2017-03-28 13:00:00

መልካም ሥራችንን በጊዜ እና በቦታ መገደብ የለበትም።


መልካም ሥራችንን በጊዜ እና በቦታ መገደብ የለብንም

ዝግጅታችንን ለምትከታተሉ አድማጮቻችን በሙሉ በድጋሚ ልባዊ ሰላምታችንን እናቀርብላችኋለን። እንደሚታወቀው ይህ ወቅት የጾምና የጸሎት እንዲሁም የእኛ እገዛ እና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በሙሉ ከወትሮ በበለጠ በፍቅርና በርኅራሄ ልብ ተነሳስተን በጎ ሥራችንን የምናበረክትበት ወቅት ነው። እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን አንድ ነገር ቢኖር መልካም ሥራችንን በጊዜ እና በቦታ መገደብ የለብንም። ለምሳሌ “ያለሁበት ወቅት የጾም ወቅት ስለሆነ በእነዚህ ቀናት ወይም ሳምንታት ውስጥ በምኖርበት አካባቢ መልካምን ባደርግ” ብለን ማሰብ ተገቢ አይደለም። የዕድሜአችን እያንዳንዷ ቀን ለሌችም ሆነ ለራሳችን መልካምን ሠርተን የምናልፍባት የእግዚአብሔር ውድ ስጦታ ናትና። ባለፉት ዝግጅቶቻችን ቅዱስ መጽሐፍትን መሠረት ያደረጉ አንዳንድ መልዕክቶችን ስናካፍላችሁ መቆየታችን ይታወሳል። በዛሬው ዝግጅታችን “ምሕረትን ስለማድረግ” በሚል ርዕስ ወደ ተዘጋጀው አጭር መልዕክት እንወስዳችኋለን። ቆይታችሁን ከእኛ ጋር በማድረግ እንድትከታተሉን እንጋብዛችኋለን።

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በዕለታዊ ኑሮአችን የሚያጋጥሙን ብዙ የተለያዩ ገጠመኞች አሉ። መልካም ሥራችን በሰዎች ዘንድ እንድንወደድ፣ ጥሩ ስምን እና አክብሮትን እንድናገኝ ሲያደርጉን በተቃራኒው በቤተሰብ፣ ወይም በጎረቤት፣ ወይም በጓደኛ ወይም በማንም ላይ የምንፈጽመው በደል ጥላቻንና ቅራኔን ከማትረፍ ባሻገር ክፉዎች እንድንባል ያደርገናል። ነገር ግን ሌሎችን በድለን ከሆነ ወይም ሌሎች እኛን በድለውን ከሆነ፣ ይህን ከመሰለ በኑሮአችን መካከል እንቅፋት ከሚሆንብን ከማይመች አካሄድ ተመልሰን እርቅን፣ ሰላምን እና ፍቅርን የምንጀምርበት መንገድ ባይኖር ኖሮ የምንኖርባት ዓለማችን ምንኛ የከፋች እንደምትሆን መገመት አያዳግትም። በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ሲከሰት የሚታየው ጥላቻና ጦርነት መመልከት በቂ ይሆናል።

ቅዱስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ. በ1997 ዓ.ም. የዓለም ሰላም ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ “ዘመናችን የሰው ልጅ በኤኮኖሚ ወይም በሃብት ለመበልጽግ፣ በተራቀቁ ሳይንሳዊ ግኝቶች አዲስ ውጤቶችን ለማስመዝገብ የሚሽቀዳደምበት ዘመን እንደሆነ ገልጸው፣ ይህም በሰዎች መካከል በብዙ መልኩ ስምምነት ማጣት፣ ግብረ ገብ፣ ፍቅርና መተሳሰብ የጎደለው የብቸኝነትና የጥላቻ ሕይወት እንዲስፋፋ አድርጎታል ካሉ በኋላ፣ ዛሬ የምናየው የሰው ሕይወት በዋዛ ለሞት መዳረግ፣ የብዙ ቤተሰብ ዋይታ፣ ሐዘንና ስቃይ የዚሁ ውጤት ናቸው ብለዋል። የዘር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት እና የባሕል ልዩነቶችም ሳይቀሩ እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ። ነገር ግን የምንገኝበትን አስከፊ ጊዜ ተገንዝበን ያን ሁሉ ጥላቻንና መለያየትን አስወግደን፣ በአንድ ጥላ ሥር ሆነን ለፍቅር፣ ለሰላምና ለአንድነት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል በማለት አሳስበው ነበር።

ወደ ዛሬው ርዕሳችን ተመልሰን ስለ ምሕረት ስንናገር፣ ኑሮአችንን ሰላማዊ እና እውነተኛ ፍቅር በግልጽ የሚታይበት ለማድረግ፣ በመካከላችን ስምምነት እና መግባባት እንዲኖር ለማድረግ የሚያግዙን የተለያዩ መንገዶች እንዳሉ እናውቃለን። ከጥላቻ፣ ከቂም፣ ከመቀያየም እና ከመለያየት ይልቅ ስምምነት፣ መግባባት፣ መተጋገዝ፣ መተሳሰብ፣ ፍቅር እና ሰላም የነገሰበት እንዲሆን ለማድረግ ከሚያግዙን መንገዶች መካከል አንዱ የበደሉንን ይቅር ብለን ምሕረት ስናደርግ ነው። ብዙን ጊዜ የበደሉንን ይቅር ማለት ወይም ምሕረትን ማድረግ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ነገር ግን ቅዱስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው “እነሆ ሰላምን በይቅርታ እና በምሕረት ጎዳና ላይ ፈልጓት፣ ታገኟታላችሁ” ብለው እንደ ነበር ይታወሳል። ምሕረት በእግዚአብሔር የድነት ሥራ ተካፋዮች የሚያደርገን ተግባር ነው። እግዚአብሔር ለበደላችን ወይም ለኃጢአታችን ዘለዓለማዊ ምሕረት የምናገኝበትን መንገድ ሲያዘጋጅ ልጁን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም ልኮት፣ ምንም ጥፋት ሳይገኝበት፣ እኛ ለሠራነው ኃጢአት እርሱ እንደ ወንጀለኛ በመቆጠር፣ በመገረፍ፣ በጦር ትወግቶ በመሰቃየት፣ ልብሶችን ተገፎ በመዋረድ፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት አደረገው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአታችን ይቅርታን እና ምሕረትን በማስገኘት የመጀመሪያ ምሳሌ ሆነ። ምሕረትን ማድረግ አስፈላጊነት እንደሆነ ሕዝቡንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ እያለ ያስተምር ነበር። ምሕረትን የሚያደርጉ ፥ ምሕረትን ስለሚያገኙ ደስ ይበላቸው። (በማቴ. ወንጌል ምዕ. ፭ ቁጥር ፯) በዚያው ምዕራፍ በቁጥር ፱ ላይ፥ በሰዎች መካከል እርቅና ሰላምን የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ ደስ ይበላቸው። እንግዲህ የተወደዳችሁ የዚህ መልዕክት ተካፋይ የሆናችሁ በሙሉ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ምሕረትን ያገኘን ሁላችን፣ እርሱ ባሳየን መንገድ በመጓዝ የበደሉንን ይቅር ብለን ምሕረትን ማድረግ ይኖርብናል። ልባችንም ምሕረትንና እርቅን እንጂ በቀልን የሚፈልግ እንዳይሆን የምሕረት አባት ወደ ሆነው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ጸሎታችንን እናቀርባለን።








All the contents on this site are copyrighted ©.