2018-05-31 16:04:00

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ““የመቁጽሪያን ጸሎት አዘውትራችሁ በመጸለይ ለማሪያም ያላችሁን መንፍሳዊ ቅርበት አሳድጉ”


ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ “የመቁጽሪያን ጸሎት አዘውትራችሁ በመጸለይ ለማሪያም ያላችሁን መንፍሳዊ ቅርበት አሳድጉ”

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የላቲን ስረዓት አምልኮ በሚከተሉት ምዕመናን ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ኤልሳቤጥን የጎበኘችበት እለት በዛሬው እለት በግንቦት 23/2010 ዓ.ም ተዘክሮ ማለፉ ይታወሳል።

የእዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 1፡39-56 ላይ እንደ ተጠቀሰው ማርያም “በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሎአልና። ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”በማለት ኤልሳቤጥ ማሪያምን በታላቅ ደስታ በቤቷ የተቀበልችበት በዓል ነው።

እነዚህ ሁለት ሴቶች ማለትም ማሪያም እና ኤልሳቤጥ በዝምድና የተሳሰሩ ቢሆኑም ነገር ግን በእድሜ፣ በባሕሪይ፣ በአከባቢያዊ ሁኔታ የተለያየ ዓይነት ሕይወት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ሁለት ሴቶች ማሪያም እና ኤልሳቤጥ የየራሳቸው የሆነ የግል ምስጢር ደብቀው የያዙ ሴቶች ነበሩ። የማሪያምን ጉዳይ በምንመለከትበት ወቅት ማሪያም የዩሴፍ እጮኛ የነበረች ሴት እንደ ነበረች የሚታወቅ ሲሆን ነገር ግን መልኣኩ ገብርኤል ከእግዚኣብሔር ተልእኮ የምስራቹን ቃል ካበሰራት በኃላ በሰው ሳይሆን “በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አርግዛ” በመገኘቷ ይህ ሁኔታ ደግሞ በወቅቱ በነበረው የማኅበርሰብ ክፍል አንድ ከትዳር ውጭ ያረገዘች ሴት በድንጋይ ተወግራ ትሙት የሚል ሕግ በመኖሩ የተነስ ተጨንቃ ነበር፣ እግዚኣብሔር በመንፈስ ቅድስ አማካይነት በእርሷ ማደሩን በወቅቱ እርሷ ይህንን ጉዳይ ለሌሎች ማስረዳት የከበዳት ጉዳይ ነበር፣ በእዚህም ምክንያት ሁሉንም ነገር በልቧ እያሰላሰልች ይዛው ቆይታ ነበር።

ኤልሳቤጥም በበኩሉዋ “አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣ ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር። የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቶአል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ዘካርያስም መልአኩን፣ “ይህን በምን አውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች” አለው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ በማለት ምስቱ ኤልሳቤጥ በእስተ እርጅና ወንድ ልጅ እንደ ምትወልድ ባበሰረው መሰረቱ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ታረግዛለች” (ሉቃስ 1፡8-)። ነገር ግን ኤልሳቤጥ በእስተርጅና እድሜ በገፋበት ወቅት ማርገዟ ከፍተኛ የሆነ ምስጢር ሆኖባት ነበር።

ስለእዚህ እነዚህ ሁለት ሴቶች የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር በውስጣቸው ደብቀው የያዙት አንድ ምስጢር መኖሩ፣ ሁለቱም አንድ ወንድ ልጅ እንደ ሚወልዱ እየተጠባበቁ መሆናቸው እና ሁለቱንም ያበሰረው ደግሞ መልኣኩ ገብርኤል መሆኑ ያመሳስላቸዋል።

በእዚህ አጋጣሚ ይህንን ማሪያም ኤልሳቤጥን ለመጎብኘት የሄደችበት ቀን በምንዘክርበት በዛሬው ቀን  “ልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው” (ሉቃስ 1:41-43) በማለት ገና በማሕጸኑዋ ውስጥ ያለውን ሕጻኑን ኢየሱስን እንዳመስገነች ሁሉ፣ እኛም ማሪያም ልባችንን፣ ቤተሰባችንን፣ ሀገራችንን እና እንዲሁም ዓለማችንን እንድትጎበኝ እና በደስታ እና በሰላም፣ በመንፈስ የተሞላን ሆነን እንኖር ዘንድ እንድተረዳን በሕይወታችን ውስጥ ልንጋብዛት ያስፈልጋል ለማለት እንወዳለን።

