2018-04-02 12:53:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እያንዳንዱ የቅጣት ፍርድ ተስፋን የሚሰንቅ ሊሆን ይገባል ማለታቸው ተገለጸ።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እያንዳንዱ የቅጣት ፍርድ ተስፋን የሚሰንቅ ሊሆን ይገባል ማለታቸው ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን የተናገሩት ትናንት የተከበረውን የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ምክንያት በማድረግ በሮም ከተማ፣ ትራስቴቨረ በተባለ ስፍራ በሚገኘው በረጂና ቸሊ ማረሚያ ቤት ለሚገኙት የሕግ ታራሚዎች ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ቅዱስነታቸው ሕግ ታራሚዎችን በመንፈስ አብሯቸው እንዳሉ ተናግረው ተስፋ እንዳይቆርጡ አሳስበዋል። ወደ ስፍራው የመጡትም ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረኝን ለማከናወን በእርሱ ተልኬ ነው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ ማረሚያ ቤት የሕግ ታራሚዎችን ሲጎበኙ አራተኛ ጊዜ አችቸው ሲሆን በሮም ትራስቴቨረ የሚገኘውን ረጂና ቸሊስ ማረሚያ ቤት ሲጎበኙ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ለማረሚያ ቤቱ ሰራተኞችና ለሕግ ታራሚዎች በሙሉ በዕለቱ የተነበበውን የቅዱስ ወንጌል ቃል መሠረት በማድረግ ባሰሙት ስብከታቸው እርሳቸው እንዳደረጉት ራስን ዝቅ በማድረግ ኢየሱስ የመረጠውን መንገድ በመከተል ለሌሎች ትህትናን ማሳየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው ወደ ስፍራው እንደደረሱ በቅድሚያ ከማረሚያ ቤቱ የሕግ ታራሚዎች መካከል በሕመም ላይ የሚገኙትን ከጎበኟቸው በኋላ ወደ መስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ገብተው፣ ከሰባት የተለያዩ አገሮች ማለትም ከኢጣሊያ፣ ከፊሊፒን፣ ከሞሮኮ፣ ከሞልዳቪያ፣ ከኮሎምቢያ፣ ከናይጀሪያ እና ከሴራሊዮን የመጡ የካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስ፣ የእስልምናና የቡዳ እምነት ተከታይ የሆኑትን የ12 የሕግ ታራሚዎችን እግር የማጠብ ስርዓት ፈጽመዋል። የእግር ማጠብ አገልግሎት በኢየሱስ ዘመን በባሪያና በጣም ዝቅተኛ በሆነ የሕብረተሰብ ክፍል እንደሚከናወን ተናግረው፣ ኢየሱስም የሐዋርያቱን እግር ያጠበበት ምክንያት እኛም ትህትና በተሞላ መንገድ፣ ራስን ዝቅ በማድረግ እርስ በርስ እንድንዋደድ የመጀመሪያ ምሳሌ ለመሆንና ይህን ሊያስተምረን ፈልጎ እንደነበር ገልጸዋል። ሁለቱ ሐዋርያት ኢየሱስን አንደኛውን በቀኙ ሌላኛውን በግራ እንዲያስቀምጥ ብለው ያቀረቡትን የወንጌል ክፍል ጠቅሰው፣ ኢየሱስም እነዚህን ሐዋርያት በፍቅር ዓይን በመመልከት የመንግሥታት መሪዎች ትዕዛዝ መስጠትን እንጂ በመካከላቸው አንዱ ሌላውን ማገልገል ወይም አንዱ ለሌላው መታዘዝ እንደማይፈልጉ መናገሩን አስታውሰዋል።

የሚያዛችሁ አለቃ ሊያገለግላችሁም ይገባል። የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነትም ይህ ነው። የዚያን ጊዜ ባሕልና ወግ ቀይሮታል። የዘመናችንም ባሕል እንዲቀየር መልዕክት ያስተላልፋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የተከበረ እና የተናቀ የለም። ሁሉም እኩል ናቸው። ይህ በተግባር ቢውል ኖር ስንት ጦርነትና ስንት የሰው ሕይወት ከሞት መትረፍ ይችል ነበር ብለዋል። የበርካታ መንግስታት መሪዎችና ነገስታት ይህን ቢያስተውሉ ኖሮ የስንቱ ሰው ሕይወት ከሞት ይተርፍ ነበር ብለውል። ሃብታምና ብርቱ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በድሕነታቸው የተናቁ የተገለሉ የደከሙ ብዙ እንዳሉ መዘንጋት የለብንም ብለዋል። የእነዚህ ደሆችና ደካማ የሆኑ ሰዎች አስተዋይ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም ራሱን በትህትና ዝቅ በማድረግ በተግባር አሳይቶአል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለሕግ ታራሚዎች ባሰሙት የማጽናኛ ስብከታቸው፣ ከምናውቃቸው፣ ከምንወዳቸው ጋር በሰላም መቆየት ቀላል ነው። ነገር ግን እኛን ካሰቃዩን፣ እኛን ከማይወዱን ጋር በሰላም መኖር ቀላል አይደለም። ዛሬ በጸሎታችን የሚወዱን እና የሚጠሉንም በሙሉ የምንወድበትን ጸጋ እንዲሰጠን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠይቅ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በሕይወታችን ችግሮች ቢገጥሙንም ተስፋ መቁረጥ እንደማያስፈልግ አሳስበዋል። እያንዳንዱ ቅጣት ተስፋን እንደሰነቀ መዘንጋት የለበትም። የሞት ቅጣት ሲሆን ግን ሰብዓዊም ክርስቲያናዊም አይደለም። እያንዳንዱ ቅጣት ሰዎችን ወደ መልካም አቅጣጫ የሚመራና፣ ቅጣትን ጨርሶ በሕብረተሰቡ መካከል አንዱ ለሌላው መልካምን ለማድረግ ዕድልና ተስፋን የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል ብለው ለታራሚዎቹ መልካም ተስፋን ተመኝተውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃን ጳጳሳት ጉብኝታቸውን አጠቃልለው ወደ ቫቲካን ከመመለሳቸው በፊት ከታራሚዎቹ መካከል ሙሉ በሙሉ ከሰው ጋር መገናኘት ከማይፈቀድላቸው ጋር ከተገናኙ በኋላ መስዋዕተ ቅዳሴውን ባሳረጉበት መንበረ ታቦት ላይ ለማረሚያ ቤቱ የሚሆን ስጦታ አስቀምጠውላቸዋል።                       
All the contents on this site are copyrighted ©.