2017-07-17 11:34:00

የሐምሌ 9/2009 ዓ.ም. እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ።


የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ።

ሳምንቱን ሁሉ ስንወጣ እና ስንወርድ ለሥጋችን እንዲሁም ለነብሳችን  አገልግሎት የሚሆኑ ተግባራትን ስናከናውን ከርመን አሁን ደግሞ ለእግዛኢብሔር በተቀደሰችሁ በዚህ በሰንበት ቀን ለፈጸምናቸው በደሎች ይቅርታን ለመጠየቅ፣ እግዚኣብሔር ለዋለን ውለታ ምስጋናን ለማቅረብ፣ ቀጣዩም ሕይወታችን በእግዚኣብሔር ተመርቶ ክርስቲያናዊ የሆኑ ሥነ-ምግባራትን በሕይወታችን ውስጥ በመለማመድ፣ ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን መልካም ተግባራትን ለመፈጸም እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን የምንጠይቅበት፣ የምንማጸንበት፣ የምንልምንበት እንዲሁም የምናመሰግነበት እለት ነው እለተ ሰንበት።

የዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

“እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል። በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ብሄድ እንኳ፣አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣እነርሱ ያጽናኑኛል” (መዝ. 23: 1-4)።

ወደ መልካም መንገድ የሚመረና እግዚኣብሔር ነው፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት በጣም ብዙ የሚባሉ ውዥንብሮች በበዙበት ዓለማችን፣ የጦርነት ዜና በሰፊ በሚደመጥበት ዓለማችን፣ በተለዩ ምክንያቶች ኑሮ አስቸጋሪ በሆነበት ዓለማችን እውነተኛ እረፍትን የሚሰጠን እግዚኣብሔር ብቻ ነው። ለዚህ ሲባል ነው እንግዲህ የሰው ልጅ ራሱ በፈጠረው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ተመስርቶ መኖር የማይችለው። ለአእምሮ ረፍትን የሚያጎናጽፈን እግዚኣብሔር ብቻ ስለሆነ እርሱን ዘወትር የሕይወታችን ማእከል አድርገን መኖር ይኖርብናል ማለት ነው።

በዛሬው እለተ ሰንበት የተነበቡልን የእግዚኣብሔር ቃላት በቅድሚያ የተወስደው ወደ ዕብራዊያን ከተጻፈው መልዕክት ከምዕራፍ ዕብ. 6፡ 7-2ዐ  ያለው ሲሆን ይህም “የእግዚኣብሔር የተስፋ ቃል እርግጠኛነትን” የሚገልጽ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ሐዋሪያ ጴጥሮስ የጻፈው የመጀመሪያ መልዕክቱ 3: 8-18 ላይ የተወስደው “መልካም በማድረግ መከራን መቀበል” በሚል አርእስት የሰፈረው ነው። የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የተወስደው ከማቴዎስ ወንጌል 13:1-30 ላይ ያለው እና “የዘሪው ምሳሌ” የሚለው ነው።

 

በዛሬው ወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዳችን ልብ ጉራማይሌ መሆኑን ለማስተማር በማሰብ የዘሪው ምሳሌን በመጠቀም ሕዝቡን ሲያስተምር እናገኛለን። በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሮ ወይም ደግሞ በትምህርት ቤትም ይሁን በማንኛውም የትምህርት መስጫ ሥፍራ ምሳሌን ተጠቅሞ ማስተማር ልናስተላልፈው የፈለግነውን ጭብጥ ሐሰብ በሚገባ ለማስተላለፍ ያስችለናል፣ አድማጫችንንም ወይም አንድ መልእክት ልናስተላልፍለት የፈልግነው ሰው ሐሳባችንን በሚገባ እንዲረዳና ግልፅ ለማድረግ ስለሚያስችል ምሳሌን ተጠቅሞ የማስተማር ዜደ ማዘውተር ተገቢ ነው።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ በጣም ብዙ የሚባሉ ምሳሌዎችን እናገኛለን። ለምሳሌ በተለይም ደግሞ በ2ኛው ሳሙኤል 12:1- የተጠቀሰውን ነቢዩ ናታን ምሳሌያዊ አነጋገርን ተጠቅሞ ንጉሥ ዳዊትን የገሰጸበትን በዋቢነት መውሰድ እንችላለን። ከሁሉም በላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አብዛኛውን ጊዜ በምሳሌ አስተምሯል ምሳሌዎቹም የታወቁ ናቸው፡፡ ምሳሌ አስተዋይና ብልህ ያደርጋል፣ የማያስተውለውን ግን በድንቁርና ያጨልማል /ማር. 4፡1ዐ-12/

