2017-04-15 15:11:00

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2009 ዓ. ም. የትንሣኤ በዓል በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክ።


 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ፳፻፱ (2009) . . የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል በማስመልከት ለመላው  ምዕመናን  ያስተላለፉት መልዕክ

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስናው መንፈስ በኩል በታላቅ ኃይል ከሞት በመነሳቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያበሥር ነው፡፡ (ሮሜ 1፡ 4)

ብፁዐን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናትና፤ ገዳማውያን/ዊያት

ክቡራትና ክቡራን ምዕመናን

መላው ሕዝበ እግዚአብሔር

በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ

 

 ከሁሉ አስቀድሜ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል በመስቀሉ ሰላምና እርቅ ያደረገ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው ክብረ በዓል አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን በራሴና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም አቀርብላችኋለሁ፡፡

የዚህን መልእክት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

 የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን ተቀብሎ የተሰቀለውና በመቃብር ውስጥ የዋለው ሞትን ድል ባደረገበት የትንሣኤ በዓል ዛሬ ሁላችንም ልንደሰት ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ለእኛም የዘላለምን ሕይወት ተስፋ አቆይቶልን በመንፈሱ እንድንኖር አድርጎናልና፡፡

የክብር ጌታ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሁላችንንም ኃጢያትና ሸክም ተሸክሞ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተልንን ይህን ታላቅ ፍቅር አስበን በራሱ ደም ያገኘልንን ጽድቅ በፀጋ ተቀብለን ከክፉ ነገሮች ሁሉ በመራቅ ለእርሱ ክብር በቅድስና በመኖር ያደረገልንን ውለታ አክብረን በመያዝ ፍቅርን ተላብሰን መኖር ያስፈልገናል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሕይወቱን አሳልፎ ለዓለም ሁሉ ሕዝብ ብርሃን በመሆን ከሞት ተነሥቷል፡፡ እርሱ ሞትን ድል የነሣ የጌቶች ጌታ ነው፡፡ እኛም የትሣኤውን ጌታ ሁሌም በማክበር ለእግዚአብሔር ክብርና ለመንፈሣዊ ሕይወታችን ግንባር ቀደም ሆነን በመገኘት ከክርስቶስና ከቤተክርስቲያን ያገኘነውን የእምነት ሥራ አጠንክረን በመያዝ ጌታችን እንደሚያስተምረን እንዲሁም መልካም ሥራችሁን አይተው የሰማይ አባታችሁን እንዲያመሰግኑት የእናንተም ብርሃን በሰው ፊት ይብራ (ማቴ.5፡16) ባለን መሠረት በየዕለት ከዕለት ሕይወታችን ውስጥ ዘወትር የተግባር ምስክርነት መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡

 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ ፈቃድ ስለሁላችን በመሞት የጥልን ግድግዳ በማፈራረስ ሰላሙን በመስጠት ንጉስነቱን አሳይቶ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጭኖአል፡፡ በመስቀሉ ሰላምን ሰራ፤ በመስቀሉ እርቅ ወረደ ፡፡

በጌታችን ትንሣኤ የእግዚአብሔር ልጆች በተቀደሰው እውነት አዲስ ብርሃን አይተዋል ስለዚህ በመንገዳችን እርምጃ ከኛ ጋር ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔር ዘውትር ከእኔ ጋር እንደሆነ አውቃለሁ በአጠገቤም ስለሆነ አልታወክምይላል  (መዝ .168 )፡፡ ሕያው የሆነው ኢየሱስም ጠባቂያችን በመሆን መንገዳችንን ይመራናል፡፡ እኛም ልባችንንና ፈቃዳችንን ሙሉ በሙሉ ልንሰጠው ይገባናል፡፡

እኛም ክርስቲያኖች ወደእርሱ በመቅረብ በትንሣኤው ፀጋና በረከት ከኃጢያት መንገዶች በመራቅ ከእግዚአብሔር አባታችን የሚያርቁንን መጥፎ ተግባሮች ሁሉ አስወግደን በሃይማኖት እምነትና መልካም ሥነ ምግባር በመታገዝ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሆነን መጓዝ ይኖርብናል፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን ሐዋርያዊ ያዕቆብ የሚለብሱትና የሚመገቡት የሌላቸው ወንድሞችና እህቶች ቢኖሩ፣ እናንተ ለኑሮአቸው የሚያስፈልጋችውን ነገር ሳትሰጡአችውበሰላም ሂዱ ! ይሙቃችሁ፣ ጥገቡ !”  ብትሉአቸው ምን ይጠቅማቸዋል፤ ከመልካም ሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው ይላል፡፡ (ያዕ 2፡15-17)  በመሆኑም በዚህ የትንሣኤ በዓል ጊዜ በራሳችን ጥቅም ሳንወሰን ክርስቶስ በኛ ላይ የጣለውን መልካም የማድረግ ሁኔታን ሳንዘነጋ  እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ በመርዳትና በማካፈል በዓሉን እንድናከብር አደራ እላችኃለሁ፡፡ እንዲሁም በአገራችን በንዳንድ ቦታዎች በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት በደረሰው ድርቅ የተጎዱትን ወገኖቻችንን ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ በማድረግ እግዚአብሔር ዝናቡን እንዲያወርድልን በጸሎታችን እንበርታ፡፡

በቅርቡ ቤተክርስቲያንንና መላውን ምዕመናን እንዲሀም ሕዝባችንን ያሳዘነው አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ ክስተትና በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በወረዳ አንድ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የደረሰው ከፍተኛ አደጋ የሁላችንንም ልብ ያሳዘነ እንደመሆኑና እንዲሁም በተለያየ አደጋዎች የሞቱትን ወንደሞቻችንና እህቶቻችንን ዘላዓለማዊ መንግስቱን እንዲያዋርስልንና ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥልን በጌታ ትንሣኤ እንመኛለን፡፡

መንግስትም ሰላማዊና ከአደጋ የነጻ የትራፊክ ምልልስና ውሎ እንዲኖር ለተያያዘው እርምጃ ምዕመናኖቻችንና ሕብረተሰባችን ተባባሪ እንዲሆኑ እያሳሰብኩ ከአደጋ የነጻ አካባቢንም ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት እምነታችን የጸና ነው፡፡

የሰላሙ ንጉሥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአገራችን ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለጎረቤቶቻችን ሰላሙን ይስጠን፡፡

በመጨረሻም ከአገር ውጭ የምትኖሩ በተለያዪ ሥራዎችና ትምህርቶች ተሰማርታችሁ ያላችሁ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምዕመናኖቻችን፣ የአገር ድንበር ለማስከበር በየዳር ድንበሩ የምትገኙ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት፤ ከአገር ውጭ ተሰማርታችሁ ያላችሁ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ በየሐኪም ቤቱና በየቤቱ የምትገኙ ህሙማን፤ እንዲሁም  በማረሚያ ቤቶች ያላችሁ የሕግ ታራሚዎች በጌታ ትንሣኤ እግዚአብሔር  እንዲባርካችሁ፣ እንዲምራችሁና እንዲፈታችሁ እየተመኘሁ ለሁላችሁም እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የደስታና የፍሰሐ ብሎም የበረከት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያን አገራችንን ይባርክልን ይጠብቅልን፡

U ፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ








All the contents on this site are copyrighted ©.