2018-06-16 16:11:00

የሰኔ 10/2010 ዓ.ም የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ


የሰኔ 10/2010 ዓ.ም እለተ ሰንበት ቃል እግዚኣብሔር እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

የዕለቱ ምንባባት

  1. 1ቆሮ 14፡1-25
  2.  1ኛ ዮሓ 4፡1-8
  3. ሓዋ ሥ 14፡44-11፡10
  4.  ዮሓ 15፡17-27

የዩሐንስ ወንጌል 15፡17-27

እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ፣ ትእዛዜ ይህቺ ናት።

ዓለም ደቀ መዛሙርትን መጥላቱ

 “ዓለም ቢጠላችሁ፣ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ።ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ፣ ዓለም የራሱ እንደሆኑት አድርጎ በወደዳችሁ ነበር፤ ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለ ዚሁ ነው። ‘አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን አሳደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ከሆነም ቃላችሁን ይጠብቃሉ። የላከኝን ስለማያውቁ፣ በስሜ ምክንያት ይህን ያደርጉባችኋል። መጥቼ ባልነግራቸው ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው የሚሰጡት ምክንያት የላቸውም። እኔን የሚጠላ፣ አባቴንም ይጠላል። ሌላ ሰው ያላደረገውን በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ፣ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እነዚህን ታምራት አይተዋል፤ ሆኖም እኔንም አባቴንም ጠልተዋል።ይህም፣ ‘ያለ ምክንያት ጠሉኝ’ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው። “እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ፣ ከአብ የሚወጣው አጽናኙ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል። እናንተም ደግሞ፣ ከመጀመሪያው ከእኔ ጋር ስለ ነበራችሁ፣ ትመሰክራላችሁ።

 

 

የሰኔ 10/2010 ዓ.ም እለተ ሰንበት ቃል እግዚኣብሔር እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ከጰራቅሊጦስ በኋላ ያለውን ሦስተኛ ሰንበት እናከብራለን። በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ የዕለቱ ንባባት ኣማካኝነት መልዕክቱን ያስተላልፍልናል። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ መልዕክቱንም እንዲህ በማለት ይጀምራል ፍቅርን ተከታተሉ ይለናል። ሁላችንም እንደምንረዳው ፍቅር የሁሉ ነገር መጀመሪያም መጨረሻም ነው። እግዚኣብሔር ኣንድያ ልጁን ወደ ምድር የላከው ለእኛ ለልጆቹ ካለው ፍቅር የተነሳ ነው፣ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስም ሕይወቱን ኣሳልፎ ለመስቀል የሰጠው ለኣባቱና ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሳ ነው። ፍቅር ከሌለ ምንም የለም፣ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው የቆሮንጦስ መልዕክት ምዕራፍ 13 ከቁጥር 1 ጀምሮ ስለ ፍቅር ብዙ ይናገራል እንዲህም ይላል፣ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር  ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮህ ናስና እንደሚንሸዋሸው ጸናጽል ሆኛለው ይላል። ትንቢትም ቢኖረኝ ምስጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁል ባውቅ ተራሮችንም አስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ ይለናል። እንግዲህ ፍቅርን መከታተል ማለት የፍቅር ውጤት የሆኑትን ነገሮች ሁሉ መያዝና በእነርሱም ውስጥ መኖር ማለት ነው። በፍቅር የሚኖር ሰው ይታገሳል በፍቅር የሚኖር ሰው ቸርነትን ያደርጋል በፍቅር የሚኖር ሰው ኣይቀናም በፍቅር የሚኖር ሰው በራሱ ኃይል ብቻ ኣይመካም ኣይታበይም በፍቅር የሚኖር ሰው የማይገባውን ኣያደርግም ኣይበሳጭም ተንኮል ኣያስብም። እንግዲህ ዛሬ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ  በቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ኣድርጎ ይህንን ያሳስበናል። በመቀጠልም ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በልሳንና በትንቢት ስለመናገር ይናገራል። ሁለቱም ስጦታዎች ማለትም  በልሳን ወይም በትንቢት መናገር የሚመነጩት ከራሱ ከእግዚኣብሔር ነው፣ ሆኖም ኣንድ ሰው በልሳን ሲናገር ያንን ልሳን የሚተረጉም ሰው ከሌለ ያ የልሳን ቋንቋ የሚያበረታው የሚያፅናናው የሚያንፀው ያ በልሳን የተናገረውን ሰው ብቻ ነው፣ ስለዚህ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ለኣብዛኛው ሰው መበረታታት መፅናናት መታነፅ ሲባል ልሳን ከመናገር በላይ  ትንቢት የመናገር ስጦታን ፈልጉ እሹ ይለናል። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በዚሁ በምዕራፍ 14፡5 ላይ እንዲህ ይለናል፣ ሁላችሁ በልሳን እንድትናገሩ እወድ ነበር ትንቢትን ብትናገሩ ግን ልሳን ከመናገር የበለጠ እወድ ነበር ምክንያቱም ማኅበሩ ይታነፅ ዘንድ ነው፣ ንግግሩም ባይተረጎም እንኳን በልሳን ከሚናገር ሰው ይልቅ ትንቢት የሚናገረው ይበልጣል ይለናል። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ኣንድ የሚጨምረው ነገር ኣለ ይኸውም ኣንድ ሰው ልሳን ወይንም ትንቢት ከመናገሩ በፊት ሕይወቱ በፍጹም የተስተካከለና በእውነተኛ ክርስቲያናዊ መንፈስ የተገነባ ሊሆን ይገባዋል፣ ምክንያቱም የልሳንም ሆነ የትንቢት ሥጦታዎች ባለቤት ራሱ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ነው፣ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ይህንን ጸጋ ከመቀበሉ በፊት ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ቀጥተኛና የጠበቀ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል፣ ሕይወቱ በክርስቶስ መንፈስ ተታነፀ ሊሆን ይገባል ።