ስለምሳሌ ምንነት ይህን ያህል ካልን በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውን የዘሪውን ምሳሌ የበለጠ ለመረዳትና ከሕይወታችን ጋር ለማዛመድ ያስችለን ዘንድ በውስጡ ያሉትን ገጸ-ባሕርያት መመልከት ያስፈልጋል፡፡

ሀ.  ዘር፡- የምስራች ቃል፣ የእግዚአብሔር መንግስት፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ትዕዛዝ

ለ.  መሬት ወይም አፈር፡-የተለያዩ /ጉራማይሌ/ የሆኑትን ልቦናችንን ያመለክታል

ሐ. ዘሪው፡- እግዚአብሔር ሲሆን የተለያዩ አንደበቶችን ይጠቀማል፡፡

  1. በመንገድ ዳር ያለው ልባችን፡- ቃሉ በልባችን ይወድቃል ግን አያፈራም፡፡ ቃሉን እንሰማለን ነገር ግን ወደ ልባችን ዘልቆ አይገባም፡፡ ልባችን ደንድኗል፡፡ ወዲያውኑ ዲያቢሎስ እንደ ወፍ መጥቶ ቃሉን ከልባችን ይወስዳል፡፡ ይህም ባልተዘጋጀ ልብ የእግዚአብሔር ቃል የሚሰሙትን፣ የሚያነቡትን፣ አንዳንዴም የሚያነቡትንና፣ የሚጸልዩትን ሰዎች ልብ ልያውክ ይችላል።
  2. ጭንጫማ ድንጋያማ ልባችን፡- ቃሉ በደስታ ይበቅላል፣ ነገር ግን ስር መሰረት ስለሌለው በቀላሉ በችግር፣ በመከራ ይናወጣል፡፡ እንዲሁም የእግዚብሔርን በረከት ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ዋጋ መክፈልን አይፈልግም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ልብ ያለው ሰው በአንድ በኩል ክርስቶስን ለመከተል የሚፈልጉ ሰዎች ላይ ስደት እንደሚደርስባቸው አልተገነዘቡም፡፡ በሌላ በኩል የጠበቁትን ቁሳዊ ጥቅም አላገኙም፡፡ ስለዚህ ያማርራል፣ ይበሳጫል አልፎም ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ለአጭር ግዜ ይፀናል እስከ ፍፃሜው ግን አይፀናም፡፡
  3. በእሾህ መካከል ያለው ልባችን፡- ክርስቶስን ሕይወት መኖር በጥሩ ሁኔታ መኖር ይጀምሩታል ነገር ግን የዚህ ዓለም አሳብ የሀብት ፍቅር፣ ከንቱ ምኞቶች መነቆ ይሆኑባቸዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ፈጥነው ያድጉና መንፈሳዊ ሕይወታችንን ያንቃሉ፣ ያለፍሬም ያስቀራሉ፡፡ የሌላቸው ቅርንጫፎች ደግሞ ተቆርጠው ወደ እሳት ይጣላሉ፡፡/ዮሐ. 15፡5-6/
  4. በመልካም መሬት ያለው ልባችን፡-ይህንን ልብ የያዙ ሰዎች እግዚአብሔር የሰጣቸውን ስጦታዎች በመገንዘብ በስጦታቸው ሊኖሩ መስዋዕት ይከፍላሉ፡፡ እግዚአብሔር በሰጣቸው ፀጋ ያመሰግናሉ፣ በፀጋው በመኖር ፍሬ ያፈራሉ፡፡ እንዲሁም ይህ ልብ ያላቸው መመሪያቸው የእግዚአብሔር ቃል፣ ቋንቋቸው ፍቅር እና ዓላማቸው ቅድስና ነው፡፡ ታዲያ እኔና እናንተ የትኛው ልብን ይዘን ይሆን?

