2018-05-26 12:38:00

የግንቦት 19/2010 ዓ.ም ሰንበት ዘጰራቅሊጦስ ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ


የግንቦት 19/2010 ዓ.ም ሰንበት ዘጰራቅሊጦስ ወይንም በዓላ ሃምሳ ሰንበትን ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

የእለቱ ምንባባት

  1. 1ኛ ቆሮ 15፡20-40
  2. 1ጴጥ 1፡1-12
  3. የሐዋሪያት ሥራ 1፡1-13
  4. የዮሐንስ ወንጌል 20፡1-18

 

ኢየሱስ ከሞት ተነሣ

በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ፣ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ መግቢያ ተንከባሎ አየች። ስለዚህም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ፣ “ጌታን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው።

“ከዚያም ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። 4ሁለቱም ይሮጡ ነበር፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ጴጥሮስን ቀድሞት ከመቃብሩ ደረሰ። ጐንበስ ብሎ ሲመለከት ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን በዚያው እንዳለ አየ፤ ወደ መቃብሩ ግን አልገባም። ይከተለው የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ እርሱም ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን አየ፤ እንዲሁም በኢየሱስ ራስ ላይ ተጠምጥሞ የነበረውን ጨርቅ አየ፤ ይህም ጨርቅ ከከፈኑ ተለይቶ እንደ ተጠቀለለ ነበር። ከዚያም አስቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባ፤ አይቶም አመነ፤ ይኸውም ኢየሱስ ከሙታን መነሣት እንዳለበት ገና ከመጽሐፍ ስላልተረዱ ነበር።

ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ታየ

ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ የቤታቸው ሄዱ፤ ማርያም ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ታለቅስ ነበር፤ እያለቀሰችም መቃብሩን ለማየት ጐንበስ አለች። የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች።

እነርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት። እርሷም፣ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አላውቅም” አለች። ይህን ብላ ዘወር ስትል ኢየሱስ በዚያው ቆሞ አየች፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም። እርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?”አላት።

እርሷም የአትክልቱ ቦታ ጠባቂ መስሎአት፣ “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው። ኢየሱስም፣ “ማርያም” አላት። እርሷም፣ ወደ እርሱ ዘወር ብላ በአራማይክ ቋንቋ፣ “ረቡኒ” አለችው፤ ትርጒሙም “መምህር ሆይ” ማለት ነው። ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሎአል ብለሽ ንገሪአቸው” አላት። መግደላዊት ማርያምም፣ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ “ጌታን እኮ አየሁት!” አለች፤ እርሱ ያላትንም ነገረቻቸው።

የእዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

 

ግንቦት 19/2010 . ሰንበት ዘጰራቅሊጦስ ወይንም በዓላ ሃምሳ ሰንበትን ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘጰራቅሊጦስ ወይንም ደግሞ በዓላ ሃምሳ የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን። እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ በሰላምና በጤና ኣደረሳችሁ። ይህ ዕለት በክርስትና እምነት ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው ትልልቅ በዓላት ኣንዱ ነው ምክንያቱም በዚህ ዕለት እንደቤተክርስቲያናችን ኣስተምህሮና እምነት መሠረት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለሓዋርያቱ እንደማይተዋቸው ቃል በገባው መሠረት የሚያበረታታውን፣ የሚያፅናናውን፣ ኃይል የሚሰጠውን መንፈስ ቅዱስ፣ የቅድስት ሥላሴ ሦስተኛ ኣካል በእመቤታችንና በሓዋርያት ላይ መውረዱን እንዘክራለን።

