2018-03-31 18:52:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለዓለም አቀፍ ወጣት ካቶሊካዊያን ተወካዮች ያደረጉት ንግግር።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለዓለም አቀፍ ወጣት ካቶሊካዊያን ተወካዮች ያደረጉት ንግግር።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለዓለም አቀፍ ወጣት ካቶሊካዊያን ተወካዮች ያደረጉት ንግግር።

በሚቀጥለው ዓመት በጥቅምት ወር 2011 ዓ. ም. በወጣቶች ጉዳይ ዙሪያ ለመወያየት በታቀደው ለ15ኛው ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ዝግጅት እንዲሆን በማለት በሮም ከመጋቢት 10 እስከ 15 ድረስ ዓለም አቀፍ የወጣት ካቶሊካውያን ተወካዮች ስብሰባ ተካሂዷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ዓለም አቀፍ የወጣት ካቶሊካዊያን ተወካዮች ስብሰባ ላይ በመገኘት 300 ለሚሆኑ የስብሰባው ተካፋዮች ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ የሚከተለውን ንግግር አድርገውላቸዋል።

ውድ ወጣቶች ሆይ!

በቅድሚያ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። በዚህ የስብሰባ ወቅት እያንዳንዳችን ለመንፈሳዊ ጉዞአችን ይጠቅማል ብለን በልባችን የምናስበውን ሃሳብ በግልጽ በመነጋገር እንደምንወያይ ተስፋ አደርጋለሁ። በግልጽ መነጋገር ስንል ፍርሃትን በማስወገድ መነጋገር ማለት ነው። ምናልባትም በምንናገረው ጉዳይ ሌሎችን የምናስቀይም ከሆነ ይቅርታን ጠይቀን ሃሳባችንን መግለጽ መቀጠል ያስፈልጋል። ሲናገሩ የሚያስቀይሙን ቢኖሩም በትሕትና ማዳመጥ ያስፈልጋል። የመናገር መብት እንዳለ ሁሉ የማዳመጥም መብት አለ።

ጥሪያችንን አክብራችሁ ወደ ሮም ስለመጣችሁ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባልሁ። አንዳንዶቻችሁ ረጅም መንገድ በመጓዝ ወደዚህ ቦታ መጥታችኋል። ሌሎች ደግሞ በየአገሮቻቸው ምሽት ከመሆኑ የተነሳ ወደ መኝታ የሚሄዱበት ሰዓት ነው። ቢሆንም በያሉበት ሆነው በብዙሃን መገናኛዎች የስብሰባችሁን ሂደት እየተከታተሏችሁ ይገኛሉ። ከተለያዩ አገሮች ሕዝቦችና ባሕሎች መካከል የመጣችሁ፣ ከተለያዩ የእምነት ክፍሎች የተላካችሁ ናችሁ። በዚህ ስብሰባ ላይ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ እምነት ተከታዮች ናችሁ። አማኝ ያልሆናችሁም ትገኛላችሁ። ሆኖም በዚህ ዓለም አቀፍ የውጣቶች ስብሰባ ላይ በመገኘት ሃሳባችሁንና አስተያየታችሁን ለማካፈል ባላችሁ ፍላጎት ተነሳስታችሁ መጥታችኋል። ከእናንተ በተጨማሪ ይህን ስብሰባ በተለያዩ አገሮች ሆነው በማሕበራዊ መገናኛዎች በኩል ሃሳባቸዉን የሚያካፍሉንንም ጭምር ላመሰግናቸው እወዳለሁ።

