2018-02-14 16:23:00

19ኛው የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች ስብሰባ በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ እንደሚካሄድ ታወቀ።


 

19ኛው የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች ስብሰባ በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ እንደሚካሄድ ታወቀ።

የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች ስብሰባ ከሐምሌ 6 እስከ 16 ቀን 2010 ዓ ም ድረስ አዲስ አበባ ላይ እንደሚካሄድ ታውቋል። አባል አገሮች ዘጠኝ ሲሆኑ እነርሱም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ማላዊ ሲሆኑ ተባባሪ አባል አገሮችም ጂቡቲ እና ሶማሊያ መሆናቸው ታውቋል።

ዋና ጽሕፈት ቤቱን ናይሮቢ ኬንያ ያደረገው የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት ጠቅላላ ስብሰባውን በየአራት ዓመት የሚያደርግ ሲሆን ያለፈውን ጉባኤ በማላዊ፣ ሊሎንጉዌ ማካሄዱ የሚታወቅ ነው። በዚህም ወቅት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት የሆኑትን ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል የሕብረቱ ዋና ሊቀ መንበር አድርጎ በመሰየም  ቀጣዩን ጠቅላላ ጉባኤ በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ላይ እንደሚያካሄድ ወስኖ መለያየቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የምሥራቅ አፍሪቃ ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት ጉባኤ ሲያዘጋጅ የመጀመሪያው ሲሆን የመክፈቻው ዕለት መስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት በሚሌኒየም አዳራሽ ከተፈጸመ በኋላ የአስር ቀን ስብሰባውን በአፍሪቃ ሕብረት ኤኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚያከናወን ታውቋል።

ዘንድሮ የሚካሄደው የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች ቀዳሚ ዓላማ፣ በአንድ አገር ውስጥ የሚታየው የባሕል፣ የቋንቋ የእምነት ብዝሃነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ መሆኑን በመረዳት፣ ይህ ብዝሃነትም በሕዝቦች መካከል የመከባበርንና የበለጠ መተዋወቅን፣ በሰላምና በፍቅር አብሮ የመኖርን ባሕል የሚያሳድግ እንጂ ጥላቻንና ጸብን የሚቀሰቅስ መሆን እንደሌለበት መልዕክት ለማስተላለፍ የታለመ ነው ተብሏል።

በስብሰባው ወቅት ብዙ ምሁራን የሚሳተፉበት ሲሆን በተጨማሪም በምሥራቅ አፍሪቃ በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጉዳዮች ዙሪያ ጳጳሳቱ ስፋ ያሉ ውይይቶች እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በመጀመሪያው ቀን ስብሰባ ከምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን የተወጣጡ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያንና ገዳማዊያት፣ የምዕመናንና የወጣት ማሕበራት ተወካዮች የሚካፈሉ ሲሆን ቅድስት መንበርን ጨምሮ ከዓለም ዙሪያ የተጋበዙ በአጠቃላይ ከ300 በላይ ተሳትፊዎች እንደሚገኙ ታውቋል።    

 








All the contents on this site are copyrighted ©.