2017-03-28 10:14:00

ጾም መጾም ለምን አስፈለገ?


ጾም መጾም ለምን አስፈለገ?

ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደኅንነት ሚስጢር ጋር አዛመደን በመገምገምና የራሳችንን ሂሲ በመስጠት “እርሱ በሞተ ጊዜ ኋጥያት በእርሱ ላይ ሥልጣን እንዳይኖረው በማያዳግም ሁኔታ አንድ ጊዜ ሞቶዋል” (ሮሜ 6:10) የሚለውን ከግምት በማስገባት ታዲያ ኢየሱስ በማያዳግም ሁኔታ አንድ ጊዜ ከሞተልንና ካዳነን የእኛ በጾም እና በጸሎት መድከም ምን ዋጋ አለው? ለምንስ አስፈለገ? ልንል እንችል ይሆናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾምንና የጸሎትን አስፈላጊነት በበረሃ ለ40 ቀንት በመጾም (ማቴ. 4.2) የጾምን አስፈላጊነት አሳይቶናል። በተጨማሪም በጌተ ሰማኒ በአትክልቱ ሥፍራ ደም እስከ ምያልበው ደረስ በመጸለይ (ሉቃስ 22.44) የጸሎትን አስፈላጊነት እርሱ ራሱ በተግባር አሳይቶናል።

በምድር ላይ የክርስቶስ ሙሽራና የእርሱ ተወካይ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን እንድንጾም እና በጸሎትም እንድንበረታ የምታዘን በአንድና በአንድ ምክንያት ብቻ ነው። ይህም ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንዲህ ይላል “አንድ እንኳን ጻዲቅ ሰው የለም አስተዋይም ሰው የለም፣ እግዚኣብሔርን የሚፈልግ የለም፣ ሁሉም ከእውነት መንገድ ወጥተው ተሳስተዋል፣ ደግ ሥራ የሚሰራ አንድም ሰው እንኳን የለም፣ ሰውን የሚጎዳ ክፉ ቃል ለመናገር አፋቸው እንደ መቃብር የተከፈተ ነው፣ በምላሳቸው ያታልላሉ፣ የከንፈራቸው ንግግር እንደ እባብ መርዝ የሚጎዳ ነው፣ አፋቸው በመራር እርግማን የተሞላ ነው፣ እግራቸው ሰውን ለመግደል የፈጠነ ነው፣ በመንገዳቸው የሚገኘው ጥፋትና መከራ ነው፣ የሰላምን መንገድ አያውቁም እግዚኣብሔርን ከቶ አይፈሩም” ይለናል ሐዋሪያው ጳውሎስ ውደ ሮም ሰዎች በጻፈው መልእክቱ 3:13-18 ላይ።

ከላይ ሲነበብ እንደ ሰማነው ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ “ደግ ሥራ የሚሰራ አንድም ሰው እንኳን የለም፣ እግዚኣብሔርንም ከቶ አይፈሩም” ይለና። ለእዚህም ነው ታዲያ ከላይ የተዘረዘሩ ክፉ ነገሮች በመፈጸማችን የተነሳ ከእኛ እርቆ የነበረውን የእግዚኣብሔር ፀጋ መልሰን መጎናጸፍ እንድንችል በቅድሚያ መጽዳት ይኖርብናል። ይህ የጾም ወቅት ራሳችንን ለመንፈሳዊ እሴቶች ማስገዛት እንድንችል፣ ክፉ ተግባሮቻችንን አስወግደን በመታደስ ወደ እግዚኣብሔር መመልስ እንችል ዘንድ የምንጸልይበት፣ የምንጾምበት፣ ለተቸገሩ ሁሉ የምንመጸውትበት፣ ለፈጸምነው በደል ይቅርታን የምንጠይቅበትና ለኋጥያታችን እና ለፈጸምነው በደል ሁሉ ካሳ የምንከፍለበት ልዩ ወቅት ነው። በተለይም ደግሞ የደኅንነታችን ሁሉ ምንጭ የሆነውን በፋሲካ በዓል ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መሰቃየቱን፣ መገረፉን መሞቱን እና ከሙታን መነሳቱን በማስታወስ እኛም እንደ አንድ ክርስቲያን የእርሱን ፈለግ በመከተል ስለ ኋጢያታችን የምናዝንበት፣ ግላዊ የሆኑ ፍላጎቶቻችንን የምንሰዋበት፣ በሕይወታችን ዘመን ሁሉ እግዚኣብሔርንና እህት ወንድሞቻችንን እንዳነውድ ደንቃራ በመሆን የጋረደንን የሰይጣን ክፉ መንፈስ በክርስቶስ መስቀል ላይ በመቸንከር ከኋጥያት ቀንበር ነጻ የምንወጣበት ወቅት ነው የጾም ወቅት። በአጠቃላይ ስንመለከት ከኋጥያት ባርነት ወደ ነፃነት የሚደረግ ጉዞ ነው የጾም ወቅት።

የሰው ልጅ የሚፈጽመው በደል እና ኋጥያት በቃላት ለመገልጸ ያዳግታል። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እግዚኣብሔር ሰውን በመፍጠሩ ተጸጽቶ እንደ ነበረ ይገልጻል። በኦርት ዘፍጥረት 7:4 እንዲህ ይላል “ከሰባት ቀን ቡኋላ ለአርባ ቀን እና ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለው የፈጠርኩትን ሕያው ፍጡር ሁሉ መልሼ ከምድር ገጽ አጠፋለሁ” ይላል። ምክንያቱም በእዚያን ዘመን ከነበሩ ሰዎች መካከል ጻዲቅ ሆነ የተገኘው አንድ ሰው ብቻ ነበረ ስሙም ኖኅ ይባላል።

በእዚህ የጾማችን ወቅት እንደ ቃዬን ሳይሆን እንደ አቤል፣ እግዚኣብሔር በውሃ መጥለቅለቅ እንዳጠፋቸው ሰዎች ሳይሆን እንደ ኖኅ ከምርጦቹ አንዱ እንድንሆን፣ እንደ ሳኦል ሳይሆን እንደ ጳውሎስ፣ እንደ ስምዖን ሳይሆን እንደ ጴጥሮስ እንድንሆን የተጠራንበት ቅዱስ ወቅት በመሆኑ ጾማችንን በተለምዶ እንደ ምናደርገው ከምግብ እና ከመጠጥ በመታቀብ ብቻ የምናሳልፍበት ወቅት ሳይሆን እግዚኣብሔር በሚሻው መንፈሳዊ ጎዳና ላይ መመላለስ እንድንችል እሜቤታችን ቅድስት ማሪያም ሁላችንንም በጸጋዋ ትርዳን። አሜን!!

ምንጭ፡ በአባ መብራቱ ኃይሌጊዮርጊስ የተዘጋጀ።








All the contents on this site are copyrighted ©.