2018-03-28 15:26:00

የሕማማት ሣምንት


የጎርጎሮሳዊያኑ  የቀን ቆጣጠር በሚከተሉ ክርስቲያኖች ዘንድ አሁን ያለንበት ወቅት የሕማማት ሣምንት እንደ ሆነ ይታወቃል። በእዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስርዐተ አምልኮ ደንብ መሰረት እኛን ለማዳን እና ከእግዚኣብሔር ጋር እኛን ለማስታረቅ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ያቀረበው ክርስቶስ ተላልፎ መሰጠቱን፣ መንገላታቱ፣ በመስቀል ላይ እንደ ሌባ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ መቀበሩን እና ከሙታን መነሳቱን እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተከናወኑባቸው ሦስት ዋና ዋና ቀኖች በተለየ ሁኔታ በታላቅ መነፍሳዊነት የከበራሉ። እነዚህ ሦስት ቀኖች የሚከተሉት ናቸው።

  1. ኢየሱስ መከራውን ከመቀበሉ በፊት ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን ራት ከመብላቱ በፊት የሐዋሪያቱን እግር ያጥበበት፣ እርሱ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የጀመረውን መንፈሳዊ ተልዕኮ እንድያስቀጥሉ በማሰብ ምስጢረ ክህነትን የመሰረተበት፣ የመጨረሻ ራት ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር የተካፈለበት የጸሎተ ሐሙስ ማታ እለት በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
  2. በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የተፈረደበት፣ የተሰቃየበት፣ በመስቀል ላይ ተስቅሎ የሞተበት እና የተቀበረበት የስቅለተ ዐርብ እለት ይጠቀሳል።
  3. በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ኃይል ሞትን ድል አድጎ ከሙታን የተነሳበት የእለተ ሰንበት ቀን ይከበራል።

በእነዚህ የእምነታችን መሰረት በሆኑት በሦስቱ ቀናት ውስጥ በተፈጸሙት የፍቅር ምስጢራዊ ተግባራት ውስጥ ክርስቲያኖች ሁላችን ራሳችንን በማስገባት በታላቅ መንፈሳዊነት በንስሐ፣ በጾም እና እንዲሁም በጸሎት እንድንተጋ ያስፈልጋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ዘወትር ረዕቡ እለት በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ወይም ደግሞ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። የእዚሁ መርሃ ግብር አንዱ አካል በሆነው በዛሬው እለት ማለትም በመጋቢት 19/2010 ዓ.ም. ያደርጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማሕበረሰቦች ዘንድ በአሁኑ ወቅት የሕማማት ሣምንት በታላቅ መነፈሳዊነት እያከበሩ እንደ ሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ያደርጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ኢየሱስ በእዚህ ምድር በነበረው ቆይታ ላይ የገጠመውን መከራ፣ ሞት እና ከእዚያም መቀበሩን እና ከሙታን መነሳቱን በምያመልክቱ ሦስት ቀናት ማለትም ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻ እራት የበላበት የእለተ ሐሙስ ምሽት፣ በመስቀል ላይ የተቸነከረበት የስቅለተ ዐርብ እለት እና ከሙታን የተነሳበት የእለተ ሰንበት እለት በእነዚህ ቀናት ውስጥ በኢየሱስ ላይ የተፈጸሙትን ተግባራት በማንሳት ሰፋ ያለ አስተምህሮ ማድረጋቸው ታውቁዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.