ለ15ኛው ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ስኬታማነት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ያሉትን አስተባባሪ ዋና ጽሕፈት ቤት አባላትን፣ ብጹዕ ካርዲናል ባልዲሰሪን እና ረዳቶቻቸውን በሙሉ አመሰግናቸዋለሁ። ለሲኖዶሱ ከሚያበረክቱት ሰፊ አስታውጽዖ ጋር የሲኖዶሱ አዘጋጅና አስተባባሪ ከመሆን በተጨማሪ እንደ ወጣት ተወካዮችም በመሆን የሲኖዶሱ ግንባር ቀደም ተዋናይ ናችሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ በብዙ ቦታዎች እንደተጠቀሰው፣ እግዚአብሔር ወጣት ነቢያት ለሆኑት፣ ለሳሙኤል፣ ለዳዊት እና ለዳንኤል፣ ብዙ አጋጣሚዎችን በመጠቀም መናገርን ይወድ ነበር። ወጣቱ ነቢዩ ሳሙኤል የእግዚአብሔርን ድምጽ እንደሰማ የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ሳነብ ያስደስተኛል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው በዚያን ጊዜ ሕዝቡ የተበታተነ በመሆኑ የእግዚአብሔርን ድምጽ ለመስማት ይህን ያህል የተረጋጋ አልነበረም። ነገር ግን ይህ ወጣት በር ከፍቶ የእግዚአብሔርን ድምጽ ለመስማት ወጣ። በአስቸጋሪ ጊዜያት እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ርህራሄ ቀጣይነት እንዳለው ለማስረዳት ሲል ወጣቶችን ይመርጥ ነበር። ምክንያቱም ወጣቶች ፍርሃትን አስወግደው በድፍረት እውነትን ስለሚናገሩ ነው። ነቢዩ ዳዊት ምንም እንኳን በደለኛ ቢሆንም ከልጅነቱ ጀምሮ ደፋር ነበር። ሲወለድ ቅዱስ፣ ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ ሆኖ የሚወለድ ሰው የለም። ነገር ግን ሰዎች በሙሉ ሐጢአተኞች ቢሆኑም እግዚአብሔር በልባቸው ውስጥ ያስቀመጠው፣ መልካምን የማድረግ ፍላጎት አላቸው። ይህ ደግሞ በሕይወታቸው ውስጥ እየተንጸባረቀ ወደ ፊት እንዲጓዙ ያደርጋቸዋል። ይህም መልካምና ደስ የሚያሰኝ የሕይወት አካሄድ ነው። ቅድስና የተሰጠው ለካህናት ወይም ለደናግል በአጠቃላይም ለቤተ ክህነት ብቻ እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ ሊኖሩ ይችላሉ። እንደዚህ ማሰብ ትክክል አይደለም። ሁላችንም ለቅድስና ተጠርተናል። እናንተ ወጣቶች ያላችሁን ሃይል እና ድፍረት በመጠቀም መናገርን፣ ማዳመጥን፣ መቃለድን፣ መሳቅንና ማልቀስንም ትችሉበታላችሁ። እኛ አዛውንት ግን ነገሮችን እንደየ አመጣጣቸው ስለምንቀበላችው ማልቀስ አይሆንልንም።

ብዙን ጊዜ ስለ ወጣቶች ስንናገር እነርሱ ራሳቸው በውይይቱ እንዲሳተፉ በማድረግ ሃሳባቸውን ከእነርሱ ለመስማት የምናደርገው ፍላጎት ዝቅተኛ ነው። ወጣቶች ለሚያስመዘግቡ አስደሳች የሥራቸው ወጣቶች እናደንቃቸዋለን። በእርግጥ አድናቆትን መስጠት ሰዎችን ለማስደሰት ወይም ለማበረታታት ብለን ከምናደርጋቸው ­መንገዶች መካከል አንዱ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ለሰዎች የምንሰጠው አድናቆት ከልባችን ሳይሆን ቀርቶ ከአንገት በላይ ብቻ ከሆነ ሰውን እንደ ማሞኘት ይቆጠራል። ሰው ሞኝ ከሆነ የሚጠይቁትን በሙሉ ሊያደርግ ወይም ሊያከናውን ይችላል። እናንተ ወጣቶች ግን ሞኞች አይደላችሁም። በወጣቶች ዙሪያ የተደረጉ በርካታ መልካም የተባሉ የጥናት ውጤቶች አሉ። እነዚህ የጥናት ውጤቶች ጠቃሚ ናቸው። ነገር ግን ወጣቶችን ፊት ለፊት አግኝተዋቸው ወይም አነጋግረዋቸው የሚያገኙትን መልካም ውጤት የሚያክል የለም። እንደሚታወቀው ስለ ወጣትነት ዕድሜ ብዙ ይጻፋል፣ ብዙ ጉባኤዎችም እንደሚካሄዱ ይታወቃል። ነገር ግን መነጋገር ያለብን ስለ ወጣትነት ዕድሜ ሳይሆን ስለ ወጣቶች መሆን አለበት። ወጣቶችን በማሳተፍ ታሪካቸውንና ሕልማቸውን ከራሳቸው መስማት ያስፈልጋል። ልባቸው ምን እንደሚያስብ ጠይቀናቸው የሚሉንን ከእነርሱ መስማት ያስፈልጋል።

