2018-01-19 16:52:00

ር. ሊ. ጳ. ፍራንቸስኮ በፔሩ የሚያደርጉትን 22ኛ ሐዋሪያዊ ጉብኝት በይፋ ጀመሩ


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮ ከጥር 7-10/2010 ዓ.ም. በቺሊ ያደረጉትን 22ኛውን ሐዋሪያዊ ጉብኝት በትላንትናው እለት አጠናቀው የ22ኛው ሐዋሪያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ መዳረሻ ወደ ሆነችው ፔሩ ማቅናታቸው የታወቀ ሲሆን በትላንትናው እለት እኩለ ሌሊት ላይ የፔሩ ዋና ከተማ በሆነቺ በሊማ በሚገኘው ዓለማቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ መድረሳቸው ታውቁዋል። 

ቅዱስነታቸው በሊማ ዓለማቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በደረሱበት ወቅት የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር በሆኑት ፐድሮ ፓብሎ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን ሁለት ሕጻናት የአበባ ጉንጉን አቅርበውላቸዋል። የተለያዩ ባለስልጣናት እና በሀገሪቷ የሚገኙ ብጹዕን ጳጳሳትም በስፍራው ተገኝተው የአቀባበል ስነ-ስረዓት አድርገውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በፔሩ በሚያደርጉት ቆይታ ከሀገሪቷ ባለስልጣናት፣ ከሃይማኖት መሪዎች እና እንዲሁም በእዚያው በፔሩ በሚያሳርጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የሚያደርጉት ስብከት እና ንግግሮች ይዘት ከአሁኑ ብዙዎች በጉጉት የሚጠባበቁት ክስተት እንደ ሆነ የታወቀ ሲሆን ምክንያቱም በፔሩ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ ችግሮች፣ ሙስና፣ እንዲሁም በተለይም በአማዞን ደን አከባቢ የሚኖሩ የአማዞን ቀደምት ሕዝቦች ላይ የሚደርሰውን ኢፍታዊ ተግባር፣ በአማዞን ደን ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ሐብት የአከባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ ያላደረገ፣ ይባስ ብሎም ለዘመናት የተፈጥሮን ሂደት በተከተለ መልኩ ከሚኖሩት ስፍራ እየተፈናቀሉ ለክፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን፣ ይህንን እና ይህንን የመሳሰሉ የሀገሪቷን ችግሮችን ከግምት ያስገባ ንግግር ቅዱስነታቸው እንደ ሚያደርጉ ይጠበቃል።

ቅዱስነታቸው በፔሩ በሚያደርጉት የሦስት ቀን ጉብኝት ከፍተኛ ተኩረት የተሰጠው በዛሬው እለት ምሽት በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር 1.30 ላይ በአማዞን ጥቅጥቅ ደን ዳርቻ ላይ ከሚኖሩ የአማዞን ሕዝቦች ጋር የሚያደርጉት ቆይታ እና ንግግር ከአሁኑ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ የዓለማችን ስነ-ምዕዳር ተጠብቆ ይሔድ ዘንድ የራሱን ከፍተኛ አስተዋጾ በማድረግ ላይ በሚገኘው የአማዞን ጥቅጥቅ ደን ላይ በአሁኑ ወቅት እየተፈጸመ የሚገኘው ከፍተኛ ጭፍጨፋ በማንሳት ለዓለም ድምጻቸውን እንደ ሚያስተጋቡ ይጠበቃል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ  አሁን በፔሩ እያደርጉት የሚገኘው 22ኛው ሐዋሪያዊ ጉብኝት በፔሩ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተደረገ ሦስተኛው ሐዋሪያዊ ጉብኝት ሲሆን ከእዚህ ቀደም 1985 እና 1988 በቅደም ተከተል በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት በዩሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ከተደረገው ሐዋሪያዊ ጉብኝት በመቀጠል ይህ አሁን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በፔሩ እያደረጉት የሚገኘዋ ሐዋሪያዊ ጉብኝት በአንድ የካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በፔሩ የተደረገ ሦስተኛው ሐዋሪያዊ ጉብኝት ነው።

የአማዞን ጥቅጥቅ ደን በቀጠናው የሚገኙ አራት ሀገራት ማለትም ብራዚልን፣ በፔንን፣ ኮሎንቢያን እና ቦሊቪያን የሚያውስን ደን መሆኑ የምታወቅ ሲሆን  ቅዱስነታቸው ከሰዓታት በፊት በፔሩ በኩል በሚገኘው የአማዞን ደን ባለበት ስፍራ ላይ በምትገኘው ቡሄርቶ ማልዶናልዶ በምታባል ክፍለ ሀገር በመገኘት በእዚያው ለሚጠብቁዋቸው ከተለያዩ የፔሩ ግዛት የተውጣጡ 4000 ለሚሆኑ የአማዞን ተወላጆች ተወካዮች ጋር እንደ ሚገናኙና በእዚያም ንግግር እንደ ሚያደርጉ ይጠበቃል።

