2017-06-15 10:28:00

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ "ማንኛችንም ብንሆን ያለፍቅር መኖር አንችልም" ማለታቸው ተገለጸ።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በሳምንት አንድ ቀን በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ረፋዱ ላይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች ሰፋ ያለ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። የዚሁ አጠቃላይ የሆነ አስተምህሮ አንድ ክፍል በሆነው በሰኔ 7/2009 ዓ.ም. አስተምህሮዋቸው ከዚህ በፊት የክርስቲያን ተስፋ በሚል አርዕስት ስያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ማንኛውም ሰው ያለፍቅር መኖር አይችልም ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዛት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ማንኛችንም ብንሆን ያለፍቅር መኖር አንችልም በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው  በአንጻሩም “ልወደድ ይገባኛል የሚለው አስተሳሰብ ወደ ባርነት የሚመራን አስተሳሰብ ነው ብለው በአሁን ጊዜ የምንኖር ሰዎች ጭንቀታችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚመነጨው “ብርቱዎች፣ ሳቢዎች እና ቆንጆዎች ካልሆንን፣ ማንም ሰው ስለእኛ አይጨነቅልንም ከሚለው አስተሳሰብ የመነጨ ነው ብለዋል።

ዛሬ ብዙ ሰዎች ውስጣዊ ባዶነታቸውን ለመሙላት ይፈልጋሉ፣ ታዲያ እኛ ሰዎች እንዴት ነው ለውስጣዊ ፍላጎታችን ማረጋገጫ መስጠት የምንችለው? በማለት አስተምህሮውቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ሁሉም ሰዎች ሌሎችን ለመሳብ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉበት እና በተቃራኒው ደግሞ ለሌሎች ሰዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መልካም ነገር የመመኘት ፍላጎት እያነሰ የሚገኝበት ዓለም ውስጥ እንዳለን ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ፍጹም የሆነ የእግዚኣብሔር ፍቅር የተስፋችን ሁሉ ምንጭ ነው በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህም የእግዚኣብሔር ፍቅር በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት እና በተሰጠን  በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተረጋጡዋል ብለዋል።

ማንኛችንም ብንሆን ያለፍቅር መኖር አንችልም። ደስታ የሚመነጨው ፍቅርን ከማወቅ፣ በነጻ የተሰጠን እና የተቀበልነው ስጦታ መሆኑን ስንለማመድ ብቻ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በዓለማችን የሚታየው ደስታ ቢስ የመሆን ስሜት የተወለደው ለራሳችን ስንል ብቻ መወደድ አለብኝ ከሚል ስሜት የመነጨ ነው ብለዋል።

የተገባን ስለሆን ሳይሆን ነገር ግን መልካምነቱን ከእኛ ጋር ለመካፈል በማሰብ እግዚኣብሔር እኛን በዘለዓለማዊ ፍቅር እንደ ሚወደን እምነት ያስተምረና ያሉት ቅዱስነታቸው ከእርሱ መንገድ ርቀን በምንሄድባቸው ጊዜያት ሳይቀር በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው የጠፋ ልጅ አባት ምሳሌ በምሕረቱ ይፈልገናል ፈልጎ ባገኘን ጊዜ ደግሞ ያቅፈናል ብለዋል።

ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ “ነገር ግን እኛ ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ ክርስቶስ በእኛ ምትክ ሞቶአል” እንደ ሚል በማስታወስ አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ በዚህ ተግባሩ ተወዳጅ የእግዚኣብሔር ልጆች እንድንሆን አድርጎናል ብለዋል።

በክርስቶስ ከሙታን መነሳት እና በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታ አማካይነት የእግዚኣብሔር የፍቅር ሕይወት ተካፋዮች ሁነናል ያሉት ቅዱስነታቸው ሁላችንም በእግዚኣብሔር እቅፍ ውስጥ በመግባት አዲስ የነጻነት ሕይወት ውስጥ በመሳተፍ የእርሱ ፍቅር የተስፋችን ሁሉ ምንጭ መሆኑን መረዳት እንችል ዘንድ እንዲረዳን መጸለይ ያስፈልጋል ካሉ ቡኃላ ለእለቱ ያዘጋጁትን አስተምህሮ አጠናቀዋል።  

 








All the contents on this site are copyrighted ©.