2018-06-26 09:11:00

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሐዘን መግለጫ


ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም.

 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሐዘን መግለጫ

ዛሬ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም ኢትዮጵያውያን በአንድነት፣ በፍቅር፣ በይቅርታ ስሜት ተሞልተው በቅርብ ጊዜ ወደስልጣን የመጡትን በአገልጋይነት የመሪነት መንፈስ ተመርተው ኢትዮጵያን ወደ ጥልቅ ዲሞክራሲ እና ህዝቡ በሚፈልገው የኢትዮጵያ አንድነት አቅጣጫ እየወሰዱ ያሉትን ክቡር ዶ/ር ዓቢይ አህመድና መንግስታቸውን ለማመስገንና ለያዙት ኢትዮጵያዊ ዓላማ ከጎናቸው መሆናቸውን ለመግለፅ ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባ ከተማ በነቂስ ለሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸው ያታወቃል፡፡ ይህንን ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ሃይማኖት እና የፖለቲካ አመለካከት ሳይለያቸው በፍፅም ኢትዮጵያዊ አንድነት መንፈስ ያሰባሰበ ሠላማዊ የፍቅር፣ የመደመር መገለጫ የሆነ ሠልፍ መሀል ይህንን ፍቅር፣ አንድነት እና ይቅርታን ለመፈተን በተደረገ የቦንብ አደጋ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በተፈጠረው ሁኔታ የተሰማን ሃዘን ጥልቅ ነው፡፡ ይህ ክስተት በጣም አሳዛኝና አስደንጋጭ ቢሆንም የህዝቡን የአንድነት፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የይቅርባይነት ጉዞ እንደማይገታው እናምናለን፡፡ ለዚህም መላው ኢትዮጵያውያን ጥላቻን፣ ዘረኝነትን አስወግደው የጀመሩትን የተስፋ፣ የሰላም፣ የአንድነት ጉዞ በጋራ ሆነው በተፈጠረው ነገር ሳይረበሹ በፍፁም ፅናት እንዲያስቀጥሉት እየተማፀንን ለሞቱ ወገኖቻችን የዘላለም እረፍትን እንመኛለን፡፡ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ከአምላካችን እንዲያገኙ እየተማፀንን በሆስፒታል ለሚገኙ ለተጎዱ ወገኖቻችን በፍጥነት ፈውስ እንዲያገኙ በፀሎት ከእነርሱ ጋር መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

 

†ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን

የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት

የአመሰያ ሊቀመንበር

 








All the contents on this site are copyrighted ©.