ይህንን በዓል ኣይሁዳውያን የሳምንታት በዓል የመከር በዓል ብለው ያከብሩታል ምክንያቱም ሁላችንም እንደምናውቀው ሰባት ቁጥር በኣይሁዳውያን ዘንድ ልዩ ትርጉም ኣለው ሰባት ቁጥርን የቅድስና የፍጽምና መገለጫ ኣድርገው ይወስዱታል። እግዚኣብሔር ዓለምን በስድስት ቀን እንደ ፈጠረ በሰባተኛው ቀን እንዳረፈ ኣይሁዳውያኑም በኦሪት ዘፀኣት 34፡21 ላይ እንደተገለጸው ስድስት ቀን እንዲሰሩና በሰባተኛው ቀን ግን እንዲያርፉ በተሰጣችው ትዕዛዝ መሠረት ሰባተኛ ቀንን ያከብሩ ነበር። እንዲሁም ሰባት ሳምንት ለሰባት ለሰባት ቀን ማለትም ኣርባ ዘጠኝ ቀን ከቆዩ በኋላ ቀጣዩን ቀን ማለት ነው ኣምሳኛውን ቀን ያለፉት የሰባት ሳምንታት መጨረሻ ቀን በማለት የሳምንቱ ሁሉ በዓል በኩራት ነው ብለው ያከብሩታል። በዚህም ዕለት ለእግዚኣብሔር መሥዋዕት ያቀርባሉ እግዚኣብሔርም ኣገራቸውን ከብቶቻቸውን እህላቸውን እንዲባርክላቸው ልመናና ምስጋና ያቀርባሉ።

