2017-03-28 10:59:00

ምስጢረ ንስኃ


በዓብይ ጾም ወቅት ምዕመናን ከእግዚኣብሔርና ከእህት ወንድሞቻቸው ጋር የሚታረቁበት ወቅት ነው። በኃጢያታችን ምክንያት እግዚኣብሔርን፣ ራሳችንን፣ ወንድም እህቶቻችንና ተፈጥሮንም ሳይቀር በድለናል። ይህንን በደላችንን ደግሞ በዚህ በዓብይ ጾም ወቅት ለየት ባለ ሁኔታ ሱባኄንና ንስኃን በማድረግ ከእግዚኣብሔርና ከእህት ወድሞቻችን ጋር መታረቅ ያስፈልጋል። በዛሬው አስተምህሮዋችን ሚስጢረ ንስሓ በከቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ደንብ እና ስርዓት መሰረት ምን ይመስላል የሚለውን እናቀርብላችኃለን እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

ምስጢረ ንስኃ

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የነፍሳችንና የሥጋችን ሐኪም ሽባውን ከኃጢአቱ ይቅር ብሎት አካላዊ ጤንነቱን እንደመለሰለት ሁሉ፣(ማር.2፤1-12) ቤተ ክርስቲያኑም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የመፈወስና የማዳን ሥራዎቹዋን በራሱዋ አባለትም መካከል ቢሆን እንድትቀጥል ፈቃዱ ሆኗል። የሁለቱ ምሥጢራት ማለትም ምስጢረ ንስሐና ምስጢረ ቀንዲል ዓላማም ይኸው ነው።

ንስሐ የእርቅ ምስጢር

ወደ ምስጢረ ንስሐ የሚቀርቡ ሰዎች ስለፈጸሙት ኃጢአት ከእግዚአብሔር ምሕረትን ያገኛሉ። እንዲሁም ወደ ቅዱስ ሕይወት ይመጡ ዘንድ በፍቅር፣ በመልካም አርአያነት በጸሎት ስለእነርሱ ከምትተጋውና ኃጢአታቸው ካቆሶሏት ቤተክርስቲያን ጋር ይታረቃሉ።

ከጥምቀት በኋላ የእርቅ ምስጢር ለምን አስፈለገ?

 “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋልም።” “ክርስቶስን ከለበሰው” ዘንድ ኃጢአት ምን ያህል እንደተወገደ ለመገንዘብ ማንም ቢሆን ክርስቲያንነትን በሚያስገኙት ምሥጢራት አማካይነት እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታ መጠን መረዳት መቻል አለበት። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ይላል “ኃጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናታልላለን፤ እውነትም በውስጣችን የለም”(1ዮሐ. 1፤8)፤ “እርስ በራሳችን ስለኃጢአታችን ይቅር መባባላችንን እግዚአብሔር ለኃጢአታችን ከሚያደርግልን ይቅርታ ጋር በማያያዝ፣ ጌታ ራሱ” “በደላችንን ይቅር በለን”(ሉቃ.11፤4, ማቴ.6፤12) በማለት እንድንጸልይ አስተምሮናል።

በክርስቶስ ማመን፣ የጥምቀት አዲሱ ልደት፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታና የምንመገበው የክርስቶስ ሥጋና ደም፣ ልክ ራሷ ቤተክርስቲያን፣ የክርስቶስ ሙሽራ፣ “ቅድስትና አለነውር” እንደሆነች ሁሉ እኛንም (ኤፌ.1፤4, 5፤27) “ቅዱሳንና ነውር የሌለን” አድርገውናል። ይሁን እንጂ ክርስትናን በመቀበል ያገኘነው አዲስ ሕይወት የሰውን ተፈጥሮ ልዕልነትና ድክመት፣ በዘልማድ ፍትወተ ሥጋ (ጽነት) በመባል ወደሚታወቀው ኃጢአት ማዘንበልን አላስወገደም። ከክርስቶስ የጸጋ ድጋፍ ጋር በክርስቲያናዊ ሕይወት ትግል ራሳቸውን ብቁ እስካላደረጉ ድረስ፣ በተጠመቁም ዘንድ ይኖራልና። ጌታ ከቶውንም ሳያቋርጥ ወደሚጠራን ቅድስናና ዘላለማዊ ሕይወት የሚመራን የእምነት ትግል ይህ ነው።

ምሥጢረ ንስሐ - ለተጠመቁት የመመለስ ጥሪ ነው

“የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” (ማር.1፤15) እያለ ኢየሱስ ሰዎች እንዲመለሱ ይጣራል። ይሄ ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት ዋነኛ ክፍል ነው። በቤተክርስቲያን ስብከት ውስጥ ይህ ጥሪ በመጀመሪያ ደረጃ የሚተላለፈው ክርስቶስንና ወንጌልን ገና ላላወቁ ነው። እንዲሁም ጥምቀት ለቀዳሚና መሠረታዊ እምነት ሁነኛው ሥፍራ ነው። አንድ ሰው ክፋትን በማውገዝ ድኅነትን፣ ማለትም ለኃጢአቱ ምሕረትንና አዲስ ሕይወትን የሚያገኘው፣ ወንጌልን በማመንና በጥምቀት ነው። (ሐዋ.ሥራ 2፤38)

