2018-02-19 16:38:00

ለ15ኛው ጳጳሳት ሲኖዶስ በሚቀርቡ የመወያያ ሃሳቦች ላይ ወጣቶች ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ።


ለ15ኛው ጳጳሳት ሲኖዶስ በሚቀርቡ የመወያያ ሃሳቦች ላይ ወጣቶች ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ።

በጥቅምት ወር 2011 ዓ. ም. በወጣቶች ጉዳይ ላይ በስፋት የሚመክር የጳጳሳት ሲኖዶስ በሮም እንደሚካሄድ ይታወቃል። በዚህ የጳጳሳት ሲኖዶስ ወቅት የሚቀርቡ ሐሳቦችን እና አስተያየቶችን ለማሰባሰብ እንዲያመች ተብሎ ከመጋቢት 10 ቀን እስከ መጋቢት 15 ቀን 2010 ዓ. ም. በሮም አንድ ስብሰባ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

ከዓለም ዙሪያ የተወጣጡ 300 ወጣቶች የሚካፈሉበትን ስብሰባ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተው እንደሚከፍቱት ይጠበቃል። በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የሚደረገው የጳጳሳት ሲኖዶስ በሦስት አበይት ርዕሶች እነርሱም፣ “ወጣቶች፣ እምነትና፣ ጥሪያቸውን በሚገባ ለይቶ ማወቅ” የሚሉ እንደሆነ ታውቋል። በስብሰባው ወቅትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመገኘት ከአምስቱም አህጉራት የጳጳሳት ጉባኤዎችን ከሚወክሉ ወጣቶች፣ ከተለያዩ መንፈሳዊና ማሕበርዊ እንቅስቃሴዎች አባላት፣ ከገዳማዊያንና ገዳማዊያት፣ ከተለያዩ የሐይማኖት ተወካዮች፣ ከማረሚያ ቤቶች እና በጎጂ ሱስ ከተጠቁ ወጣቶች ለሚቀርቡት ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጡበት ይጠበቃል።

በመጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ. ም. በስብሰባው ላይ በአካል ተገኝተው ከሚሳተፉ 300 ወጣቶች በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወጣቶችም በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ Synod2018 የሚለውን የጳጳሳት ሲኖዶስ ድረ ገጽና ማሕበራዊ ሚዲያን በመጠቀም፣ እርስ በርስ በመወያየት ሃስብ ማካፈል እንደሚቻል የጳጳሳት ሲኖዶስ አስተባባሪ ይሆኑት ፊሊፖ ፓሳንቲኒ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

የጳጳሳት ሲኖዶስ አስተባባሪ የሆኑት ፊሊፖ ፓሳንቲኒ እንደገለጹት፣ ማሕበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የወጣቶችን ጥያቄዎች፣ ምስክርነቶችንና በዛሬው ዓለም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማሰባሰብ ተደማጭነት እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል ብለዋል። ፊሊፖ ፓሳንቲኒ በማከልም ወጣቶች ድምጻቸው ተደማጭነትን አግኝቶ በሕይወታቸው የተስፋ ምልክቶች የሚታዩበትን መንገዶች ማመቻቸት ይቻላል ብለዋል።

የማሕበራዊ ሚዲያዎች መልካም ጎኑን የጠቆሙት፣ በቡሩንዲ የፎኮላሪ እንቅስቃሴ አባል የሆኑት ስቴላ ማሪሌነ ኒሺሙዌ እንደገለጹት በአገራቸው በርካታ ወጣቶች የፎኮላሪ እንቅስቃሴ አባል እንደሆኑ አስረድተው፣ በማሕበራዊ ሚዲያ በኩል ቤተ ክርስቲያን ለወጣቶች የምታስተላልፈው መልዕክት ፈጣንና እጅግ ጠቃሚ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸው እንደዚሁም ወጣቶችም ሐሳባቸውን፣ ጥያቄዎቻቸውንና አስተያየቶቻቸውን ለመግለጽ ወይም ለማሰማት ጥሩ አጋጣሚ እንደተፈጠረላቸው አስረድተዋል። ከዚህ በፊት በማሕበራዊ ሚዲያዎች የቀረቡትን ጥያቄዎች በመመለስ 221,000 ወጣቶች መሳተፋቸውንና  ከእነዚህም መካከል 56 በመቶ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ከአውሮፓ እንደነበሩ የ15ኛው ጳጳሳት ሲኖዶስ አስተባባሪና ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሎረንሶ ባልዲሰሪ ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሎረንሶ ባልዲሰሪ እንደገለጹት፣ ከመጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ ም ጀምሮ በሮም የሚካሄደው የወጣቶች ስብሰባ ከዚህ በፊት በየአገሮች ወይም በጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አባል አገሮች የተካሄዱት ስብሰባዎች ተከታታይ እንደሚሆን አስረድተው፣ ባለፈው ዓመት በአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤ ምክር ቤት ተመሳሳይ የወጣቶች ስብሰባ ተካሂዶ እንደነበር፣ እንደዚሁም ዘንድሮ በጥር ወር ላይ በሰነጋል ዋና ከተማ በዳካር በተደረገው ስብሰባ ላይ ከክርስትናና ከእስልምና እምነቶች የተወጣጡ ወጣቶች ተካፍለው እንደነበር አስታውሰዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.