እኛም ክርስቲያኖች በዚህ ዕለት ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ትልቅ መንፈሳዊ ኃይልና ልዩ መንፈሳዊ ጸጋ የተቀበልንበት ዕለት ነዉና በታላቅ ክብርና ድምቀት እናከብረዋለን። በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበት ዕለት ነው ምክንያቱም ይህ ኣፅናኝ ወደ እመቤታችንና ወደ ሓዋርያት ከመውረዱ በፊት ሁሉም ፈርተው በኣንድ ቤት ውስጥ  ተደብቀው ነበር ይህ ኃይል ሰጪ መንፈስ ቅዱስ ወደ እነሱ ከወረደ በኋላ ግን ውስጣቸው በደስታ ተሞላ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመላው ዓለም በታላቅ ድፍረትና ተነሳሽነት ለመስበክ ተነሳሱ። ይህም ቃል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በዮሓንስ ወንጌል 14፡26 ላይ የተናገረው ነው እንዲህም ይላል ኣብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው ኣፅናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። ይህንን በጥምቀታችን ኣማካኝነት የተቀበልነው መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በሙላት እንቀበለዋለን ይህ በመጀመሪያ በጥምቀታችን ኣማካኝነት የተቀበልነውን መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በኣዲስ መንፈስ እናድሰዋለን። ይህ መንፈስ ቅዱስ ወደ ውስጣችን ሲሰርፅ ሰባቱን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ማለትም ጥበብ ዕውቀት ማስተዋል ምክር ኃይል ርህራሄ ፈሪሃ እግዚኣብሄር የዞልን ይመጣል። እነዚህም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች የበለጠ መንፈሳዊ ኣገልግሎት የምንሰጥበትንና ራሳችንን በመንፈሳዊነት የምናንፅበት እንዲሁም ማንኛዉንም ዓይነት ፍርሃት ይሁን ድንጋጤ ይሁን ተስፋ መቁረጥ ይሁን ኣስወግደን በእርግጥም ስለእኛ ሲል የሞተውን ክርስቶስ በዕለታዊ ኑሮኣችን እንድንመሰክር ብሎም የእርሱን ፈለግ በመከተል የትኛውንም ዓይነት መስቀል በመሸከም እርሱ ወደደረሰበት ቦታ ለመድረስና የእርሱ መስቀል ተካፋዮ እንደሆንን እንዲሁ ደግሞ የእርሱ ዘለዓለማዊ ክብር ተካፋዮች እንድንሆን ብዙ እርዳታ ያደርጉልናል። መንፈስ ቅዱስ ወደ ውስጣችን በሚገባ ጊዜ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በቆሮንጦስ መልዕክቱ 15፡20 ላይ እንደሚለው በኣእምሮኣችን የበሰልንና ለኃጢኣት ደግሞ የሞትን ወይንም ደግሞ ክፉ ለሆነ ነገር እንደ ሕፃናት እንድንሆን ያደርገናል። ይህም ማለት ኃጢኣት ከማድረግ ፍጹም የተቆጠብንና መልካም በሆነ ነገር ሁሉ ግን ተሳታፊ እንድንሆን የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭና መልእክተኛ እንድንሆን ያደርገናል። መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ኣምሳ በእመቤታችንና በሓዋርያት ላይ የመውረድ ታሪክ በክርስትና እምነት ውስጥ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ኣማካኝነት በድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ከመፀነሱ በፊትና በኋላ ኣያሌ ጊዜ ተከስቷል ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የቤተክርስቲያንና የክርስቲያኖች ሁሉ ሕይወት ነው። መንፈስ ቅዱስ የመንፈሳዊነታችን ኣነሳሸና ይህንንም መንፈሳዊነት በታላቅ ትህትና በተግባር እንድናውለው ኃይል የሚሰጥ ነው። ለዚህ ነው ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በብዙ መልዕክቶቹ ላይ ለመንፈስ ቅዱስ ራሳችሁን ኣስገዙ በእርሱም ተመሩ ከእርሱም ጋር ተጓዙ እያለ ምክሩን የሚለግሰን። መንፈስ ቅዱስ በባሕሪው ከክፉ ሁሉ የምንርቅበትና ችግርን በሙሉ የምንፈታበት መልካምንና የመልካም ፍሬ ውጤት የሆኑትን ነገሮች ደግሞ በመላው ዓለም የምንዘራበት ሁልጊዜም ወደ እውነት የሚመራና ቅድስናን ተሸክመን እንድንጓዝ የሚያደርገን የእውነትና የጽድቅ መንፈስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ምንም እንኳን በኣዳም በኩል ሞት ቢያገኘንም በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ደግሞ ኣዲስ ሕይወት እንድንላበስ ምክንያት ሆኖልናል በዚህም ምክንያት በመጀመሪያው ንባብ ሲነበብ እንደሰማነው በጽድቅ እንድንነቃ ከኃጢኣትም እንድንርቅና በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ጸጋ እንድንመላለስ ያደርገናል። እግዚኣብሔር ለየትኛውም ደካማ ተክል ወይም ዘር የራሱን ኣካል እንደሚሰጥ እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ ለዚህ ለደካማው ሥጋችን መንፈሳዊ ብርታትንና ቁርጠኝነትን ያላብሰዋል። ይህም ደግሞ ዘወትር በእግዚኣብሔር ጥበብ ውስጥ እንድንመላለስና የእርሱን ቃል የእርሱን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እንድንተጋ ከእርሱም ጋር ኣብረን የቅድስናን ጎዳና እንድንጠርግና እንድናዘጋጅ ያደርገናል። የመጀመሪያው ሰው ኣዳም መሬታዊ አንደነበረ እኛም ዘወትር በኃጢኣት ውስጥ ብቻ ተሳታፊዎች ከሆንን ኣፈር ሆነን እንቀራለን ነገር ግን ልክ እንደ ሁለተኛው ሰው እንደ ክርስቶስ ሰማያዊ መሆን ከፈለግን የእርሱን መንገድ ለመከተል የምንችለውን ሁሉ ጥረት አናደርጋለን። የዚህ ጥረታችን ኣሳኪ የዚህ ጥረታችን ፈፃሚ ደግሞ ይህ ዛሬ የምናከብረው በዓል ባለቤት የሆነው የቅድስት ሥላሴ ሦስተኛ ኣካል የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው። ትልቁ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ሰውን በደከመ ጊዜ ማበረታታት ባዘነ ጊዜ ማፅናናት በሰነፈ ጊዜ ኃይልን መስጠት ከኃጢኣት እርቆ እንዲኖር ደግሞ ሁል ጊዜ በልባችንና በኣእምሮኣችን የተቀደሰ ሓሳብ ማሳደር ነው። መንፈስ ቅዱስ በየዕለቱ እኛን ለመርዳት በዙሪያችን ኣለ ስለዚህ ልባችንን ከፍተን ወደውስጥ እንዲገባ ብንጋብዘው ውስጣችን በመግባት የሕይወታችን መሪ ይሆናል ሁልጊዜም በለመለመው መስክ በጽድቅ ጎዳና በማይጠፋው ብርሓን ውስጥ ይመራናል።