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው የዘሪው ምሳሌ ኢየሱስ የተጠቀመው በወቅቱ የነበሩት አድማጮቹ በቀላሉ የሚረዱት በምሳሌ ሲነገራቸው በመሆኑ የተነሳ አስተምህሮውን በሚገባ በውስጣቸው ለማስረጽ አስቦ ነው። ዛሬ እኛ ልናነሳው የሚገባው ጥያቄ በእያንዳንዳችን ቤተሰብ ውስጥ፣ በእያንዳንዳችን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ፣ በእያንዳንዳችን ማኅበረሰብ ውስጥ ምን ዓይነት መሬት ነው የሚገኘው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ይገባናል። ይህንን ጥያቄ በምናነሳበት ወቅት በምናገኘው መልስ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን የሚገባን፣ ነገር ግን በተቃራኒው ልባችን የሚገኝበትን ደረጃ ከገመገምን ቡኃላ፣ በልባች ውስጥ የተዘራው የእግዚኣብሔር ቃል እዳያድግ አንቆ የያዙትን እንቅፋቶችን ነቅለን በማውጣት የኢየሱስን ቃል በነጻነት ተቀብሎ በተግባር የሚያውል መልካም የሆነ ልብ እንዲኖረን ራሳችንን እንድንመረምር ጊዜና እድል የሚሰጠን በመሆኑ የተነሳ ነው።

ይህ በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው ምሳሌ በሁለት መንገድ በቀጥታ እኛን ይመለከታል። ሁለት ጥሪዎችን  በቀጥታ ለእኛ በአደራነት ያቀርባል። በመጀመሪያ እግዚኣብሔር ዘሩን የሚዘራብን መልካም ፍሬ ማፍራት የሚችል ልብ እንድንሆን ጥሪ ያቀርብልናል። እርግጥ ነው አንድ አንዴ ልባችን ልክ በመንገድ ላይ እንደ ተዘራው ዘር ይሆናል፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን ግን በጥልቀት ወደ ውስጣችን እንዲገባ ሳናደርገው ቀርተን፣ በዚሁ ምክንያት ክፉ ነገር መጥቶ በልባችን የተዘራውን ዘር ይወስደዋል። አንደንድ ጊዜም ልክ ዛሬ ኢየሱስ እንዳለን በዓለም ጉዳዮች በመጨናንቅ እና በመጠበብ፣ ከእግዚኣብሔር ይልቅ የዓለምን ሐብት ምቾት በምንመኝበት ወቅቶች ሁሉ ዐፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ የወደቀምን ዘር እንመስላለን። ስለዚህም ከዚህ ተግባራችን ተላቀን ለእግዛአብሔር ቃል ምቹ የሆነ፣ ለእራሳችን ብሎም ለማኅበረሰቡ መልካምነትን በጎነትን፣ እና ጽድቅ የሚያጎናጽፍ መልካም ልብ እንዲኖረን በቅድሚያ ጥሪ ያቀርብልናል።

የዛሬው ምሳሌ በሁለተኛ ደረጃ ጥሪ የሚያደርግልን፣ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ መልካም መሬት እንድንሆን ብቻ ሳይሆን ክርስቲያኖች በመሆናችን የተነሳ የእግዚኣብሔርን ቃል መዝራት፣ በጎነትን መስበክ መልካም የተባሉ ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባራትን ለሌሎች እንድናስተምር ተጠርተናል። ስለዚህም በአጠቃላይ ዛሬ ኢየሱስ ጥሪ የሚያደርግልን መልካም እና ፍሬያማ መሬት እንድንሆን ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም ባሻገር የእግዚኣብሔርን ቃል መዝራት እንዳለብን ያሳስበናል።

በተጫማሪም ኢየሱስ ንጹህ የሆነ እምነት እንዲኖረን፣ የቅዱስ ወንጌል ቃላትን በእምነት እንድንቀበል፣ እግዚኣብሔር መልካም ያልሆነውንና መልካም ፍሬ የማያፈራውን መሬት የመቀየር ኃይል እናዳለው ማመን ይኖርብናል። በዛሬው እለተ ሰንበት እንዲህ ብለን እንጸልይ “ጌታ ሆይ በልባችን ውስጥ የተዘራውን የአንተን ቃል በደስታ ማጣጣም እና መጠበቅ እንድንችል እርዳን፣ ቃልህን በትህትና የሚቀበል መልካም እና ፍሬያማ መሬት በልባችን ውስጥ ፍጠርልን፣ መልካም፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ይቅር ባይ፣ ቃልህን አክባሪ ሆነን በመገኘት ቃልህን በታማኝነት መጠበቅ እንድንችል እርዳን” አሜን

 








All the contents on this site are copyrighted ©.