2018-03-02 16:50:00

በኢየሩሳሌም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መካነ መቃብር የሚገኝበት ቤተክርስቲያን ክፍት ሆኖ እንዲቆይ መወሰኑ ተገለጸ።


በኢየሩሳሌም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መካነ መቃብር የሚገኝበት ቤተክርስቲያን ክፍት ሆኖ እንዲቆይ መወሰኑ ተገለጸ።

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

በእስራኤል ባለሥልጣናት በኩል የቀረበውን የግብር ክፍያ ሥርዓት በመቃወም ሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የካቶሊክ፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ እና የአርመኒያ ቤተ ክርስቲያን በሕብረት ሆነው፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር የሚገኝበት ቤተ ክርስቲያን እንዲዘጋ ሰኞ ዕለት ውሳኔ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ፊደስ የዜና ተቋም ይፋ ባደረገው ዘገባ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ነታኛሁ፣ ለአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በላኩት መልዕክት፣ መንግሥታቸው ከቤተ ክርስቲያን ተጠሪዎች ጋር በመምከር ለጉዳዩ ምላሽ እንደሚሰጥ መግለጻቸውም ይታወሳል። የክልሎች ሕብረት ሚኒስትር በሆኑት በዛኪ ሃነግቢ የሚመራ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው ነበር። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በወጣው ትዕዛዝ መሠረት፣ የኢየሩስሌም ማዘጋጃ ቤት፣ በአብያተ ክርስቲያናት እጅ በሚገኙ ንብረቶች ላይ የተጣለው አዲስ የግብር ሥርዓት ለጊዜው ተግባር እንዳይሆን መደረጉ ታውቋል።

የሚኒስትር ሃነግቢ ምክር ቤት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የወጣውን ትዕዛዝ በመጥቀስ      እንዳስታወቀው፣ ባለፉት ጊዜያት ለ99 ዓመታት ውል ተፈርሞባቸው ሲከራዩ በቆዩት በርካታ የአብያተ ክርስቲያናት ንብረቶች ጉዳይ በዝርዝር እንደሚመለከትና፣ አብያተ ክርስቲያናትም ያለባቸውን ዕዳ መክፈል እንዲያስችላቸው በማለት በሽያጭ ያዛወሯቸውንም ንብረቶች እንድሚመለከት ገልጿል። የእስራኤል ፓርላማ፣ ንብረትነታቸው የአቢያተ ክርስቲያናት የሆኑ ቦታዎችንና ንብረቶችን በውርስ መልክ ለእስራኤል መንግሥት ማዛወር የሚያስችሉ ሕጎችን ለማውጣት ጥናት ሲያደርግ መቆየቱ ታውቋል። አሁን በእስራኤል መንግስት እና በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚነሱ ማንኛውም አወዛጋቢ ጉዳዮች በሕግ እንደሚታገዱ ታውቋል። ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንዳስገነዘበው፣ እስራኤል፣ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ የክርስትና እምነት ተከታዮችና የሌሎች እምነቶች ተከታዮችም፣ እምነታቸውን ለመግለጽ ሙሉ ነፃነት ያለባት ብቸኛዋ ሀገር በመሆኗ ኩራት ይሰማናል ብሏል።

በኢየሩሳሌም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር የሚገኝበትን ቤተ ክርስቲያን የሚያስተዳድሩ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፣ ሰኞ ዕለት ከሰዓት በኋላ፣ በጋራ ሆነው ባወጡት መልዕክታቸው፣ የእስራኤል መንግሥት ለወሰደው መልካም እርምጃ እግዚአብሔርን አመስግነው፣ በእየሩሳሌም ከተማ፣ ቅዱስ ስፍራዎች ለዘመናት ሳይዘጉ እንዲቆዩ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉትንም ሁሉ አመስግነው፣ ኢየሩሳሌም የተለያዩ ሐይማኖቶች በመከባበር አብረው የኖሩባት ቅድስት ከተማ መሆኗንንም አስገንዝበዋል።

በኢየሩሳሌም ከተማ የሚገኙ ቅዱስ ስፍራዎች ክፍት ሆነው እንዲቆዩ በማለት የእስራኤል መንግሥት የወሰደው አቋም ትክክልና ተገቢ እንደሆነ፣ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ጉዳይ አጥኚ የሆኑት፣ ጋዜጠኛ ጆርጆ በርናርደሊ ገልጸዋል። ጋዜጠኛው በማከልም፣ ውሳኔው፣ በእስራኤል መንግሥትና በእስራኤል አገር በሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ሰላማዊ አቅጣጫ እንዲመለስ ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሯል ብለዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.