2018-01-27 17:37:00

ጥር 20/2010 ዓ.ም. አስተርዬ ሁለተኛ እለተ ሰንበት ንባባት እና አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ


ጥር 20/2010 ዓ.ም. ዘጥምቀት ወይንም አስተርዬ ሁለተኛ እለተ ሰንበት ንባባት እና አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

የእለቱ ምንባባት

2ቆሮ.1፡13-24

ልታነቡት ወይም ልትረዱት የማትችሉትን ነገር አንጽፍላችሁም፤ ሁሉንም እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ። እናንተ በእኛ እንደምትመኩ ሁሉ እኛም በእናንተ እንደምንመካ አሁን የተረዳችሁን በከፊል ቢሆንም፣ በጌታ ኢየሱስ ቀን ሁሉን ትረዳላችሁ። በዚህ ርግጠኛ ስለ ነበርሁ በዕጥፍ እንድትጠቀሙ፣ በመጀመሪያ ልጐበኛችሁ ዐቅጄ ነበር። ወደ መቄዶንያ ስሄድ እግረ መንገዴን ልጐበኛችሁና ከመቄዶንያም በእናንተ በኩል ተመልሼ ወደ ይሁዳ ስሄድ በጒዞዬ እንድትረዱኝ ዐቅጄ ነበር። ይህን ሳቅድ በሚገባ ሳላስብ ያደረግሁት ይመስላችኋልን? ወይስ በዓለማዊ ልማድ አንዴ፣ “አዎን፣ አዎን” ወዲያው ደግሞ፣ “አይደለም፣ አይደለም” የምል ይመስላችኋልን? እግዚአብሔር ታማኝ እንደሆነ ሁሉ፣ ለእናንተ የምንናገረው ቃላችን፣ “አዎን” እና “አይደለም” ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም እኔም ሆንሁ ሲላስናጢሞቴዎስ፣ እኛ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “አዎን” እና “አይደለም” አልነበረም፤ ነገር ግን በእርሱ ዘወትር፣ “አዎን” ነው። በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በእርሱ ነውና፤ እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ “አሜን” የምንለው በዚህ ምክንያት ነው። እንግዲህ፣ እኛንም እናንተንም በክርስቶስ ጸንተን እንድንቆም የሚያደርገን እግዚአብሔር ነው፤ የቀባንም እርሱ ነው፤ የእርሱ ለመሆናችን ማኅተሙን ያተመብን ደግሞም ወደ ፊት ለምናገኘው ነገር የመንፈሱን ዋስትና በልባችን ያኖረ እርሱ ነው።ወደ ቆሮንቶስ ተመልሼ ያልመጣሁት እንዳላሳዝናችሁ ብዬ ነው፤ ይህ እውነት ካልሆነ እግዚአብሔር ይመስክርብኝ። ጸንታችሁ የምትቆሙት በእምነት ስለ ሆነ፣ ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁ ላይ ለመሠልጠን አይደለም።

1ዬሐ.222-29

ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማነው? ይህ አብንና ወልድን የሚክደው የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ የለውም፤ ወልድን የሚያምን ሁሉ አብም አለው። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ይኑር፤ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ቢኖር፣ እናንተም በወልድና በአብ ትኖራላችሁ። ይህ እርሱ የሰጠን ተስፋ የዘላለም ሕይወት ነው። ስለሚያስቷችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ። እናንተ ግን ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በውስጣችሁ ይኖራልና፤ ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ነገር ግን እውነት እንጂ ሐሰት ያልሆነው የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉም ነገር እንደሚያስተምራችሁ፣ ያም እውነት እንጂ ሐሰት እንዳልሆነ፣ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በእርሱ ኑሩ።እንግዲህ ልጆች ሆይ፤ እርሱ ሲገለጥ ድፍረት እንዲኖረን፣ በሚመጣበትም ጊዜ በፊቱ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ። እርሱ ጻድቅ መሆኑን ካወቃችሁ፣ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ታውቃላችሁ።

.ሥራ. 1320-27

ይህም ሁሉ የተፈጸመው በአራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ ነበር።“ከዚህ በኋላ፣ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው። ከዚያም ሕዝቡ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለመኑት፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን፣ የቂስን ልጅ ሳኦልን ሰጣቸው፤ እርሱም አርባ ዓመት ገዛቸው። ሳኦልንም ከሻረው በኋላ፣ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ ስለ እርሱም፣ ‘እንደ ልቤ የሆነና እኔ የምሻውን ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ሲል መሰከረለት።

