2018-01-02 16:22:00

ሰላምን በተስፋ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጠየቁ።


ሰላምን በተስፋ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጠየቁ።

ርዕሠ ሊቃነ  ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰኞ ታህሳስ 23 ቀን 2010 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን የሰላም ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ ሰላምን በተስፋ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳሰበዋል። “ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂ ሰዎች የሰላም ፈላጊዎች ናቸው” ባሉት መልዕክታቸው፣ በዓለማችን ከ250 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች  እንዳሉ፣ ከእነዚህም መካከል 22 ሚሊዮን 500 ሺህ ጥገኝነት ጠያቂዎች እንደሆኑ ተናግረው፣ በሰላም እጦት ምክንያት ስደትና መከራ የሚደርስባቸውን ሰዎች በሙሉ በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል። 

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

አባ ሚካኤል ቸርኒ፣ በቅድስት መንበር፣ የሕዝቦች ማሕበራዊ ሁለ ገብ እድገት ጽህፈት ቤት፣ የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ክፍል ምክትል ጸሐፊ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት መሠረት ባደረገው ንግግራቸው፣ ስደተኞችና ጥገኛነት ጠያቂዎች ሰላምን በማስፈን፣ ሰፊ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ አስታውሰዋል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብሎ በማስተናገድ፣ የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ በማድረግና በማስተዋወቅ፣ ከሚኖሩበት ማሕበረሰ ጋር በመተዋወቅ፣ ኑሮአቸውን በብቃትና በሰላም መምራት የሚችሉበትን መንገዶች ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል።

አባ ሚካኤል በማከልም፣ ስደተኞችን መቀበል ሲባል፣ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ብቸኝነትና መገለል እንዳይሰማቸው፣ እያንዳንዳችን ልባችንን፣ አእምሮአችንንና መኖሪያ ቤቶቻችንም ጭምር በመክፈት በፍቅር ተቀብለን ማስተናገድ ያስፈልጋል ብለዋል። “በምንኖርበት አካባቢ ስደተኛ የለም” ብሎ ማሰብ ትክክል እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ በመልካም አስተሳሰብ፣ አብረው በመኖር ችግራቸንም ሆነ ደስታቸውን መጋራት ወንጌልን በተግባር የመኖር አንዱ መንገድ ነው ብለዋል።

አባ ሚካኤል ንግግራቸውን በመቀጠል በተጀመረው የጎርጎሮሳውያኑ አዲስ አመት 2018 ዓ ም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሁለት አበይት አለም አቀፍ ጉዳዮች በቂ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። እነርሱም ለስደተኞችና ጥገኘት ጠያቂዎች ቋሚ ደንቦችን ማውጣት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ስደተኞችንና ጥገኘት ጠያቂዎችን በተመለከተ ከቅድስት መንበር ለቀረቡት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ድጋፍንና እውቅናን መስጠት የሚሉ ናቸው ብለዋል። በቅድስት መንበር የሕዝቦች ማሕበራዊ እድገት ጽህፈት ቤት፣ የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች መምሪያ ክፍል፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ውስጥ ስደተኞችን ተቅብሎ ማስተናገድ፣ መንከባከብ፣ ማስተዋወቅና ከሕብረተሰቡ ጋር አብረው መኖር እንዲችሉ ማድረግ በሚሉ አራት ርዕሠ ጉዳዮች ውስጥ ለተጠቃለሉ 20 ነጥቦች ከክርስቲያናዊ  ድጋፍ በተጨማሪ ፖለቲካዊ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የስደተኞችን ጉዳይ በተገቢ መልኩ በሥራ ለመተርጎም ሃላፊነት እንዲታከልበትና ክብር መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።   

ካለፈው ተሞክሮአችን በመነሳት፣ ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ፣ መንከባከብ፣ ማስተዋወቅና ከሕብረተሰቡ ጋር አብረው መኖር እንዲችሉ ማድረግ የሚሉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተሻሉና በጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ አመት 2018 ዓ. ም. ጠንክረን የምንሳተፍባቸው ሥራዎቻችን ናቸው ብለዋል።   

 

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.