2017-06-13 09:47:00

አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ተልኮልናል።


 

አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ተልኮልናል።

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን በመከታተል ላይ የምትገኙት ከቫቲካን ሬዲዮ የሚደርሳችሁን የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ነው። እሁድ ግንቦት 27 ቀን 2009 ዓ. ም. የጴንጠቆስጤ በዓል በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ በድምቀት ተከብሮ መዋሉን ከመንፈሳዊ አስተንትንዎች እና ከቅዱስ ወንጌል ከቀረቡ ንባባት ጋር በማድረግ ማስደመጣችን ወይም መዘገባችን ይታወሳል። በጊዜ ጥበት የተነሳ በዓሉን በማስመልከት ያሉንን ዝግጅቶች በሙሉ በዕለቱ ልናቀርብላችሁ ባለመቻላችን፣ ከዛሬ ጀምሮ በየሳምንቱ በተከታታይ ማቅረብ መልካም ሆኖ ስለታየን እናተም በጽሞና እንድትከታተሉ እንጋብዛችኋለን።

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ዘንድሮ በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተከበረውን የጴንጠቆስጤ በዓል ልዩ የሚያደርገው፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ የተመሠረተበት ሃምሳኛ ዓመት በተመሳሳይ ዕለት ተከብሮ በመዋሉ ነው። ስለ ተሃድሶ እንቅስቃሴው አጀማመር ወይም ታሪካዊ አመጣጥ ከመግለጻችን አስቀድመን በክርስቲያኖች ዘንድ በየዓመቱ ስለሚከበረው ስለ ጴንጠቆስጤ በዓል የሚከተለውን አጭር መልዕክት እናካፍላችኋለን።

ጴንጠቆስጤ የሚለው ቃል ከግሪክ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም ሃምሳኛ ማለት ነው። ይህም የተባለበት ምክንያት በብሉይ ኪዳን ዘመን አይሁዳውያን ከእርሻዎቻቸው እህል አጭደው እና ወቅጠው ወደ የቤታቸው  የሚያስገቡበት ወቅት እና ይህን ካከናወኑ በኋላ ላስገቡት የእህል መጠን ደስታቸውን በመግለጽ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ዕለት በመሆኑ ነው። ይህም ዕለት የፋሲካ በዓል በተከበረ በሃምሳኛው ቀን በመዋሉ ነው።  ወደ አዲስ ኪዳን ዘመን ስንመጣ ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ የገባላቸውን የተስፋ ቃል በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ከቁጥር 15 እስከ 18 የተጻፈውን እናነባለን። “እናትና አባት እንደሌላቸው ልጆች ብቻችሁን አልተዋችሁም ፤ የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ፤ እኔ አብን እለምነዋለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል። ይህ አጽናኝ፥ ስለማያየውና ስለማያውቀው ዓለም ሊቀበለው የማይችለው የእውነት መንፈስ ነው፤ እናንተ ግን ታውቁታላችሁ፤ ምክንያቱም እርሱ ከእናንተ ጋር ስለሚኖርና በውስጣችሁም ስለሚሆን ነው።” በዚህ የተስፋ ቃል መሠረት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በተነሳ በ፶ኛው ቀን ወይም የፋሲካ በዓል ባለፈ በሃምሳኛው ቀን፣ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ከእነርሱም ጋር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተገኘችበት ሥፍራ እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ፣ መንፈስ ቅዱስን ላከባቸው። ይህ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በቤተክርስቲያን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በኃይል የወረደበት ዕለት እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ ቀን ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስን በመቀበል ለዓለም ተገለጠች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ሲመሠርታት በእርሱ የሚያምኑት ሁሉ የሚቀደሱባቸውን የተለያዩ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎችን በአዲስ ኪዳን ሕጉ አዘጋጅቶአል። እርሱ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ በክብር በመቀመጡና ከአብ የተሰጠውን ተስፋ መንፈስ ቅዱስን በመቀበሉ፣ ይህን ከአብ የተቀበለውን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ወደ ዓለም በመላክ በእርሱ የሚያምኑትን ዘወትር ይቀድሳቸዋል።

እንግዲህ ከሐርያት ዘመን አንስቶ የኢየሱስ ፈቃድ ይፈጸም ዘንድ መንፈስ ቅዱስም በእያንዳንዳችን ላይ ወርዶ እንዲያጽናናን፣ እንዲያበረታታን፣ ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ በመረከብ እንዲመራን በምስጢረ ጥምቀት ጸጋ አማካይነት እንቀበላለን። ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ የተላከልን እና በምስጢረ ጥምቀት በኩል የተቀበልነው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ፣ በእምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ጥሪአችን መሠረት መልካም ሥራዎቻችንን እንድናከናውን የሚያግዘን መለኮታዊ ኃይል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም መንፈስ ቅዱስን ስለ መቀበል ሲናገር፣ ወደ ሮም ሰዎች በላከው መልዕክቱ እንዲህ ይላል፥ “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ስለዚህ አባባ ብላችሁ የምትጠሩበትን የልጅነት መንፈስ ትቀበላላችሁ እንጂ በፍርሃት ለመኖር የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁም” ይላል።

ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ የተላከልን እና እያንዳንዳችን የተቀደስንበት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እያንዳንዳችንን የሚያጽናናንና በምሕረቱ ልጆቹ አድርጎን የአንድ ቤተሰብ ወገን የሚያደርገን መንፈስ ነው። የአንድ ቤተሰብ ወገን በመሆናችንም የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ የእርሱን የማዳን ሥራ እንደ ሐዋርያት በሰዎች መካከል በቃልም ሆነ በተግባር የምንመሰክርበትን ኃይል ተቀብለናል።

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን የዚህን ዝግጅት ሁለተኛውን ክፍልና ስለ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሳምንት በምናቀርብርው ዝግጅት እንመለስበታለ። እስከዚያው የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን።

ከዮሐንስ መኰንን








All the contents on this site are copyrighted ©.