2018-02-05 16:17:00

በሮም በሚገኘው የላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል መዘጋጀቱ ታወቀ።


ሮም በሚገኘው የላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ  ዓለም አቀፍ የውጣቶች ፌስቲቫል እንደሚካሄድ የዩኒቨርሲቲው አስተዳዳሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኤንሪኮ ዳል ኮቮሎ አስታወቁ።

የወጣቶች ቤተክርስቲያን በሚል ርዕስ ከየካቲት 30 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ ም ድረስ በወጣቶች ሐዋርያዊ አስተዳደር ዙሪያ የሚነጋገር ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል በሮም የላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንደሚካሄድ ታውቋል። ይህ የወጣቶች ፌስቲቫል፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጽኑ ፍላጎት በበጭው ጥቅምት ወር 2011 ዓ ም በወጣቶች ጉዳይ ላይ ለሚወያይ የጳጳሳት ሲኖዶስ ሰፊ አስተዋጽኦን ሊያበረክት ይችላል ተብሏል። ፌስቲቫሉ በሮም የሚገኘው የላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ከፐንሲልቫኒያው ቪላኖቫ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን በጋራ ያዘጋጁት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

በሮም የላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኤንሪኮ ዳል ኮቮሎ እንደገለጹት በወጣቶች ሁለንተናዊ እድገትን ላይ የሚወያይ የጳጳሳት ሲኖዶስ በዩኒቨርሲቲው ዓለም ለሚገኙ ወጣቶችም በጣም አስፈላጊ እንደሚሆን አስረድተዋል። አቡነ ኤንሪኮ ዳል ኮቮሎ እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ዩኒቨርሲቲ ወስጥ ከመላው ዓለም የመጡ ተማሪዎች እንደሚገኙ ጠቅሰው ይህም የተለያዩ ባሕሎችን ያማከለ፣ የወጣቶችን እምነትና ጥሪያቸውን በጥልቀት የሚመለከት ገንቢ ውይይት እንደሚካሄድ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በማከልም የወጣቶችን የእምነት አካሄድ በተመለከተ በአውሮፓ፣ በአፍሪቃና በእስያ ወጣቶች መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ አስረድተዋል። በዩሮ-አትላንቲክ አካባቢ የወጣት እምነት ተጨባጭ በሆኑት የተለያዩ ፍልስፍናዎች የተበረዘ ነው ብለዋል። ያም ሆኖ መልካም ዓለም የሚመሰረተው ለውጥን በሚሹ ጽኑ ፍላጎት ባላቸው በወጣቶች እንደሆነ በሮም የላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኤንሪኮ ዳል ኮቮሎ አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ካዘጋጀው ፌስቲቫል ምን ይጠበቃል ያሉት አቡነ ዳል ኮቮሎ፣ በርሳቸው አስተያየት፣ ቤተ ክርስቲያን በውጣቶች መንፈሳዊና ማሕበራዊ ሕይወት ዙሪያ ስትከተል ለቆየችው መንገድ ተጨማሪ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ ለአዲሱ ትውልድ በሚስማማ መልኩ አቅጣጫን ለመቀየስ ይረዳል ብለዋል። የትኛውን የቤተክርስቲያን የአካሄድ ዜይቤን ወጣቶች ይፈልጋሉ የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄን ለመመለስ የሚያስችል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሃሳብ በመጥቀስ የሚከተለውን ብለዋል። የተሻለ ዓለም የሚገነባው፣ ለወጣቶች ምስጋና ይግባቸውና፣ ወጣቶች ለለውጥ ካላቸው ፍላጎት ተነሳስተው በሚያበረክቱት የሃሳብና የተግባር አስተዋጽኦ ነው ብለዋል።

በሮም በሚገኘው የላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ፣ የዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተዳደር ጥናት ዘርፍ ዳይረክተ የሆኑት ፕሮፈሰር ጁሊዮ ካፕሪ እንደገለጹት ፌስቲቫሉ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ምሁራንን፣ ባሕላቸውንም የሚያሳትፍ በመሆኑ ውጤታማ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የዘንድሮ ፌስቲቫል ካለፉት በተለየ መልኩ ሽልማት የሚያስገኙ ውድድሮች ሳላሉ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያናቸው ወይም ቁምስናቸው የሚገኝበትን ሁኔታ በማጤን በሥራ ቢተረጉሙ ጥሩ ይሆናሉ የሚሏቸውን ሃሳቦች የሚያቀርቡበት ይሆናል ብለዋል።

የወጣቶች ፌስቲቫል እንደመሆኑ የውጣቶችን ሃሳብ ለመረዳት፣ የልባቸውን መሻት በመረዳት ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለመላው ሕብረተሰብ ማበርከት የሚችሉትንና ሕብረተሰቡ ለእነርሱ ሊያበረክት የሚችለውን በትክክል ለመረዳት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ፕሮፈሰር ጁሊዮ ካፕሪ አስረድተዋል። በማከልም የዚህ ፌስቲቫል ዋና ጠቀሜታው ሐዋርያዊ አገልግሎትን ፍሬያማ ለማድረግ የሚረዱ ሃሳቦች የሚቀርቡበት፣ ወጣቶችን የምናዳምጥበት፣ ቤተክርስቲያንም ወደፊት ለወጣቶች በሚበጅ ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ እንድታስብበት የሚጋብዝ በመሆኑ አስፈላጊ ፌስቲቫል ነው ብለዋል።                          








All the contents on this site are copyrighted ©.