ቅዱስነታቸው በወቅቱ የሚያደርጉት ንግግር እርሳቸው ከእዚህ ቀደም “ላውዳቶ ሲ” (በአማሪኛው ውዳሴ ለአንተ ይሁን) በሚል አርእስት ባሳተሙት እና “የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከመውደሟ በፊት እንታደጋት” የሚል ጳጳሳዊ መልእክት አስተላልፈው እንደ ነበር  የሚታወስ ሲሆን ይህ አሁን ቅዱስነታቸው ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኃላ የሚያደርጉት ንግግር ይህንን ከእዚህ ቀደም “ላውዳቶ ሲ” (ወዳሴ ላንተ ይሁን) በሚል አርእስት ለዓለም ካስተላለፉት መልእክት ጋር በማዛመድ እንደ ሚናጉርም ይጠበቃል።

ይህ አሁን ቅዱስነታቸው በፔሩ በኩል በሚገኘው የአማዞን ደን አከባቢ ከሚኖሩ የየአማዞን ሕዝቦች  የማኅበርሰብ ክፍሎች ጋር የሚያደርጉት ቆይታ ሁለት ዓይነት እንድምታን ለዓለም እንደ ሚያሰማ ተገልጹዋል።

በቅድሚያ ይህ ቅዱስነታቸው በእዚህ አከባቢ የሚያደርጉት ሐዋሪያዊ ጉብኝት በእዚያ አካባቢ የሚኖሩ የአማዞን ሕዝቦች ለብዙ አመታት ያህል ተገለው የኖሩ፣ እንዲሁም በከፍተኛ የድኽነት አረንቋ ስር የሚገኙ፣ በአከባቢያቸው የሚገኘው እና ለብዙ ሺ አመታት ለእነዚህ ለአማዞን ሕዝቦች እና ለዘርማንዘራቸው በመጠለያነት፣ የምግብ ምንጭ በመሆን በአጠቃላይ የሕይወታቸው ሕልውና የሆነው የአማዞን ጥቅጥቅ ደን በሕገወጥ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እየተጨፈጨፈ ለተወሰኑ ሰዎች ክፍተኛ የገንዝብ ማግኛ ምንጭ ቢሆንም እነዚህ የአማዞን ሕዝቦች ግን በከፍተኛ የድኽነት አርቋ ሥር ሰልሚገኙ፣ የመኖር ሕልዋናቸው አደጋ ላይ በመውደቁም ጭምር እና እንዲሁም የአማዞን ደን “የዓለማችን ሳንባ” በመባል የሚታወቅ በመሆኑ የእዚህ ደን አደጋ ላይ መውደቅ የአማዞን ሕዝቦች የመኖር ሕልውናቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የመኖር ያለመኖር ሕልዋናቸው እና ዋስትናቸው በመሆኑ ጭምር አሁን ቅዱስነታቸው በአከባቢው የሚያደርጉት ጉብኝት የእነዚህ ጭቁን ሕዝቦች ችግር ለዓለም ቅልጭ አድርገው በማሳየት እና በማጋለጥ “የጋራ መኖሪያ ቤታችንን እንከባከብ” በማለት መፍትሄ ያስገኛል የሚል እንድምታን በቅድሚያ ያዘለ ነው።

በሁለተኛ ደርጃ ደግሞ ፔሩ በከፍተኛ ድኽነት የሚጎሳቆሉ ሕዝቦች የሚኖሩባት ሀገር በመሆኗ፣ 42 የሚሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሚገኙባት ሀገር ስትሆን ይህንን የሀገሪቷን የድኽነት ሁኔታ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጥልቀት እንድትረዳ እና በእዚህም ላይ ተመስርታ የራሷን አዎንታዊ ድርሻ መጫወት የምትችልበትን መንገድ ቅዱስነታቸው እንደ ሚጠቁሙም ይጠበቃል። ከ85-90% የሚገመት የፔሩ ሕዝብ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በመሆናቸው የተነሳ፣ ለሀገሪቷ የተቀናጀ ሁለንተናዊ እድገት ይመጣ ዘንድ ቤተክርስቲያን እና ሕዝቡ በጋር መስራት እንደ ሚገባቸው፣ እንዲሁም በፔሩ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሙስና ተወግዶ ማህበራዊ ፍትህ ይሰፍን ዘንድ፣ እኩል የሀብት ክፍፍል በመላው ሀገሪቱ ይደረግ ዘንድ ቤተክርስትያኒቷ የበኩሉዋን ማሕበራዊ አስተዋጾ እንድታደርግ መንገድ ያመቻቻሉ ተብሎ በመጠበቁ የተነስ ይህ ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በፔሩ የሚያደርጉት ሐዋሪያዊ ጉብኝት አጉዋጊ እንዲሆን አድርጎታል።








All the contents on this site are copyrighted ©.