁርስ ለመብላት ጊዜ የለኝም እንላለን፡፡ ክርስቲያናዊ ተግባር እንዳንፈጽም ብዙ አስረው የያዙን ነገሮች አሉ ከእነዚህ ነገሮች ለመላቀቅ እንግዲህ ጸሎት ወሳኝ ነገር ነው፡፡

አራተኛው ዘር በመልካም መሬት ላይ በለስላሳ መሬት ላይ የተዘራው ነው፡፡ይህ ዘር በጥሩ ሁኔታ በቅሎ መቶ ዕጥፍ ፍሬ እንዳፈራ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ይህ አራተኛው ምሳሌ የሚያስረዳን የእግዚአብሔር ቃል በሚነገርበት ጊዜ በጥንቃቄ የሚሰሙትንና ቃሉን በደስታ የሚቀበሉትን የሰሙትንም በተግባር ላይ የሚያውሉትን አስተዋይ ክርስቲያኖችን ነው፡፡ ማንኛውም ክርስቲያን በሰማውና በተረዳው የእገዚአብሔር ቃል በሰማውና በተረዳው የእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ ጸንቶ መኖር እጅግ ያስፈልገዋል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን የዘሪን ምሳሌ ሲያሰተምር ዓላማው የነበረው በዚያ የተሰበሰቡትን ሰዎች መንፈሳዊና የስነ ምግባር አቀማቸውን ወይም ጠባያቸውን ለመንገር ብቻ አልነበረም ዋና ዓላማ ሰዎች ከመጥፎ ጠባያቸውና ተግባራቸው እንዲታረሙ ለማድረግ ነበር፡፡ የደነደነው ልባቸው እንዲለሰልስ እሾህ ከልባቸው እንዲነቀልና እንዲታረም ዐለቱ ወይም ድንጋዩ ከልባቸው ተፈንቅሎ እንዲወገድና ልባቸው እንደ መልካም መሬት ለስልሶ መቶ ዕጥፍ እንዲያፈራ ነበር፡፡ ሁለተኛው ይህ ትምህርት በጌታ የተነገረው በዚያች በገሊላ ባሕር አጠገብ ለተሰበሰቡት ሰዎች ብቻ አይደለም፡፡ የጌታ ቃል ዘለዓለማዊ ነው የሚያስተምረውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚኖሩ ሕዝቦች ነው፡፡ የእኛም ልብ ዛሬ እንደ ጭንጫ ምድር ሆኖ እንደሆነ በኃጢአት እሾህ ተተብትቦ እንደሆነ በንስሓ ልባችንን ማንጻት አለብን፡፡

እንግዲህ አራት የምድር ዓይነቶች አይተናል ደረቅ ምድር ጭንጫማ ምድር እሾሃማ ምድር እና መልካምና የለሰለሰ ምድር ናቸው፡፡ እያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን በየትኛው ደረጃ ላይ እንዳለ ራሱን መመርመር ይገባዋል፡፡ እንግዲህ ሁላችንም መልካሙና ለስላሳው መሬት ሆነን መልካም ፍሬ ለማፍራት ቸሩ መድኃኔ ዓለም ይርዳን ዘመነ ክረምቱን ይባርክልን፡፡ አሜን!!

 








All the contents on this site are copyrighted ©.