2017-06-25 16:23:00

"የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ዋና ዓላማ አስተምህሮ" በክቡር አቶ ዩሐንስ መኮንን!


የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ዋና ዓላማ

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን በመከታተል ላይ የምትገኙት ከቫቲካን ሬዲዮ የሚተላለፍላችሁን የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ነው። ባለፈው ሳምትን ስለ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አጀማመር በተመለከተ አንድ ዝግጅት ማቅረባችን ይታወሳል። ቃል በገባንላችሁ መሠረት በዛሬው ዝግጅታችን እንቅስቃሴው የተመሠረተበትን ዋና ዓላማ እንመለከታለን።     

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ሲመሠርታት መላው ዓለም የምንቀደስበትን እና በእርሱ የምናምን በሙሉ እንደ እርሱ ፈቃድ የምንመራበትን፣ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ልኮልናል። ይህን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከሰባቱ የቤተክርስቲያን ምስጢራት መካከል በምስጢረ ጥምቀት በኩል እንቀበላለን። ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን ከመጀመሩ አስቀድሞ በመጥመቁ ዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ ከአባቱ ዘንድ የተላከው መንፈስ ቅዱስ በሙላት አርፎበታል። በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ቁጥር 21 እና 22 ላይ የተጻፈውን እናነባለን፥ ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስም ተጠመቀ፤ ሲጸልይ ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሆኖ በእርሱ ላይ ወረደ ፤ በዚያኑ ጊዜ “አንተ የተወደድክ ልጄ ነህ ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣ። ኢየሱስ ክርስቶስም የማዳን ሥልጣኑ እና ስለ አባቱ ዘለዓለማዊ መንግሥት የማስተማር ዕውቀቱ የራሱ ብቻ እንዳልሆነ እንዲህ በማለት ተናግሯል፥ አብ ያስተማረኝን እናገራለሁ እንጂ በራሴ ሥልጣን ብቻ ምንም አላደርግም፤ የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ዘወትር የማደርገው እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ስለሆነ ብቻዬን አልተወኝም (የዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 8 ቁጥር 28 እና 29)። እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው የእግዚአብሔር ስልጣን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት እና የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ወይም ኃይል አንድ ላይ ሆነው እናገኛቸዋለን። ስለዚህ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ስንጠመቅ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሠረታት ቤተክርስቲያን አባል መሆናችንን እናረጋግጣለን። የቤተክርስቲያን አባል መሆን ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ አምላካዊ ኃይል በመታገዝና በመመራት እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበትን መልካም አገልግሎት ለማበርከት የሚያስችለንን ጸጋ እንቀበላለን ማለት ነው። ይህ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመታደስ ፍሬያማ መሆን ይኖርበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ መልዕክቱ በምዕራፍ 5 ቁጥር 19 ላይ፥ “የመንፈስ ቅዱስን ሥራ አታዳፍኑ ይላል።” ከቤተክርስቲያን ምስጢራት መካከል አንዱ የሆነው ምስጢረ ሜሮን፣ በምስጢረ ጥምቀት በኩል ያገኘነው ጸጋ ጥንካሬን እንዲያገኝ፣ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች በይበልጥ በውስጣችን እንዲያድጉ በማድረግ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለንን ትስስር በይበልጥ ፍጹም በማድረግ የክርስቶስ እውነተኛ ምስክሮች ሆነን በቃልና በተግባር እምነታችንን እንድናስፋፋ እና እንድንጠብቅ፣ የክርስቶስን ስም በድፍረት እንድንናገርና በመስቀሉ ከቶውንም እንዳናፍር የመንፈስ ቅዱስን ልዩ ኃይል ይሰጠናል። በማለት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ያስረዳል።

እንግዲህ ይህን ሃቅ በመገንዘብ፣ የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱን በቫቲካን ከተማ ያደረገው ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ የሚከተሉ አምስት ዓላማዎችን ለመላው ምዕመናን ይፋ አድርጓል።

1ኛ        እያንዳንዱ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ፣ በጌታችን እና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማያቋርጥ መታደስን እንዲያመጣ መርዳት፣

2ኛ        ምዕመናን የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት በሙሉ ልብ አምነው፣ እርሱ የሚሰጠውን ኃይል በግል ሕይወት ተቀብለው ክርስቲያናዊ አገልግሎትን ለቤተ ክርስቲያንና ለዓለም ማበርከት እንዲችሉ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ መለወጥን ወይም መታደስን እንዲያመጡ ማበረታታት፣

3ኛ        ምዕመናን መንፈስ ቅዱስን በመቀበል፣ ከእርሱ የሚገኙትን መንፈሳዊ ስጦታዎችን በመላዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ መጠቀም እንዲችሉ ማድረግ፣ እነዚህም መንፈሳዊ ስጦታዎች በምዕመናን፣ በቤተ ክኅነት እና በገዳማዊያን መካከል በሙላት እንዲገኙ በማድረግ፣ ከሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በፍቅርና በሰላም በመተባበር ወደ ቅድስና የሚመራቸውን ሐዋርያዊ ተልዕኮ በኅብረት እንዲያከናዉኑ ማበረታታት፣

4ኛ        የወንጌል ተልዕኮን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመታገዝ ክርስትናን ለተቀበሉትም ይሁን ላልተቀበሉት የቅዱስ ወንጌልን ቃል በስፋት ለማዳረስ እንዲቻል ማገዝ፣ በተለይ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ እንዲፋጠን ከተፈለገ የወንጌልን መልዕክት በቃል እና በተግባር እየኖሩ በማሳየት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች መሆናችንን እንደየ ጥሪአችን መሠረት በእምነትና በፍትሕ መግለጽ እንዲቻል ማበረታታት፣

5ኛ        በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባለን ሙሉ ሕይወት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በቅድስና ማደግ እንዲቻል ማገዝ ፣ በቤተ ክርስቲያን ምስጢራትና የስርዓተ አምልኮ ሕይወት በመሳተፍ፣ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊነት እና የጸሎት ሕይወት መሳተፍ እንዲቻል እገዛ መስጠት፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የምታስተምራቸውን ትምህርቶች መቅሰም እንዲቻል ማድረግና ይህም የቤተ ክርስቲያን አባቶች በሚያወጡት ዕቅዶች የታገዘ እንዲሆን ማድረግ፣ የሚሉ ናቸው።

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን፣ ስለ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ዓላማ በተመለከተ የቀረበውን ዝግጅት በዚህ እናጠቃልላለን፣ ሳምንት በሌላ ዝግጅት እስከምንገናኝ ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን።

ከዮሐንስ መኰንን








All the contents on this site are copyrighted ©.