ችግር እንዳይመጣባቸው ከመስጋት የተነሳ የወጣቶችን ጥያቄ ወይም ሃሳብ ማዳመጥ የሚፈሩ ሰዎች አሉ። በዚህ ምክንያት ከወጣቶች መራቅን ወይም አለ ማቅረብን የሚመርጡ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ብዙ ሰዎች በሩቅ ሆነው ከወጣቶች ጋር በስልኮቻቸው ብቻ መልዕክትን መለዋወጥ ወይም ፎቶግራፍ መላላክን ይመርጣሉ። ይህን ከማድረግ ይልቅ ወጣቶችን በቅርብ መያዝ እና ከእነርሱ ጋር መሆን ያስፈልጋል። ያለንበት ባሕል ምንም እንኳ እድሜአችን የገፋ ቢሆንም በአለባበስ፣ በአንጋገር ወጣቶችን በመምሰል የወጣትነት ጊዜአችንን ረጅም እንድናስመስል ሲጋብዘን በሌላ ወገን ደግሞ በወጣትነ ዕድሜ ማከናወን ያለብንን ተግባር እንዳናከናውን ያደርገናል። ሰዎች ዕድሜአቸው እየጨመረ በሄደ ቁጥር በመኳኳል ሆነ በሌላ መንገዶች ወጣት መስለው ለመታየት ይፈልጋሉ። ምክንያቱም ወጣት መስለው ከታዩ ከወጣቶች ጎራ ከተሰለፉ ከወጣቶች የሚሰነዘሩ ጥያቄዎች አይመለከተንም ብለው ስለሚያስቡ ነው። ከሥራ ማጣት የተነሳ ለኑሮአችሁ እንኳ በቂ ዋስትናን የማይሰጥ ሥራ በመፈለግ ላይ ትገኛላችሁ። ይህ ችግር በየአገሮቻችሁ ስለ መኖሩ እርግጠኛ ባልሆንም በብዙ አገሮች፣ ለምሳሌ በኢጣሊያ ከ25 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑ የሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር 35 በመቶ ገደማ ይደርሳል። በሌላው የኢጣሊያ ጎረቤት አገር የሥራ ፈላጊ ወጣት ቁጥር 47 በመቶ ደርሷል። እንደዚሁም በሌላ የአውሮጳ አገር እስከ 50 በመቶ ይደርሳል። በዚህ ሁኔታ አንድ ሥራ የሌለው ወጣት ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ይታመማል፣ ይበሳጫል፣ ለጎጂ ሱሶች ይጋለጣል፣ ራሱን ወደ ማጥፋት ደረጃ ላይ ይደርሳል፣ ወይም ወደ ሌላ አገር ይሰደዳል፣ ይባስ ብሎ በአሸባሪነት ጎራ ይሰለፋል ወይም ደሞዝ ስለሚከፈለው በአማጽያን ቡድን ይመለመልና ወደ ጦር ሜዳ ይሄዳል። በዚህ መልክ በወጣቶች ላይ ለሚደርስ ቀውስ ሕብረተ ሰቡ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል። ስለዚህ ወጣቶች የችግራችሁን ዋና ምክንያት በሚገባ ስለምታውቁ በግልጽ ብትናገሩ መፍትሄን ለማፈላለግ ይጠቅማል። እንደ እውነቱ ከሆነ እናንተ ወጣቶች ብዙን ጊዜ የራሳችሁን አዲስ ባሕል በመፍጠር ከሕብረተ ሰቡ መካከል ትገለላላችሁ። እናንተ የምትፈጥሩት አዲስ ባሕል ለሌሎች ግልጽ ባይሆንም ነገር ግን እናንተ ተገለገሉበታላችሁ። እነዚህን አዳዲስ ባሕሎቻችሁን ማየትና ማወቅ እንፈልጋለን።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሙሉ ተቀባይነት እንዲኖራችሁ ያስፈልጋል። ቅዱስ ወንጌልም የሚጠይቀን ይህን ነው። ጎረ ቤትን መውደድ፣ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ በሕብረት መጓዝ፣ ፍርሃትን አስወግደን በመቀራረብ ያለንን በጋራ መካፈል እንደሚያስፈልግ ያሳስባል። ከዚህ የቅድመ ሲኖዶስ ስብሰባ መልካም ሃሳብ እንደሚገኝ ተስፋ አለኝ። ቤተ ክርስቲያን ዛሬ እያንዳንዳችሁን ለማዳመጥ ተዘጋጅታለች። ምክንያቱም እግዚአብሔርና ታሪክ የሚጠይቃችሁን ነገር በትክክል እንድናውቅ ያስፈልጋል። እናንተን ማጣት ማለት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ለመቅረብ ከምንጓዝበት መንገድ አንዱን እናጣለን ማለት ነው።

