2017-04-21 15:06:00

ቅዱስነታቸው ፋጢማ በሚባል ሥፍራ ቅድስት ማሪያ የተገለጸችላቸው ለሁለት ሕጻናት የቅድስና ማዕረግ እንደ ሚሰጣቸው አስታወቁ።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በትላንትናው እለት ማለትም በሚያዝያ 12/2009 ዓ.ም. ፍራንቸስኮ እና ዣሽንታ ማርቶ የተባሉትን ሁለት ታዳጊ እረኞች ለነበሩ ሕፃናት  የቅድስና ማዕረግ በግንቦት 5/2009 ዓ.ም. እንደ ሚያገኙ አስታወቁ።

በወቅቱ እረኞች ለነበሩ ሦስት ሕፃናት እንደ የአውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር የዛሬ 100 ዓመት ገደማ 1917 ዓ.ም. በፖርቱጋል በሚገኘው ፋጢማ በሚባለው አከባቢ ልዩ ስሙ ኮቫ ዳ ኢራ በተባለው ሥፍራ ለሶስት ታዳጊ የከብት እረኞች ለነበሩ ሕፃናት ፍራሲሽኮ፣ ዣሺንታ ማርቶ እና ሉሲያ ለተባሉ ሦስት ታዳጊ ለነበሩ ልጆች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያ የተገልጻላቸው መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ፒዮስ ሰባተኛ እንደ የአውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በግንቦት 13/1946 ዓ.ም. የእዚህን ግልጸት ትክክለኛነት ከመረመሩ ቡኃላ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ሥም የንግደት ሥፍራ ይሆን ዘንድ ቤተ መቅደስ እንዲሠራ ፈቃድ መስጠታቸውና እስከ ዛሬም ድረስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምዕመናን በሥፍራው ንግደት በማድረግ እንደ ሚገኙም ያታወቃል።

በወቅቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ለእነዚህ 3 ሕፃናት በመገለጽ ከጥቂት ዓመታት ቡኃላ ሁለተኛ የዓለም ጦርነት እንደ ሚነሣ በመተንበይ ሁሉም ክርስቲያኖች ሰላም ይሰፍን ዘንድ በእየለቱ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማሪያም የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲያደርጉ ከእመቤታችን ትዕዛዝ መቀበላቸው ይታወቃል።

በተመሳሳይ መልኩም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በእለቱ በ16ኛው እና 17ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት ለነበሩ በአጠቃላይ 35 ለሆኑ ሰዎች የቅድስና ማዕረግ እንደ ሚሰጥ መግለጻቸው የሚታወቅ ሲሆን ከእነዚህም መሀል ሰላሳዎቹ እንደ የአውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1645 ዓ.ም. የሆላንድ ወታደሮች ብራዚልን በቅኝ ግዛት በያዙበት ወቅት የካቶሊክ እምነታቸውን ቀይረው ካልቪን ወደ መሰረተው የፕሮቴስታንት እምነት እንዲቀይሩ በተገደዱበት ወቅት አሻፈረኝ በማለታቸው ደማቸው እንዲፈስ በመደረጉ በጊዜው ላሳዩት መንፈሳዊ ጽናት ይህ የቅድስና ማዕረግ እንደ ተሰጣቸው ተገልጹዋል።

ቀሪዎች ሦስቱ ደግሞ ወጣት የሜክሲኮ ሀገር ተወላጆች መሆናቸው የታወቀ ሲሆን በወቅቱም የካቶሊክ እምነታቸውን ቀይረው ባሕላዊ ወደ ሆነ እምነት እንዲመለሱ ለቀረበላቸው ጥያቄ አሻፈረኝ በማለታቸው የተገደሉ ሲሆን ለዚህ ለእምነታቸው  እስከ መጨረሻ ላሳዩት ጽናት የተሰጣቸው የቅድስና ማዕረግ መሆኑም ተጠቁሙዋል።

ቀሪዎቹ ሁለቱ የቅድስና ማዕረግ የሚሰጣቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካህናት የነበሩ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን አንደኛው በ20ኛው ክፍለ ዘመን ችላ የተባሉና የተጣሉ ሕፃናትን በመሰብሰብ ያሳድጉ የነበሩ የእስፔን ሀገር ተወላጅ የነበሩ ካህን መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በመጨረሻም እንደ የአውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ18ኛው ክፍለ ዘመን በጣሊያን ሀገር በሚገኘው ናፖሊ በሚባለው ጋዛት ውስጥ የሚገኙ ድኻ የሚባሉ የማህበረሰብ ክፍሎች መብታቸው ይከበር ዘንድ ከፍተኛ ትግል ያደርጉ ካህን መሆናቸውም ታወቁዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በግንቦት 5/2009 ዓ.ም. በፖርቱጋል ፋጢማ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ የሚገኘውን የመቁጠሪያዊቷ  የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም  የንግደት ሥፍራ የሆነውን ቤተ መቅደስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ ቡኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመጎብኘት የሚሄዱ መሆናቸውም የተገለጸ ሲሆን በእለቱ እነዚህን የቅድስና ማዕረግ የሚሰጣቸውን ድዕረ ቅዱሳን በይፋ የቅድስና ማዕረግ እንደ ሚሰጣቸዋም ተያይዞ የደረሰን ዜና ያስረዳል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.