2017-03-30 14:12:00

ተጨባጭ ያልሆኑና ሐሰተኛ የሆኑ ጣኦቶችን መከተል አቁመን የምንከባከበንን እግዚኣብሔር ልንከተል ይገባል።


“ተጨባጭ ያልሆኑ እና ሐሰተኛ የሆኑ ጣኦቶችን መከተል አቁመን እንደ አባት ለሚወደን እና ምንጊዜም የምንከባከበንን እግዚኣብሔር ልንከተል ይገባል” ይህንን የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በዛሬው እለት ማለትም በመጋቢት 21/2009 ዓ.ም. በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት የተወሰደ ነው። ቅዱስነታቸው በእለቱ በላቲን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር በተነበበውና ከኦሪት ዘፀአት 32: 7-14 ላይ በተወሰደው የመጀመሪያ ምንባብ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው እንደ ነበረ የታወቀ ሲሆን በዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተመርኩዘው ምንም እንኳን ሕዝቡ በእግዚኣብሔር ላይ ያለውን እምነት ቀስ በቀስ እያጣ ቢመጣም እግዚኣብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር ግን ሁሌም ይቀጥላል፣ እኛም ዛሬ  ከጌታ በመራቅ ለጣኦቶች እና ለዓለም በምንገዛባቸው ወቅቶች ሁሉ ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል ብለዋል።  

የዚህን ዜና ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

“እግዚአብሔር ሕዝቡን ፈልጎ ነበር፣ በተቃራኒው ሕዝቡ እርሱን ቅር አሰኝቶት ነበር” ያሉት ቅዱስነታቸው  ከኦሪት ዘፀአት በተወሰደው በእለቱ ምንባብ ላይ ተመርኩዘው “ሕልም እና የእግዚኣብሔር ቅሬታ” በሚሉ ጭብጦች ዙሪያ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው እንደ ገለጹት “እግዚኣብሔር ሕዝቡን ሰለሚወድ ሕልም ያልምላቸዋል” ካሉ ቡኃላ ያ የእስራኤል ሕዝብ ግን የእግዚኣብሔርን ሕልም ከንቱ ባደረጉበት ወቅት፣ በዚህ ጉዳይ ግራ በመጋባት ሙሴ ሕግጋቱን ሊቀበል ከወጣበት ተራራ እንዲወርድ እግዚኣብሔር ጠርቶት ነበር ብለዋል። “ሕዝቡ እግዚኣብሔርን ለ40 ቀናት ያህል ብቻ የመጠበቅ ትዕግስት አልነበረው ነበር” ያሉት ቅዱስነታቸው ያዳናቸውን እግዚኣብሔርን ዘንግተው “ለመዝናኛ የሚሆን” በወርቅ የተሠራ የጥጃ ምስል ሠርተው ማምለክ እንደ ጀመሩ ገልጸዋል።

ነቢዩ ባሩክ ይህንን ሕዝብ በተመለከተ “ከፍ ያደርጋችሁን ማን እንደ ሆነ ረስታችኃል” የምል አንድ ሐረግ ጽፎ እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው የፈጠረንን፣ እንድናድግ፣ በሕይወታችን ከእኛ ጋር የተጓዘውን እግዚኣብሔር መርሳት እግዚኣብሔርን ያስከፋል ብለዋል። ብዙን ጊዜ ኢየሱስ በወንጌል ውስጥ በተጠቀሱት ምሳሌዎች የወይን እርሻ ስፍራ ስለ ነበረው ሰው በመጥቀስ በዚያ የወይን ስፍራ የሚሠሩ ሰዎች ትርፉን ራሳቸው የወስዱ ስለነበር ይህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ኪሳራ ውስጥ በመግባቱ የተነሣ ሁል ጊዜ በልቡ ይጨነቅ እንደ ነበረ ተደጋግሞ የተጠቀሰ ምሳሌ እንዳለ በመጥቀስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “የሰው ልጅ ልብ ታማኝ በሆነው በእግዚኣብሔር ፍቅር አይረካም፣ የሰው ልጅ ልብ ሁሌም ከታማኝነት የምርቅ ልብ ነው፣ ይህም የሰው ልጅ ፈተና ነው” ብለዋል።