ቀጣዩ የካቶሊካውያን ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ፣ ወጣቶች የተጠሩበትን የፍቅርና የሙሉ ሕይወት ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተውል በታከለበት ሁኔታ ተገንዝበው ትክክለኛውን ወሳኔን ማድረግ እንዲችሉ በፍቅርና በጥበብ እገዛ እንዲደረግላቸው ይጠይቃል። እኛ ሁላችን ጥሪ አለን። እናንተ ወጣቶች ይህን ጥሪ በጊዜ ተቀብላችሁ ወደ ተግባር ለመግባት በሚያስችላችሁ የዕድሜ ደረጃ ላይ ትገኛላችሁ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው የፍቅር ጥሪን ያቀርባል። ይህን ጥሪ በትክክል ያስተዋልን ከሆነ በደስታ የሚሞላን የጸጋ ስጦታ መሆኑን መረዳት እንችላለን (ማቴ. 13 ፡ 44–46)። እግዚአብሔር እናንተን እንደሚወዳችሁና እንደሚፈልጋችሁ እርግጠኞች ሁኑ። እርሱ ታማኝ ነው፣ ተስፋውንም በእናንተ ላይ አድርጎአል። እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ላደረጉት ሁሉ እግዚአብሔር ታማኝ መሆኑን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ። ለመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት “ምን ትፈልጋላችሁ?” (ዮሐ. 1፡38) በማለት ያቀረበውን ተመሳሳይ ጥያቄ እናንተንም ይጠይቃል። እኔም በዚህ ሰዓት ለእያንዳንዳችሁ “በሕይወትህ ምን ትፈልጋለህ?” በማለት እጠይቃችኋለሁ። እግዚአብሔር ሲጠራችሁ አቤት በሉት፣ እርሱን ማዳመጥ እውነተኛ ደስታን ይሰጣል። የሕይወታችሁ ዓላማ ምን እንደሆነ፣ ምንስ እንደምትመኙ ማወቅ እንፈልጋለን። እግዚአብሔርም በሕይወት ጉዞአችሁ አብሮአችሁ መጓዝ ይፈልጋል። እኛም ቤተ ክርስቲያን እንደመሆናችን እውነተኛ ደስታ ያለበትን የሕይወት ጉዞአችሁን ከእናንተ ጋር በሕብረት መጓዝ እንፈልጋለን። ሕይወታችንን በእውነተኛ ደስታ የሞላንን ኢየሱስ ክርስቶስ ለግላችን ብቻ ማድረግ አንችልም። ጓደኞቻችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን በውል ባያውቁትም የመዳን ጥሪውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