 

ቀደም ሲል እንደ ገለጽነው የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የላቲን ስረዓት አምልኮ በሚከተሉት ምዕመናን ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ኤልሳቤጥን የጎበኘችበት እለት በዛሬው እለት በግንቦት 23/2010 ዓ.ም ተዘክሮ ማለፉ ይታወሳል። በእዚህም ምክንያት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር መሰረት ዛሬ (ግንቦት 23/2010 ዓ.ም) የተጠናቀቀውን የማሪያም ወር በመባል የሚታወቀውን የግንቦት ወር ውስጥ ያደርጉትን አንኳር አንኳር ተግባራት እንደ ሚከተለው አሰናድተናል። ተከታተሉን።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በሚያዝያ 21/2010 ዓ.ም. በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናንና የሀገር ጎብኝዎች በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ መስረቱን አድርጎ የነበረ አስተንትኖ ካደረጉ በኃላ በወቱ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በግንቦት 1/2018 ዓ.ም. (በኢትዮጲያ የቀን አቆጣጠር በሚያዝያ 23/2010 ዓ.ም ማለት ነው) የሚጀመረው የግንቦት ወር “የማሪያም ወር” በመባል እንደ ሚጠራ መገልጻቸውን ቀደም ሲል ባስተላለፍነው ዝግጅት መዘገባችን የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ በግንቦት ወር ውስጥ በተለያዩ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለየት ባለ ሁኔታ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ከሚቀርቡት የመማጸኛ ጸሎቶች መካከል በቀዳሚነት የሚገኘውን የመቁጠሪያ ጸሎት በታላቅ መንፈሳዊነት ስሜት ይጸለያል።

ይህ የግንቦት ወር በወር ደረጃ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ “የማሪያም ወር” በመባል የሚታወቅ ሲሆን በእዚህም የግንቦት ወር ውስጥ የክርስቶስ፣ የቤተክርስቲያን፣ የምዕመናን እናት ለሆነችው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ለየት ባለ መልኩ ጸሎት የሚደርግበት፣ አማልጅነቷን የምንማጸንበት፣ በተለይም ደግሞ በውስጣችን፣ በቤተሰባችን፣ በማኅበረሳባችን፣ በሀግራችን እና በአጠቃላይ በዓለም ውስጥ የጥል እና የክርክር ግድግዳ ተደርምሶ በአንጻሩ የሰላም እና የብልጽግና መንፈስ ይወርድ ዘንድ በእርሷ አማካይነት ወደ ልጇ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመማጸኛ ጸሎት እንድታቀርብልን እርሷን በተለየ ሁኔታ በመቁጠሪያ ጸሎት አማልጅነቷን የምንማጸንበት ወር ነው የግንቦት ወር።

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ላለፉት 30 ቀናት ያህል የማሪያም ወር በመባል በሚታወቀው የግንቦት ወር ውስጥ ለሰላም፣ ለእርቅ፣ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት እንችል ዘንድ ሲደረግ የነበረው ጸሎት በዛሬው እለት ማለትም በግንቦት 23/2010 ዓ.ም በይፋ ተጠናቁዋል። ምንም እንኳን ጸሎት አንድ ክርስቲያን ከውልደቱ እስከ ሕልፈቱ ድረስ በእየለቱ ሊያደርገው የሚገባው መንፈሳዊ ተግባር መሆኑ የሚታወቅ እና ጸሎት ማብቂያ የሌለው መንፈሳዊ ምግባችን መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ቅሉ፣ ነገር ግን በእዚህ የግንቦት ወር የማሪያም ወር ተብሎ በመጠራቱ የተነሳ ለየት ባለ መልኩ የመቁጠሪያ ጸሎት የሚደርግበት ወር በመሆኑ የግንቦት ወርን ለየት ያደርገዋል።