ይህ ሁለተኛው መለወጥ “ኃጢአተኞቹን በጉያዋ የያዘችውና፣ ቅድስትና በዚያው መጠን ሁልግዜም መንጻት የሚያሻት፣ እንዲሁም የንስሐና የተሃድሶን ጐዳና የምትከተለው፣ የመላዋ ቤተክርስቲያን የማያቋርጥ ተግባር ነው።” ይህ ንስሐ የመግባት የመአለስ ጥረት ሰብአዊ ክንውን ብቻም አይደለም። አስቀድሞ ለወደደን ለእግዚአብሔር መሐሪ ፍቅር ምላሽ ለመስጠት በጸጋ የተሳበና የተመሰጠ “የሚጸጸት ልብ” ትርታም ነው። (መዝ.51፤17, ዮሐ.6፤44,12፤32, 1ዮሐ. 4፤10)

ጌታውን ሦስት ጊዜ ከካደ በኋላ የጴጥሮስ ንስሐ /መመለስ/ ለዚህ ምስክር ነው። የኢየሱስ ማለቂያ የሌለው የመሐሪነት ገጽታ ከጴጥሮስ ዐይኖች የንስሐ እንባና፣ ከጌታ እርገት በኋላም፣ ለእርሱ ስላለው ፍቅር የሦስት ጊዜ እጥፍ ማረጋገጫ አፍልቋል። ሁለተኛው መመለስ “ንስሐ ግቡ!” በማለት ለመላዋ ቤተክርስቲያን የቀረበው የጌታ ጥሪ እንደሚያሳየው ማኅበራዊ ገጽታ አለው።

ውስጣዊ ንስሐ

እንድንለወጥና ንስሐ እንድንገባ የቀረበው የኢየሱስ ጥሪ፣ ከእርሱ በፊት እንደነበሩት ነቢያት ጥሪ፣ በመጀመሪያ ደረጃ “ማቅ በመልበስ አመድ በመነስነስ”፣ እንዲሁም በጾምና ተጋድሎ ላይ የሚያተኩር ውጫዊ ሳይሆን፣ ልባዊ ወይም ውስጣዊ መለወጥን የሚጠይቅ ነው። ያለ ንስሐ ፍሬ ቢስና ከንቱ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ውስጣዊ መለወጥ ገሃድ በሆኑ ምልክቶች እንቅስቃሴዎችና የንስሐ ሥራዎች መገለጽ ያሻዋል። (ኢዩኤል 2፤12-13፣ ኢሳ.1፤16-17፣ ማቴ.6፤1-6፣16-18)

ውስጣዊ ንስሐ የመላ ሕይወታችን ሥርነቀል ለውጥ፣ ፀፀት፣ በሙሉ ልባችን ወደ እግዚአብሔር መመለስ፣ የኃጢአት ማክተሚያ፣ የፈጸምናቸውን መጥፎ ተግባራት በመጥላት ከክፋት መራቅ ነው። ይህ ሁኔታ በእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ በማድረግና በጸጋው ድጋፍ በመተማመን፣ ሕይወትን የመለውጥ ምኞትና ውሳኔም ያስከትላል። ይህ ልባዊ መለወጥ አበው የመንፈስ ስብራትና ልባዊ ፀፀት በሚሏቸው ውጤታማ ሕመምና ሐዘን የታጀበ ነው።

የሰው ልብ ከባድና ደንዳና ስለሆነ እግዚአብሔር ለሰው ዘር አዲስ ልብ መስጠት አለበት። (ሕዝ.36፤26-27) መለወጥ/መመለስ ከሁሉም በፊት ልባችንን ወደ እርሱ የሚመልስልን የእግዚአብሔር ጸጋ ሥራ ነው። “አቤቱ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን” (ሰቆቃወ ኤርሚያስ 5፤21) እንደ አዲስ እንጀምር ዘንድ እግዚአብሔር ብርታትን ይሰጠናል። የእግዚአብሔርን ፍቅር ታላቅነት ባወቀ ጊዜ ነው ልባችን በኃጢአት አስፈሪነትና ክብደት ተንቀጥቅጦ በኃጢአት የተነሳ እግዚአብሔርን ላለማስቀየምና ከእርሱም ለመለየት መፍራት የሚጀምረው። ልባችን የሚለወጠው በኃጢአታችን የወጋነውን እርሱን በማየት ነው። (ዮሐ.19፤37, ዘካ.12፤10)

ከዕለተ ፋሲካ ጀምሮ፣ መንፈስ ቅዱስ “ዓለም ስለ ኃጢአት መሳሳቱን” (ዮሐ.16፤8-9) ማለትም ዓለም እግዝአብሔር አብ የላከውን አለማመኑን አረጋግጧል። ነገር ግን ኃጢአትን ቁልጭ አድርጎ በማሳየት የሰው ልብ ለንስሐና ለመመለስ የሚያበቃውን ጸጋ የሚሰጠው አጽናኝ ይኸው መንፈስ ቅዱስ ነው። (ዮሐ.15፤26, ሐዋ.ሥራ 2፤36-38)።

ምንጭ፡ ከኢትዮጲያ የሲታዊያን መነኩሳት ማህበር ድኅረ ገጽ የተወሰደ። (www.ethiocist.org)

 








All the contents on this site are copyrighted ©.