በዛሬው በሁለተኛ መልዕክት ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ በመጀመሪያ መልዕክቱ በምዕራፍ ኣራት ከቁጥር ኣንድ ጀምሮ ሓሰተኛ ነቢያቶች እንዳሉና ከበፊትም ጀምሮ እንደነበሩ መልካምና ከእግዚኣብሔር የሆነዉን እንደሚናገሩ ኣስመስለው የሓሰት ትምህርትን በመዝራት የሰይጣንን መንገድ እንደሚያስፋፉ ይነግረናል።

ኣንድ ሰው ትንቢት ወይንም ልሳን በሚናገርበት ጊዜ ያ የሚናገረው ቃል ቤተክርስቲያንን የሚያንጽ የሚያበረታ የሚያስተምር ከሆነና ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የኣብ ኣንድ ልጅ መሆኑን የሚመሰክር ሰውም ሆኖ ወደ እኛ መምጣቱንና ከኃጢኣታችንም ደሙን በማድፍሰስ እንዳዳነን የሚመሰክር ከሆነ በእርግጥም ያ መንፈስ ከእግዚኣብሔር መሆኑን ልንረዳ ይገባናል። ምናልባት ከዚህ በተቃራኒው የሚሄድ ከሆነ ደግሞ ትንቢቱም ሆነ በልሳን መናገሩ የሓሰት መሆኑን ተረድተን ልናወግዘው ይገባናል፣ ከዚህ ከሃሰት ትምህርት ልንሸሽ ይገባል። ይህንን በማስመልከት ቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ በሁለተኛ መልዕክቱ እንዲህ ይለናል እንግዲህ እናንተ ወዳጆቼ ሆይ ይህን ኣስቀድማችሁ ስለምታውቁ በኣመፀኞች ስህተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ፅናት እንዳትርዱ ተጠንቀቁ፣ ነገር ገን በጌታችንና በመድኃኒታችን በእየሱስ ክርስቶስ ፀጋና እውቀት እደጉ ይለናል፣ ይህንንም ማለቱ በሌላ ኣነጋገር ከሓሰተኞች ነቢያት ራሳችሁን ጠብቁ በሓሰተኛ ትምህርታቸውም ተስባችሁ በእምነታችሁ ኣትሰናከሉ ማለቱ ነው። በመቀጠልም ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ እግዚኣብሔር  የፍቅር ኣባት የፍቅር መገለጫና እርሱ ራሱ ፍቅር ነው ስለዚህ እኛም በእግዚኣብሔር ኣምሳል ተፈጥረናልና ከኣግዚኣብሔር ምንጋራው ነገር ኣለና እርስ በርሳችን እንዋደድ እንፋቀር በማለት ሓሳቡን ያካፍለናል። እውነት ነው እግዚኣብሔርን የሚያዉቅ ሰው በፍቅር ይኖራል በፍቅር ይመላለሳል እርስ በርሱም ይከባበራል ይተሳሰባል ፍቅር በሞላበት መልኩ ደግሞ ይተራረማልም። ይህ ነው የእግዚኣብሔርን ፍቅር በተግባር ላይ ማዋል፣ ኣለበለዚያ እንደው ለኣፋችን ብቻ እግዚኣብሔርን እንወዳለን ብለን ተግባራችን ግን ከዛ የተለየ ከሆነ፣ ገና በእርግጠም ይህ የእግዚኣብሔር ፍቅር በዉስጣችን ኣልገባም ማለት ነው። ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ በመጀመሪያ መልዕክቱ 3፡18 ላይ እንዲህ ይለናል ወዳጆቼ ሆይ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በኣንደበታችን ብቻ ኣንዋደድ ይለናል። ምክንያቱም በውስጣችን ኣለን የምንለው ፍቅር አንደው ለታይታና ለይስሙላ ብቻ ከሆነ፣ የያዝነው መስመር የተስተካከለ ኣይደለም፣ በዚህም እውነተኛ ደስታም ሆነ የመንፈስ እርካታ ልናገኘ ኣንችልም፣ ስለዚህ በፍጥነት ከዚህ ኣመለካከታችን ልንታረምና ወደ ትክክለኛ መስመር ልንመለስ ይገባናል። እግዚኣብሔርን ማወቅ ይህ ነው በእግዚኣብሔር ፍቅር መመላለስ ማለት ይህ ነው። በዛሬው በተነበበው በዮሓንስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ላይም ቀደም ሲል በተነበቡት በቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ እንዲሁም በቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ መልዕክት ላይ ስለ ፍቅር ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጠናል። እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ይመክረናል። እርስ በርስ መዋደድ ማለት በመካከላችን ምንም ዓይነት ክፍተት ኣይፈጠር ማለት ኣይደለም፣ ቢሆን መልካም ነበር ነገር ግን ልክ እንደመልካችን ኣስተሳሰባችንም የተለያየ ነውና፣ የተለያየ ሓሳብ የተለያየ ኣመለካከት ሊኖረን ይችላል፣ ነገር ግን በተረጋጋ መንፈስ በመነጋገር ችግሮችን ማስወገድ፣ ልዩነቶችን ማጥበብ፣ ኣንድነታችንን ማሳደግ ይህ ነው እርስ በእርስ መዋደድ ማለት፣ ይህ ነው በእግዚኣብሔር ፍቅር መመላለስ ማለት። ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በእግዚኣብሔር ፍቅር መኖር ቀላል ነገር እንዳልሆነ ይነግረናል፣ በውስጡ ብዙ መሰናክሎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን እንዚህን ሁሉ በጽናት ማለፍ ያስፈልጋል ይለናል። ሰው በእግዚኣብሔር ፍቅር ለመመላለስ ሲጣጣር ብዙ መከራና ግፍ ሊገጥመው ይችላል፣ ነገር ግን ይህም ቢሆን በተርጋጋ መንፈስ ማሳለፍ እንደሚገባ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያሰምርበታል፣ እንዲህም ይለናል እኔን እንዳሳደዱኝ እንዲሁም እናንተን ያሳድዷችኋል ይለናል። ስለ ክርስቶስ ብሎ መሰደድ ሁላችንን የሱ ስቃይ የእሱ መከራ ተካፋዮች ያደርገናል፣ በዚህም ምክንያት የመከራው ተካፋዮች ሆነናልና በመጨረሻም የክብሩና የደስታዉም ተካፋዮች እንሆናለን፣ በእግዚኣብሔርም ቤት በደስታና በፍቅር እንኖራለን። እመቤታችን ድንግል ማርያም ዘወትር የጌታችን የመድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስን ቃል ለመፈጸም ትተጋ እንደነበር ዛሬ ደግሞ እኛ ልክ እንደሷ የልጇን ቃል ለመጠበቅና በቃሉም መሠረት ለመኖር የምንችልበትን ጸጋና በረከት ከኣንድያ ልጇ ታማልደን የሰማነውን ቃል በልባችን እንድንይዝ በተግባር እንድናውለዉም የምያስችለንን ብርታት ታሰጠን።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.