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ዛሬ የተጠናቀቀውን የማሪያም ወር በመባል በሚታወቀው የግንቦት ወር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸኮ በተገኙበት በቫቲካን ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኘው የአቢሲኒያው የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አንስቶ እስከ ጳጳሳዊው የኢትዮጲያ ኮሌጅ አጠገብ በሚገኘው በሉርድ ማሪያም ስም በተሰየመው እና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ሐውልት በሚገኝበት ዋሻ ድረስ ዑደት በማድረግ እና የመቁጠሪያ ጸሎት በመጸለይ መጠናቀቁን ከደረሰን መረጃ ለመረዳት ተችሉዋል።

በግንቦት 1/2010 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ባድረጉት ስብከት እንደ ገለጹት “የመቁጸሪያን ጸሎት አዘውትራችሁ በመጸለይ ለማሪያም ያላችሁን መንፍሳዊ ቅርበት አሳድጉ፣ እርሷ የእግዚኣብሔር እናት በመሆኑዋ የተነሳ የእግዚኣብሔር ልጅ ምስጢር በሕይወቷ ይዛ የምትገኝ በመሆኑዋ፣ የእዚህ የክርስቶስ ምስጢር ተካፋይ እንሆን ዘንድ እና የክርስቶስን ፍቅር ከሁሉም ጋር መጋራት እንችል ዘንድ እርሷ በአማላጅነቷ እንድትረዳን ልንማጸናት ይገባል” ማለታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በተለይም ደግሞ ላለፉት 6 እና 7 አመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ ለነበረችው ለሶርያ እግዚኣብሔር ሰላሙን ያወርድ ዘንድ በእመቤታችን በቅድስት ማሪያም በኩል ለእግዚኣብሔር የመማጸኛ ጸሎት ማቅረብ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው ጥሪ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል። 

ከእዚህ ቀደም የነበሩት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማሪያም ከፍተኛ አክብሮ እና ፍቅር እንደ ነበራቸው ሁሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ከእርሳቸው በፊት እንደ ነበሩት ብጹዕን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማሪያም ከፍተኛ የሆነ አክብሮ እና ፍቅር አላቸው፣ ይህንንም ፍቅር እና አክብሮ በተለያዩ ጊዜያት በማሪያም ስም የተሰየሙ አብያተ ክርስቲያናትን በመጎብኘት በግል እና በጋ ጸሎት በማድረግ አስመስክረዋል።

በተለይም ደግሞ የዛሬ አምስት አመት ገደማ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው እንደ ተመረጡ ቅዱስነታቸው በቀዳሚነት በሮም ከተማ እንብርት ላይ በሚገኘው እና  እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ግንባታው እንደ ተጠናቀቀ በሚነገርለት፣ በውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ በማሪያም ስም ከተሰየሙ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያንት መካከል በትልቅነቱ በሚታወቀው ሳናታ ማሪያ ማጆሬ” በመባል በሚታወቀው ባዚልካ  ተገኝተው አዲስ የተሰጣቸው ሐዋሪያዊ ተሎኮዋቸውን እና አጠቃላይ መላውን ቤተክርስቲያን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማሪያም በአደራ አስረክበው እንደ ነበረ ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በተለያዩ ጊዜያት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማሪያም ስም በተሰየሙ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በመገኘት እናታችን የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን የተለያዩ እንቅፋቶች ማለፍ እንችል ዘንድ ስለምትረዳን እናት የሆነችውን ማሪያም አጥበቀን መያዝ እንደ ሚገባን አዘውትረው እና በተገኘው አጋጣሚ እንደ ሚናግሩ የሚታወቅ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ማነኛውንም ዓይነት ጸሎት፣ እና ስብከት በሚያደርጉበት ወቅት ጸሎታቸውን ወይም ስብከታቸውን የሚያጠቃልሉት በማሪያም አማላጅነት ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በጥር 20/2010 ዓ.ም. በሮም ከተማ በሚገኘው “ሳንታ ማሪያ ማጆሬ” በተባለው እና በማሪያም ስም በተሰየመው ባዚልካ ተገኝተው መስዋዕተ ቅዳሴ ካሳረጉ በኃላ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ተስፋችን ተመልሶ እንዲያለመልም የሚያደገው የምንጠቀምባቸው የቴክኖሎጂ ወጤቶች ወይም የምንወጥናቸው ስንጽሰ ሐሳቦች ሳይሆኑ፣ “በውዥንብር ጎርፍ ውስጥ በምንገባበት ወቅት ተስፋ የምትሆነን እመቤታችን ቅድስ ድንግል ማሪያም ናት” ማለታቸውን ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወሳል።