እግዚአብሔርም በገባው ቃል መሠረት ከዚህ ሰው ዘር አዳኝ የሆነውን ኢየሱስን ለእስራኤል አመጣ። ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት፣ ዮሐንስ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ንስሓ ገብተው እንዲጠመቁ ሰብኮላቸው ነበር። ዮሐንስ ተልእኮውን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ፣ ‘እኔ ማን መሰልኋችሁ? እኔ እኮ እርሱ አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግሩን ጫማ እንኳ መፍታት የማይገባ ከእኔ በኋላ ይመጣል’ ይል ነበር።“እናንት ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞች፤ ደግሞም በመካከላችሁ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፤ ይህ የድነት መልእክት የተላከው ለሁላችንም ነው። የኢየሩሳሌም ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስን አላወቁትም፤ ይሁን እንጂ በየሰንበቱ የሚነበበው የነቢያት ቃል እንዲፈጸም በእርሱ ፈረዱበት።

ሉቃ 245-52

ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር። ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።

እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። እነርሱ ግን የተናገራቸው ነገር አልገባቸውም። ከዚያም አብሮአቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር። ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።

 

ጥር 20/2010 ዓ.ም. ዘጥምቀት ወይንም አስተርዬ ሁለተኛ እለተ ሰንበት ንባባት እና አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ  ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘጥምቀት ወይንም አስተርዬ ሁለተኛ የሚለውን ሰንበት እናከብራለን፡፡

በዚህም ዕለት ዛሬ በተነበቡት ንባባት አማካኝነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረን የሚያስታውሰን ነገር አለ፡፡  ይኸውም በመጀመሪያን ንባብ ላይ እንዳደመጥነው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲላስና ጢሞቴዎስ በቆሮንጦስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል እየሰበኩ በኖሩበት ጊዜ በቅድስናና በቅንነት እንደኖሩ ይናገራል፡፡

ይህንን የቅድስናና የቅንነት ኑሮ ለመኖር የቻሉትም ከእግዚአብሔር ባገኙት ጸጋ ነው፡፡  በ1ቆሮ 15፡10 ላይ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ራሱ ሲመሰክር እንዲህ ይለል፡፡ “ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለው ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም እንደውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሰርቻለሁ ዳሩ ግን ይህ ሁሉ የሆነው ከእኔ ጋር ባለው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው” ይላል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ በቆሮንጦስ ወንጌልን እየሰበከ ሲመላለስ በቅድስናና በቅንነት እንደኖርኩ ከሁሉ በላይ ኀሊናዬ ይመሰክርልኛል ይላል፡፡  እኛም ሁላችን በቅድስናና በቅነነት የምንመላለስ ከሆነ የመጀመሪያ ምሥክርነት ሰጪ ሕሊናችን ነች፡፡  ሕሊና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ክፉና ደጉን እንዲለይ በውስጡ ያስቀመጠለት እውነተኛ ዳኛ ነች፡፡

ሕሊናችን በቅንነት እንድትመራ ደግሞ የግድ የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲያግዛት ያስፈልጋል፡፡  ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስም እንደሚመሰክረው እርሱም በቅን ሕሊናና በቅድስና መመላለስ የቻለው በዚሁ እግዚአብሔር በሚሰጠው ጸጋ ብቻ ነው፡፡ ሰው ሁል ጊዜ በኃጢአት ውስጥ የሚመላለስ ከሆነ ከእግዚአብሔር ጸጋ እርቆ እንደሚኖር ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡  ይህ የእግዚአብሔር ጸጋ በሕሊናው ውስጥ የማይመላለስ ከሆነ በምንም ዓይነት የቅንነትና የቅድስናን ጉዞ መጓዝ አይችልም፡፡

እግዚአብሔር ጸሎታችንን ልመናችንን የሚሰማው በቅንነትና በቅድስና ለመኖር ብርቱ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው፡፡  ዘወትር በኃጢያት ጐዳና የምንመላለስ ከሆንን እግዘአብሔር እንዴት ጸሎታችንን ሊሰማን ይችላል?  መዝ.66፡18 እንዲህ ይላል “ኃጢአትን በልቤ አስተናግጄ ቢሆን ኖሮ ጌታ ባልሰማኝ ነበር ይላል፡፡”

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር ሁላችንንም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፀንተን እንድንቆም በመንፈሱ የቀባንና ያተመን እግዚአብሔር ራሱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር እያንዳዳችን ዘወትር በእርሱ መንፈስና እርሱ በሚሰጠን ጸጋ መልካም ነገር ሁሉ እየሰራን እንድንኖር ይፈልጋል ለዚህም ነው ዘወትር በአጠገባችን ሆኖ የሚያስፈልገንን ጸጋና በረከት የሚያፈስልን፡፡  ከዚህ ከሚፈሰው ጸጋና በረከት መቋደስ ደግሞ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው፡፡ እግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ የምንመላለስ ከሆነ በእርግጠኝነት የዘለዓለም ሕይወት ወራሽ መሆናችንን እናስመሰክራለን፡፡  ሁለተኛው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ዩሐንስ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው የጸጋ ቅባት ሁልጊዜ እውነትን ብቻ እንድንመሰክር ያስተምረናል፡፡

እግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ የማንመላለስ ከሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅ አንችልም ወደ እግዚአብሔር የሚመራንን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ካላወቅን ደግሞ እግዚአብሔርን ለማወቅ አንችልም የዬሐንስ ወንጌል 14፡6 ላይ አንዲህ ይላል, “መንገዱ እኔ ነኘ እውነትና ሕይወትም እኔ ነኝ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ይላል፡፡

አንድ ሰው በእግዚአብሔር ጸጋ ውስጥ የሚመላለስ ከሆነ ምንም ሰው አያሳስተውም ምክንያቱም በውስጡ ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ በሕሊናው አማካኝነት እውነትንና የቅድስናን መንገድ ስለሚገልፅለት ነው፡፡  እግዚአብሔር በሰጠን ንጹህ ሕሊና የምንኖር ከሆነ በአብ እንዲሁም በወልድ ውስጥ እንኖራለን ማለት ነው፡፡  በአብና በወልድ ውስጥ የምንኖር ከሆነ ደግሞ በዩሐንስ ወንጌል 4፡14 እንደሚለው ምንጩ ከማይደርቀው የሕይወት ውኃ እንጠጣለንና በእርግጠኘነት መንገዳችን የተቃና የዘለዓለም ሕይወትም ወራሾች እንሆናለን፡፡

በአብና በወልድ ውስጥ የማንኖር ከሆነ ደግሞ ዘወትር ሐሰትን በመናገርና ለቅድስና ጉዞ የማይመቹ ነገሮችን እናደርጋለን፡፡  ይህ ደግሞ በዩሐ. ወንጌል 15፡6 ጀምሮ  እንደተጠቀሰው እንደማይጠቅም ቅርንጫፍ ተቆርጠን እንጣላለን መጨረሻችንም በእሳት ውስጥ ተጥሎ መቃጠል ይሆናል፡፡

ለዚህ ነው ቅዱስ ሐዋርያው ዩሐንስ የእግዚአብሔርን ቃል በውስጣችን ይዘን፣ የመንፈስ ቀዱስ ቅባት የሚሰጠንን ብርታትን ይዘን ፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኑር እያለ ምክሩን የሚለግሰን፡፡

በዛሬው በሉቃስ ወንጌል ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 12 ዓመት በሞላው ጊዜ የፋሲካን በዓል ለማክበር ከወለጆቹ ጋር ወደ እየሩሳሌም እንደሄደ ይናገራል፡፡  በኃላ ግን ወላጆቹ ከሌሎች ዘመዶቻቸው ጋር መስሏቸው ነበር፡፡  በስተመጨረሻም ከእነርሱ ዘንድ ሲያጡት እየፈለጉት ወደ እየሩሳሌም እንደተመለሱ ይናገራል፡፡  ከ ሶስት ቀን ፍላጋም በኋላ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመምሕራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጦቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው አገኙት፡፡

ይህ የሚያስረዳን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሆኖ የእግዚአብሔርን ልጅና ለተለየ ዓላማ ወደ ምድር የመጣ ነቢይ መሆኑ ይረዳ ነበር፡፡  ለዚህም ነው ለ3 ቀናት ያህል ከቤተ መቅደስ ሳይወጣ አባቱ ቤት የቆየው፡፡  ነገር ግን ወደ ምድር የመጣበት ዓላማ ገና ጊዜው አልደረሰምና እስኪደርስ ወደ ናዝሬት ተመልሶ አባቱንና እናቱን እያገዘ በጥበበና በቁመት በሞገስም በእግዚአበሔርና በሰው ፊት አደገ፡፡

ይህ የሚያስተምረን ሁላችን እግዚአብሔርን በሚሰጠን ጸጋ በመታገዝ ዘወትር በጥበብም በመንፈሳዊነትም እንድናድግ ነው፡፡  ምክንያቱም ከእግዚአበሔር የምናገኘው ጥበብ ከእግዚአብሄር የምናገኘው መንፈሳዊነት በዕለታዊ ኑሮአችን በመንፈሳዊ አካሄዳችን እንደ እርሱ ፈቃድ እንድንመላለስ ትልቅ እገዛ ስለሚያደርስልን ነው፡፡  በትኛውም መንገድ ማድረግ ያለብን ከእርሱ በሚመጣ ጸጋ አማካኝነት በምናገኘው ኃይል በትኛውም መንገድ መናገር ያለብን ከእርሱ በሚመጣ ጸጋ አማካኝነት በምናገኘው ኃይል  ብቻ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡  ይህንንም ለማድረግ እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን፡፡








All the contents on this site are copyrighted ©.