ቀጣዩ የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ፣ መላዋ ቤተ ክርስቲያን እንድትታደስ ጥሪውን ያቀርባል። የጳጳሳት ሲኖዶስ አዘጋጅ ጽሕፈት ቤት በድረ ገጹ ያሰራጫቸውን ቃለ መጠይቆች ስመልከት፣ ወጣቶች አስፈላጊና ትክክለኛ የሕይወት ምርጫን ለማድረግ ሲነሱ የአዋቂዎችን እገዛ ይፈልጋሉ። ወጣቶች ተሰጧቸውንና ችሎታቸውን ለማሳየት ብርታትንና ድፍረትን የሚሰጡ ሰዎችን አጥተው መቸገራቸው ተስተውሎአል። በሌላ በኩል ወጣቶች አደገኛ በሆኑ የአልኮልና የአደንዛዥ ዕጽ መጎዳታቸው ተስተውሎአል። ለውጣቶች ከቀረቡት ቃለ መጠይቆች የተሰበሰቡት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በሕይወታቸው ላይ እየደረሰ ካለው አደጋ በፍጥነት ማውጣት እንደሚያስፈልግ ያሳስባል። ቤተ ክርስቲያን ወደ ወጣቶች ለመድረስ የሚያስችላትን አዳዲስ ዘዴዎችን ማወቅ ያስፈልጋል። ሙሴ ሕዝቡን ከአደጋ ለመጠበቅ ብሎ ፍቅር የሚገኝበት መንገድ የትኛው ነው ብሎ በጠየቀ ጊዜ እግዚአብሔር መልስ ተሰጠው። በእውነት ለዚያ ሕዝብ እግዚአብሔር ይህን ያህል ቅርብ ነው ወይ ያስብላል። ስለዚህ የፍቅር ዋንኛው ምልክት ከሕዝብ ጋር መሆን ነው። የዛሬው ወጣት ጥያቄም ቤተ ክርስቲያን በቅርብ እንድትሆን የሚል ነው። እናንተ ክርስቲያኖች፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አለኝታነት የምታምኑት፣ እናንተ ካቶሊካዊ ወጣቶች በመካከላችሁ መቀራረብ እንጂ መራራቅ ሊኖር አይገባም። መራራቅን የሚያመጡ መንገዶች ብዙ ስለሆኑ እነዚያን መንገዶች ከመጓዝ  ራሳችሁን ጠብቁ። የዛሬው ወጣቶች፣ ክርስቲያኖች በሙሉ ተቀራርበው መኖርን ይፈልጋሉ። የወጣቶችን ስሜት የሚያውቁ፣ ወጣቶችን የሚያዳምጡ፣ የሚመክሩ፣ የሚገስጹ፣ መሪ መሆን የሚችሉ የቤተ ክህነት ወይም የምዕመናን ወገን በመካከላቸው እንዲገኙ ይፈልጋሉ።  

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ወጣቶችን አስመልክቶ ያስቀመጠው አስደናቂ መልዕክት ትዝ አለኝ። ይህ መልዕክት የዛሬውን ወጣቶች በማነቃቃት፣ ስግብግብነትን በማስወገድ የተሻለ ዓለምን ለመገንባት ብርታትን ይሰጣል። ይህ መልዕክት ወጣቶች በድፍረትና በእምነት የሚጓዙበትን አዲስ ጎዳናን እንዲፈልጉ፣ ዘወትር ኢየሱስን በመመልከት፣ ልባቸውንም ለመንፈስ ቅዱስ ክፍት በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል እና ለማደስ ያዘጋጃቸዋል። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ራሷን ማደስ የምትችለው በደካማነቷ የተነሳ ለሠራቻቸው ሃጢአቶች ምሕረትን በመለመን፣ ራሷን ለሌሎች አገልግሎት በማቅረብ፣ ከእግዚአብሔር የተሰጣትን ተልዕኮ በታማኝነት በመፈጸም፣ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጣት ሃይል ነው። የምታበስረውን የወንጌል መልዕክት በተግባር መኖር ስትጀምር ነው።

