2018-01-11 16:08:00

ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፣ በሶርያ የሃይማኖት መሪዎች የእርቅ መንገድ ከፋቾች ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።


ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፣ በሶርያ የሃይማኖት መሪዎች የእርቅ መንገድ ከፋቾች ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።

አመታትን ካስቆጠረው ከከባድ ጦርነት ማግስት፣ በሶርያ ሕዝብ መካከል መተማመንንና እርቅን እንዴት ማምጣት ይቻላል ለሚለው ጥያቄ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ሃሳብ መሠረት ያደረጉት ካርዲናኣል ማርዮ ዘናሪ በመልሳቸው የሶርያን ሕዝብ በማስታረቅ የሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛ አስተዋጾን ማበርከት እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በሶርያ ሕዝብ መካከል ግልጽና እውነትን መሠረት ያደረጉ ውይይቶችን ማካሄድ እና የተሰበረ ልባቸውን መጠገን ቀዳሚ መንገድ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የእዚህን መልእክት ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለው ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ጦርነቱ ባስከተለው ከባድ አደጋ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውን ተቀብሎ ማስተናገድ እና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ያሳሰቡት፣ በሶርያ የቅድስት መንበር ልኡክ ብጹዕ ካራዲናል ማሪዮ ዘናሪ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዲፕሎማቶች ያሰሙትን ንግግር በመጥቀስ፣ የጦርነት አደጋ ባንዣበበባቸው ማለትም ከሰሜን ኮሪያ ጅምሮ እንዲሁም በሌሎችም የዓለማችን ክፍሎች ሰላምን ለማንገስ ጥረት ማድረግ እንድሚያስፈልግ አሳስበው ይህም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምኞት እንደሆነ ገልጸዋል።

ከሁሉ አስቀድሞ በአሰቃቂ ጦርነት የቆሰለው የሶርያ ሕዝብ ልብ መጠገን እንዳለበት አስረድተው፣ በሶርያ እንደ አሌፖ፣ ሆምስ ፣ ራቃ፣ እና ዴር ኤዞር በመሳሰሉ አካባቢዎች ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረው ጦርነት ያደረሰውን ከባድ ጥፋት ጠቅሰው፣ በጦርነቱ ምክንያት ልቡ የቆሰለውን የሶርያ ሕዝብ ማጽናናት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ሶርያ በአንድ ዘመን፣ ሕዝቦች በመፈቃቀር፣ የተለያዩ ሃይማኖቶችም ተቻችለው የኖሩባት አገር እንደነበረች አስታውሰው፣ ዛሬ ግን ያ ሁሉ የለም ብለዋል።    

በሶርያ ላይ የሚደርስ ጥቃት አሁንም እንዳልበረደ የተናገሩት ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፣ የእስራኤል ወታደሮች በደማስቆ የሚያደርሱትን ጥቃት እንደቀጠሉበት፣ በሰሜናዊው ምዕራብ ክፍለ ግዛት በሆነችው በኢድሊብ የቦምብ ጥቃቶችን እያደረሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። የጥቃቶቹ ሰልባ የሚሆኑት ሕጻናት እና አቅመ ደካሞች መሆናቸውን ካርዲናል ዘናሪ ተናግረው፣ ሕጻናት በደረሰባቸው ጥቃት በጣም መደንገጣቸውን፣ ወላጆቻቸው ሲገደሉ በዓይን መመልከታቸውንና፣ ጾታዊ ጥቃትም እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የብርሃነ ልደት መልዕክት በማስታወስ በሶርያ ሕዝብ ላይ የወጣውን ቁስል ቶሎ ብለን መጠገን እንጀምር ብለዋል።

ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ በማከልም፣ የሃይማኖት መሪዎች እርቅን ለማውረድ ትልቅ ሚናን መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የሶርያ የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በተለያዩ ወገኖች መካከል መተማመን ሲመጣ እርቅ ሲወርድ ነው ብለዋል። በሶርያ የሚገኙት የተለያዩ የሐይማኖት መሪዎች በሕብረት በመስራት፣ በሕዝቡ መካከል የተፈጠረውን የጥላቻ እና የመለያየት መንፈስ አስወግደው የእርቅን መንገድ የማመቻቸት ግዴታ እንዳለባቸው አስረድተዋል። በአዋሳኝ አገሮች የተጠለሉት የክርስቲያን ማሕበረሰብ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል ያሉት ካርዲናል ዘናሪ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባሰሙት ጥሪ መሠረት በነፍሳት ላይ የወጣውን ጥልቅ ቁስል መጠገን እንጀምር ብለዋል።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.