ስለዚህም እግዚኣብሔር “ይህንን አቋም የሌለውን፣ በትዕግስት መጠበቅ የማይችለውን፣ ይህ ተበላሽቶ ያደገውን ሕዝብ በአንድ ነቢይ አማካይነት ይገስጻቸዋል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከእውነተኛው እግዚኣብሔር ርቆ ሌላ ሐሰተኛ የሆን አምልክ መፈለግም ጀምረው ነበር ብለዋል።

“ሕዝቡ እምነቱን አጉድሉዋል፣ እግዚኣብሔርም ቅር ተሰኝቱዋል፣ እኛም ራሳችን የእግዚኣብሔር ሕዝቦች እንደ መሆናችን መጠን ልባችን በምን ዓይነት ደረጃ ላይ እንደ ሚገኝ ጠንቅቀን እናውቃለን እና ቀስ በቀስ ተነሸራተን ወደ ጣኦት አምልኮ፣ ወደ ጊዜያዊ ደስታ፣ ወደ ዓለማዊ ኑሮ በመጨረሻም ታማኝነታችንን ወደ ማጣት ደረጃ እንዳንደርስ ሁል ጊዜ እርምጃችንን ማስተካከል ይገባናል” ብለዋል።

ዛሬ በእኛ ያልተደሰተው አምላክ አንድ ነገር እንድናስብ እንደ ሚረዳን አምናለሁ በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ጌታ ሆይ ነገረኝ፣ በእኔ አዝነሃል ወይ? በአንድ አንድ ነገር አዎን! እርግጠኛ ነኝ አዝነሃል! ይህን ዓይነት ጥያቀ ማንሳት እና ማሰብ ያስፈልጋል” ብለዋል።

እግዚኣብሔር “ለስላሳ እና አባታዊ የሆነ ልብ ነው ያለው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ለኢየሩሳሌም ያለቀሰላትን ለቅሶም ያስታውሳል ብለዋል። እስቲ አሁንም ጥያቄ እንጠይቅ “በኔ ካልተደሰተ፣ ከአምላክ በምርቅባቸው ወቅቶች ሁሉ እግዚኣብሔር ለእኛ ያለቅሳል ወይ?” በማለት ጥያቄን በድጋሚ በማንሳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ዙርያየን ከበው የሚገኙ እና ላስወግዳቸው  ያልቻልኩዋቸው፣ በባርነት ጠፍረው የያዙኝ ስንት ጣኦቶች በዙሪያዬ አሉ?፣ በእኛ ውስጥ ስንት ጣኦቶች አሉ? . . . ወዘተርፈ ብለን ስንጠይቅ እግዚኣብሔር ለእኛ ያለቅሳል” ብለዋል።

“እኛ በፍቅር የፈጠረንን እግዚኣብሔርን በመተው ሌላ ፍቅር፣ ደህንነትንም በመሻት የአርሱን ፍቅር ትተን ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ ያንን ለማጣጣም በምንፈልግበት ወቅቶች ሁሉ እግዚኣብሔርን እንደምናሳዝነው ዛሬ ማሰብ ይገባናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ይህንን በምናደርጋባቸው ወቅቶች ሁሉ ከፍ ካደረገን እግዚኣብሔር እንርቃለን ይህ የዓብይ ጾም ወቅት ይህንን ተግባራችንን የምንገመግምበት ወቅት ሊሆን የገባል” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ እንደ ገለጹት “በእየ ቀኑ ሕሊናችንን በመመርመር “ጌታ ሆይ አንተ ለእኔ ብዙ መልካም ሕልሞች ነበሩህ፣ እኔ ግን ከአንተ መራቄን አውቃለሁኝ፣ እንደት እና መቼ ወደ አንተ እንደ ምመለስ እባክህን ንገረኝ” ብለን በምንጠይቅባቸው ጊዜያት ሁሉ እርሱ በሚይስደምም መልኩ ልክ ጠፍቶ እንደ ተገኘው ልጅ አባት ሁል ጊዜ በደጅ ቆሞ እንደ ሚጠባበቀን መረዳት እንችላለን ካሉ ቡኃላ ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.