ውድ ወጣቶች ሆይ! የወንጌል መልዕክት በየጊዜው አዲስ ስለ ሆነ የቤተ ክርስቲያን ልብም ገና ለጋ ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮች፣ እምነት የሌላችሁ ብትሆኑም፣ ራሳችንን ከወንጌል መልዕክት ጋር ማስተባበር ይጠበቅብናል። ከውድቀት መትረፍ የሚያስችለንን ሃይል ለማግኘት፣ ጉዞአችንን አጠናክረን ወደ ፊት መጓዝ እንድንችል ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንደገና ተመልሰን መምጣት አለብን።  አዲስ ጉዞን መጀመር መስዋዕትነትን ሊጠይቅ ቢችልም ምንም መፍራት የለብንም። ስህተትን የሚፈራ ሰው አይታረምም። ኪሳራን የሚፈራ የንግድ ተቋም አያተርፍም። ውድቀት ሳያስፈራችሁ በምክር በመታገዝ በጥንቃቄ ወደ ፊት ተጓዙ። ችግርን የማይጋፈጥ ወጣት ምን እንደሚያጋጥመው ታውቃላችሁ። በሃያ ዓመቱ ያረጃል። አንድ ልጅ በወጣትነቱ የሚያረጅ ከሆነ፣ ቤተ ክርስቲያንም እንደዚሁ ናት። ይህን የምናገረው ታላቅ ሐዘን እየተሰማኝ ነው። ብዙ የክርስቲያን ወጣት ማሕበራት፣ ወይም የክርስቲያን ጎልማሶች ማሕበራት አርጅተው ሲመነምኑ ተመልክቼአለሁ። ያረጁበትም ምክንያት ፍርሃት ስለ ያዛቸው ነው። የፈሩትም ወደ ሕዝብ ዘንድ መውጣትን፣ ሊያጋጥማቸው የሚችል ፈተና ስላስፈራቸው ነው። አንድን ማሕበር ለመምራት ድፍረት ያስፈልጋል። የቤተ ክርስቲያን አለኝታ የሚሆኑ ወጣቶች ያስፈልጉናል። ራሱን ተኳኩሎ ወጣት የሚመስል ሳይሆን በሁለመናው ወጣት እና ደፋር የሆነ ክፍል ያስፈልገናል። “የተለመደ ነገር ስለ ሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም” ማለትን አስወግዱ። ይህ አባባል እንደ ነፍስ ማስታገሻ ነው። “የተለመደ ነገር ስለ ሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም” ከሚለው አባባል መላቀቅ በክርስትና ሕይወት እንድናድግ፣ እንድንለመልም ያደርገናል። ክርስቲያኖች በሙሉ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን እንዲያነቡ እመክራለሁ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች የተለያዩ ዘዴዎችን የሚያፈልቁ ሰዎች በመሆናቸው ወደ ፊት የመጓዝን ጥበብ አውቀውበታል። እናንተ ወጣቶች አዳዲስ ባሕሎችን መገንባት ታወቁበታላችሁ። ነገር ግን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፣ ምክንያቱም ይህ ባሕል አንዴ ሰርጾ ከገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስወገድ አይቻልም። አዲስ ባሕልን መገንባት አንድ እርምጃ ወደ ፊት መሄድን ያመለክታል ነገር ግን መልካም የሆኑ እሴቶችን የያዘ መሠረትን መልቀቅ የለበትም። መሠረት የሚሆኑትም አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ናቸው። ወጣት ነቢያት ያስፈልጉናል። ነገር ግን የሽማግሌዎችን ሕልም ካልጨመረበት ነቢይ መሆን ከቶ አይቻልም።

በመጨረሻም በዚህ የውይይት ሳምንት ውስጥ በግልጽና በሙሉ ነጻነት ሃሳባችሁን እንድታካፍሉ አሳስባችኋለሁ። የጉዳዩ ቀዳሚ ተዋናይ ስለሆናችሁ ሃሳብን በነጻነት መናገርና መግለጽ እጅግ አስፈላጊ ነው። እኔ እፈራለሁ፣ የእኔ ካርዲናሌ ከሰማኝ ምን እሆናለሁ ሳትሉ ሃሳባችሁን፣ ምኞታችሁን፣ ሕልማችሁን አውጥታችሁ እንድትናገሩ አደራ እላችኋለሁ። እባካችሁ ለእኔ መጸለይን አትዘንጉ። መጸለይ የማትችሉ ከሆናችሁ ቢያንስ በመልካም አስታውሱኝ።                                                  
All the contents on this site are copyrighted ©.