“በማሪያም ውስጥ መጠጊያ እናገኛለን፣ ጸሎታችንም በፍጹም በከንቱ አይቀርም፣ አንድ ሕጻን ልጅ በእናቱ እቅፍ ውስጥ መግባት እንደ ሚፈልግ ሁሉ እኛም በእርሷ እቅፍ ውስጥ መኖራችን ደስታን ይሰጠናል” በማለት በወቅቱ ጨምረው ተናግረዋል።

“ማሪያም ባለችበት ቦታ ሁሉ ፍርሃት በፍጹም ሊያሸንፈን አይችልም”፣ በማለት በወቅቱ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እናታችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ከማንኛውም ክፉ ከሆኑ ነገሮች ትጠብቀናለች፣ ትከላከለናለች ብለዋል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ባልችበት ቤት ሁሉ ሰይጣን በፍጹም ወደ እዚያ ሊገባ አይችልም ያሉት ቅዱስነታቸው ማሪያም ባለችበት ቦታ ሁሉ የሚያስጨንቁን እና የሚያሸብሩን ነገሮች በፍጹም ሊኖሩ አይችሉም ፍርሃት እና ጭንቀት ሕይወታችንን ሊያሸንፉ በፍጹም አይችሉም ብለዋል።

በእዚህም መሰረት ተክኖሎጂ ወይም የራሳችን ጽንሰ ሐሳቦች የእኛን ተስፋ መልሰው እንዲያለመልም ማድረግ በፍጹም እንደ ማይችሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው ነገር ግን ተስፋችን በድጋሜ እንዲለመልም ማድረግ የሚችለው የማሪያም የፊት ገጽታ ብቻ ነው፣ በጭንቀት ጎርፍ ውስጥ በምንገባበት ወቅት በእርግጠኛነት ልትረዳን የምትችለው እርሷ ብቻ እንደ ሆነች ከገለጹ በኃላ በእየለቱ ማሪያም በልባችን እና በሕይወታችንም ውስጥ ሳይቀር ትገባ ዘንድ ልንጋብዛት የገባል ብለዋል።

እናት በሌለችበት ቦታ ሁሉ እምነታችን አደጋ ላይ እንደ ሚወድቅ በመግለጽ ስበከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እናት አማራጭ ሳትሆን የግድ የምታስፈልግ ናት፣ እርሷን መውደድ ማለት መቀኘት ማለትም አይደለም፣ "እንዴት መኖር እንደሚገባን ማወቅ ማለት ነው" ምክንያቱም "ያለ እናት እኛን ልጆች መሆን በፍጹም አንችልም፣ ለእዚህም ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በነበረበት ወቅት ለዩሐንስ “እቺውና እናትህ” ብሎ በአደራ የሰጠውም በእዚሁ ምክንያት ነው ብለዋል።

ይህንንም በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል . . .

 በእናት ጉዳይ ላይ ገለልተኛ መሆን ወይም ደግሞ ከእናት መለየት በፍጹም አንችልም፣ ይህንን ብናደርግ ግን ልጆች የምሆን ሕልውናችንን እና ማንነታችንን እናጣለን፣ ሐሳባዊ በሆነ መልኩ፣ በተለያዩ ዝግጅቶች በተወጠረ መልኩ፣ ያለ ምንም እምነት፣ ያለ ርህራኄ እና የለ መልካም ልብ የምንኖር ክርስቲያኖች እንሆናለን። ነገር ግን ያለ ልብ በፍጹም ልናፈቅር አንችልም፣ እምነታችንም በአንድ ወቅት የተጻፈ ውብ የሆነ ታሪክ ሆኖ ብቻ ይቀጥላል” ማለታቸውም መጥቀሳችን ይታወሳል።

