2018-01-03 16:35:00

ቅድስት መንበር፣ የስደተኞችንና የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ በበላይነት እንድትመራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠየቀ።


ቅድስት መንበር፣ የስደተኞችንና የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ በበላይነት እንድትመራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠየቀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ አመት 2018 ዓ. ም. የጥገኝነት ጠያቂዎችንና የስደተኞችን መብት የሚያስከብሩ ሕጎች በማርቀቅ፣ ከተለያዩ መንግሥታት ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚሠራ ገልጿል። ሂደቱንም በበላይነት እንድትመራ ቅድስት መንበርን ጠይቋል። የመንግሥታቱ ስምምነትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለተከሰቱት ለበርካታ ሰዎች መሰደድ ወይም መፈናቀል መልስ ያገኛል ተብሏል።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ርዕሠ ሊቃነ  ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰኞ ታህሳስ 23 ቀን 2010 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን የሰላም ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ስለ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂ ሰዎች በተመለከተ መናገራቸውና መፍትሄውም ምን መሆን እንዳለበት መጠየቃቸ ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው እንደገለጹት መንግሥታትና ማሕበረሰብ የስደተኞችን ችግር ለማቃለል ጥረት በሚያደርጉበት ባሁኑ ወቅት፣ አመጽን፣ የዘር መድልዎንና ጥላቻን ከማስፋፋት ይልቅ ጠቃሚ እና ጽኑ የሆኑ መፍትሄዎችን ማግኘት ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል።

አባ ሚካኤል ቸርኒ፣ በቅድስት መንበር፣ የሕዝቦች ማሕበራዊ ሁለ ገብ እድገት ጽህፈት ቤት፣ የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ክፍል ምክትል ጸሐፊ በበኩላቸው፣ ዓለም አቀፍ የሰላም ቀንን በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ  ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩት መልዕክት አስፈላጊነት አውስተው፣ የዓለም አቀፍ ትኩረትንም የሳበ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል። አባ ሚካኤል በማከልም፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት፣ ስደተኞች ዕርዳታን የሚሹ ብቻ ሳይሆኑ ለሰላም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ እንደሆነ ያስታውሳል ብለዋል።

አባ ሚካኤል በንግግራቸው፣ መንግሥታት በስደተኞች ጉዳይ ውይይት መጀመራቸውንና ርዕሠ ሊቃነ  ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከተለያዩት ከፍተኛ የመንግሥታት ዲፕሎማቶች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል። ከውይይታቸው ለመረዳት እንደተቻለው ቅድስት መንበር ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትኩረት መስጠቷ ዓለም አቀፍ አድናቆትን ያስገኘ እንደሆነ ገልጸዋል።

በኒው ዮርክ የቅድስት መንበር ተወካይ፣ ከመንግሥታት ጋር የሚደረጉ ጉባኤዎችን በንቃት እንደሚሳተፍና ከሁሉም በላይ የተባበሩት መንግሥታት ቅድስት መንበርን የስደተኞችንና የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ በበላይነት እንድትመራ መጠየቁ የሚያስደንቅና ትልቅ ሃላፊነት የተጣለበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር፣ የሕዝቦች ማሕበራዊ ሁለ ገብ እድገት ጽህፈት ቤት፣ የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች መምሪያ ጽሕፈት ቤት፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚመሩ የስደተኞች ጽሕፈት ቤቶችና የጳጳሳት ጉባኤዎች በመተባበር በተግባር ሊተረጎሙ በሚገቡ 20 ርዕሶች ላይ ውይይት በማድረግ፣ ሐዋርያዊ እቅዶችን በማውጣት ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳቀረቡና በአድናቆት ተቀባይነትን እንዳገኘ ገልጸዋል።

አባ ሚካኤል እንደገለጹት፣ የስደተኞች ጉዳይ በአንዳንድ መንግሥታት ዘንድ እልባት ያላገኘ ቢሆንም፣ ቅድስት መንበር በመንግሥታቱ ውይይት ጣልቃ ሳትገባ እስካሁን ያካበተችውን ልምድ ብቻ በመጠቀም በቀላል ወጪ ገንቢ የሆኑ መፍትሄዎችን ለመንግሥታት ልታቀርብ ትችላለች ብለዋል።

ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አዲስ ሕይወት ማመቻቸት ይቻላል ያሉት አባ ሚካኤል፣ በስደተኞች የግል ጥረት ብቻ የእርሻ ሥራን፣ ንግድንና ቱሪዝምን ማሳደግ እና ይህን ተከትሎ ቤተሰብን በመመስረት ትምህርት ቤቶችን እና ቁምስናዎችን መክፈት ይቻላል ብለው በመጨረሻም፣ በአካባቢው የሚገኙትን ነገሮች ለመጋራት ቅን ፍላጎት ካለ አዲስ ሕይወት ማመቻቸት ይቻላል ብለዋል።         

 








All the contents on this site are copyrighted ©.