ይህ የሁለተኛው የቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ መልዕክት በእሳት ምንም ያህል ቢፈተን ከማይጠፋው ወርቅ ይልቅ ኣብልጦ ስለሚጠነክር እምነት ይናገራል። በዚህም ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር ማንም ሰው የዚህን ዓይነት የጠነከረ እምነት ሊኖረው የሚችለው ቀጥተኛና የጠነከረ ግንኙነት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሲኖረው ብቻ ነው። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የዚህን ሰው ዕለታዊ ኣካሔድ የትኛውንም ዓይነት እንቅስቃሴ ኣነጋገርና ኣስትሳሰብ ሁሉ ስለሚመራ ይህ ሰው እንዲህ  ዓይነት የጠነከረ እምነት እንዲኖረው ያደርጋልና ነው። መንፈስ ቅዱስ በየትኛውም ኣቅጣጫ ሰው የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ፈለግ እንዲከተል የእግዚኣብሔርን መንገድ እንዲይዝ ኃይል የሚሰጥ ልዩ መንፈስ ነው። ለዚህ ነው በዛሬው የሓዋርያት ሥራ መልዕክት በቁጥር 8 ላይ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ የሚለን። ይህ ኃይል ነው እንግዲህ በመንፈሳዊነታችን እንድንበረታ ለኃጢኣት እንድንሞትና በጽድቅ መንገድ ለመጓዝ እንድንችል መንፈሳዊ ስንቅና መንፈሳዊ ትጥቅ የሚሆነን።

በዛሬው የዮሓንስ ወንጌልም ሲነበብ እንደሰማነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ኣድርጎ በመነሳቱ ምክንያት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ኣዲስ ምዕራፍ እንደከፈተ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ኣዲስ መንፈሳዊ ኣስተሳሰብና ኣካሄድ እንደዘረጋ በዛሬውም ዕለት ይህ በቤተክርስቲያን ላይ የወረደው መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያንን ይህንን የክርስቶስን ዓላማና ዕቅድ ይዛ እንድትቀጥል ኣድስ ኣቅጣጫ ያሲዛታል፣ ምክንያቱም የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሳት በታላቅ መንፈሳዊ ስሜትና ቁርጠኝነት ለመመስከር በዓለም ሁሉ የእርሱን ወንጌል ለማዳረስ ትልቅ መንፈሳዊ ኃይልን መንፈሳዊ ድፍረትን የተቀበለችበት ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ የጀመረችበት ዕለት በመሆኑ ነው። ለዚህም ነው ዛሬ ቤተክርስቲያን የተወለደችበት ቀን ነው ብለን የምንናገረው። ስለዚህም በዚህ ቤተክርስቲያን በተወለደችበት ዕለት ከሓዋራያቶች ጋር የነበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዛሬም የቤተክርስቲያን እናት ናትና ዛሬም የቤተክርስቲያን ጠባቂ ናትና እኛን ሁላችንን ከክፉ ሁሉ ትጠብቀን። ሓዋርያቶች ኣንድነታቸው ሳይበታተን በሕብረት እስከመጨረሻ ነቅተው እንዲጠብቁና እንዲተጉ ያደረገች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዛሬም የኛን የክርስቲያኖችን ኣንድነት ታጠንክርልን።  ይህ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያገኘነውን ኣዲስ ሕይወት እስከ መጨረሻ ይዘን ለመጓዝ እንድንችል ከጎናችን ትቁምልን። ይህ የቅድስት ሥላሴ ሦስተኛ ኣካል የሆነ መንፈስ ቅዱስ ጥንት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ላይ እንደወረደ ዛሬም በእኛ በእያንዳዳችንና በቤተክርስቲያናችን ላይ ይረፍብን።
All the contents on this site are copyrighted ©.