በማሪያም እቅፍ ውስጥ መሰብሰብ እንደ ሚያስፈልግ በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የክርስትና እምነት ተከታይ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ከመጀመሪያው ጀምሮ ችግሮች ውስጥ በሚገቡባቸው ወቅቶች ሁሉ ወደ ማሪያም መሄድ እንደ ሚገባቸው ተረድተው የነበረ መሆኑን በመጥቀስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በችግር ውስጥ የሚገኙ ድኸ የሆኑ ሰዎች ችግራቸውን ለመቋቋም ያስችላቸው ዘንድ በአንድ ስፍራ እንደ ሚሰበሰቡ ሁሉ እኛም በችግራችን ወቅት በእናታችን ጉያ መሸሸግ ይኖርብናል ብለዋል።

በሕይወት ጉዞ ውስጥ ሕይወታችን መከራና ችግር ውስጥ በምትገባበት ወቅት ማሪያምን ብንማጸናት፣ ማሪያም በፍጥነት ታማልደናለች በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እርሷ ለጭቀቶቻችን ትኩረት ስለምትሰጥ፣ በሕይወታችንን ውስጥ ለሚገጥሙን ማንኛቸውም መገራገጮችን በትኩረት ስለምትመለከት በፍጹም አትዘገይም፣ በፍጹም አታሳፍረንም ካሉ በኃላ ይህንንም በይበልጥ ለማስረዳት በማሰብ “በሆስፒታል ውስጥ ሆኖ የሚሰቃየውን የልጅዋ ሥቃይ የምታይ አንድ እናት እንደ ማያስችላት እና እርሷም ከልጇ ጋር አብራ እንደ ምትሰቃይ ሁሉ እናታችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምም መከራና ችግሮች ውስጥ በምንገባባቸው ወቅቶች ሁሉ ከእኛ ጋር እንደ ምትሰቃይ በንጽጽር ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

“ሰለዚህም አሉ ቅዱስነታቸው” በስብከታቸው ማብቂያ ላይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ሕጻኑን ኢየሱስን በእጆቹዋ ላይ አቅፋ መያዙዋን ወደ የሚያሳየው ምስል እጃቸው በመጠቆም  “ስለእዚህ ወደ እርሷ በጥልቀት እንመልከት፣ የጥንት የኤፌሶን ክርስቲያኖች ለማሪያም ሰላምታን እንዳቀረቡላት እኛም እመቤታችንን ሰላም እንበላት ሁል ጊዜም በጸሎት ከእርሷ ጋር እንሁን ማለታቸውን መገልጻችን ይታወሳል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በግንቦት 1/2013 ዓ.ም የማሪያም ወር በመባል በሚታወቀው የግንቦት ወር በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ከምዕመናን ጋር በመሆን  የመቁጠሪያ ጸሎት ላይ ከደገሙ በኃላ እንደ ገለጹት “የማዳመጥ ጥበብ የታደልሽ እናት ሆይ! ጆሮዎቻችንን መክፈት እንችል ዘንድ እርጂን፣ በሺዎች ከሚቆጠሩ የዓለም ድምጾች ይልቅ የአንዲያ ልጅሽን ድምጽ ብቻ ለይተን እንድንሰማ እርጂን፣ አሁን እየኖርንበት በምንገኝበት ሁኔታ የምንገኛቸውን የተለያዩ ሰዎች በተለይም ደግሞ ድኾችን እና አቅመ ደካሞችን፣ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ በሚገብ ማዳመጥ እንችል ዘንድ አግዢን”።

“ውሳኔ የመስጠት ጥበብ የተካንሽ እናት ሆይ! ለልጅሽ ለኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ያለምንም ማቅማማት ታዛዥ መሆን እንችል ዘንድ አእምሮዋችንን እና ልባችንን አብሪ፣ በሌሎች ዓለማዊ ነገሮች ሳንወሰድ ለሕይወታችን ጠቃሚ የሆነ ውሳኔ መወሰን እንችል ዘንድ ብርታቱን ስጭን።

የተግባር እናት የሆንሽ ማሪያም ሆይ! እጆቻችን እና እግሮቻችን ወደ ሌሎች ሰዎች በፍጥነት በመጓዝ የለጅሽን ርኅራኄ እና ፍቅር እንድናደርስ፣ እንዳቺ በዓለም ውስጥ የቅዱስ ወንጌልን ብርሃን ማድረስ እንችል ዘንድ እርጂን። አሜን!” በማለት ማሪያም በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ያላትን የእናትነት ሚና ገልጸዋል።

 
All the contents on this site are copyrighted ©.