2018-06-27 15:21:00

የኤርትራ መንግሥት የሰላም ልዑካን ቡድን በትላንትናው ዕለት ማለትም በሰኔ 19/2010 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባቱ ተገለጸ።


የኢትዮጲያ ፌዴራላዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚንስቴር የሆኑት ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ ባቀረቡት የሰላም ጥሪ መሰረት የኤርትራ መንግሥት የሰላም ልዑካን ቡድን በትላንትናው ዕለት ማለትም በሰኔ 19/2010 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባቱ ተገለጸ።

ይህ የኤርታራ መንግሥት የሰላም ልዑክ በትላንትናው ዕለት አዲስ አበባ በገባባት ወቅት የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚንስቴር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ  እና የተለያዩ የሀግሪቷ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የሐይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ተወካዮች በተገኙበት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት የምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኀብረት ሊቀመንበር በስፍራው ተገኝተው የአቀባበል ስነ-ስረዓቱን መታደማቸውን ለመረዳት ተችሉዋል። የኤርትራ መንግሥት የሰላም ልዑክ ወደ ኢትዮጲያ መግባቱን በተመለከተ ከቫቲካን ሬዲዮ ተባባሪ ጋዜጠኛ ከማክዳ ዩሐንስ ጋር ካርዲናል ብርሃነየሱስ በሰኔ 20/2010 ዓ.ም ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደ ገለጹት ይህ በኢትዮፒያ ፌዴራላዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚንስቴር የሆኑት ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት እየተካሄደ የሚገኘው የሰላም ማስፈን ጥረት ቀደም ሲል ቤተክርስቲያኗ ከምዕመናኖቹዋ ጋር በሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ሰላም ይወርድ ዘንድ መላው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመን በጸሎት ይተጉ እንደ ነበረ ያስታወሱት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሰላምን የናፈቁ የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ተለያይተው እና ተነፋፍቀው የነበሩ ሕዝቦች እንዲገናኝ እድል የሚከፍት በመሆኑ የተነሳ ከፍተኛ ደስታ እንደተስማቸው ገልጸው የሰላም ሁሉ ምንጭ የሆነው እግዚኣብሔር በመሆኑ የተነሳ ሰላም በመላው ዓለም ይሰፍን ዘንድ ጸሎት ማድረጋችንን ልንቀጥል ይገባል ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.