2017-01-31 11:46:00

የጥር 21/2009 ዓ.ም. እለተ ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር በክቡር አባ ገብረመስቀል ሽኩር።


“ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል ምክንያቱም እግዚኣብሔር ትልቅ ነገር አድርጎልኛልና” (ሉቃስ 1.46-56)

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሰዎች ሁሉ!

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ የእግዚኣብሔር ፍቅርና የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችሁ ጋር ይሁን! አሜን!!

የዛሬ ሰንበት ከሰንበትነቱ ባሻገር የአስተርዮ ማሪያም አመታዊ ክብረ በዓል ይከበራል። በአመት ውስጥ ከምናከብራቸው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ክብረ በዓላት ውስጥ አንዱ ነው። የዛሬ በዓል የሚያስታውሰን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያምን እርፍት (ሞት) ነው። እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም አልሞተችም ግን ምድራዊ ሕይወቱዋን ጨርሳ አንቀላፍታለች። ሥጋዋ መበስበስ ሳይደርስበት በልጁዋ አማካይነት በነፍስ እና በሥጋ ወደ ሰማይ ተወስዳለች ወይም ፈለሰች የሚል ነው።

የእዚህን ቃለ እግዚኣብሔር ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ይህ ትምሕርት እና እምነት ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እየታመነ እና እየተከበረ  የዘለቀ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1950 ዓ.ም. በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ፒዮ 12ኛ የእመቤታችን ፍልሰታ (በነብስ እና በሥጋ) ወደ ሰማይ የወጣችበትን የእምነታችን እውነተኛ አስተምህሮ (Dogma) አድርገው ደነገጉት።

የኢትዮጲያ ክርስትና እምነት ትውፊት ስለዚህ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ሞት እና ፍለሰት እውነትነት ሲናገር፣ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በሞተች ጊዜ አይሁዶች የእመቤታችንን አስክሬን ከሐዋሪያት ለመውሰድ ፈልገው ነበረ። ምክንያቱም እርሱዋም እንደ ልጁዋ ከሞት ትነሳለች ተብሎ ውዥንብር እንዳይነሳ በመፍራት ነበር ይህንን ያደረጉት። ነገር ግን የእመቤታችን አስክሬን ተሰወረ። ስለ እዚህም ሐዋሪያት የተከሰተው ነገር ሚስጢር እንዲገለጽላቸው ሁለት ሱባሄ ውይም 15 ቀን በጸሎት ተጉ። በመጨረሻም እመቤታችን በመላዕክት ወደ ሰማይ መወሰዱዋን የሚያሳይ ራዕይ ያያሉ በእዚህም ራዕይ እመቤታችን በሥጋና በነፍስ ወደ ሰማይ መፍለሱዋን ይረዳሉ” ሲል ያስረዳናል።

ለእዚህም ነው የነሐሴ የፍልሰታ ጾም ሱባሄ እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ፍልሰታ በዓል የአስራ አምስት ቀናት የሱባኤ ዝግጅት የሚደረገው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በሥጋ እና በነብስ ወደ ሰማይ ተወስዳለች። ሌላው የዛሬው በዓል መጠርያ “አስትርዮ” ይባላል። አስትርዮ ማሪያም የተባለበት ምክንያት ይህ በዓል የሚከበርበት ወቅት የአስትርዮ ወቅት ስለሆነ ነው። አስትርዮ ማለት ግልጸት ማለት ነው።

በስርዐተ አምልኮኋችን መሰረት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውልደት ማለትም ከገና በዓል ቡኋላ እስከ ተጠመቀበት የጥምቀት በዓል ድረስ ያለው ወቅት የአስተርዮ ወይም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ግልጸት የሚከበርበት ወቅት ነው።

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ወቅት እግዚኣብሔር አብ “ይህ የምወደው ልጄ ነው!” በማለት የኢየሱስን ማንነትም ገለጸ። በቀጣዩ እለትም በቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ በመለወጥ ክብሩን ገለጸ። በቀጣዮቹ ሳምንታት ደግሞ በተለያዩ ምልክቶች ማንነቱን እና ተልዕኮውን የገለጸበት ሁኔታም ታይቱዋል። ስለ እዚህም በእዚህ ወቅት የሚከበረው የእመቤታችን ቅድስ ድንግል ማሪያም በዓል አስተርዮ ማሪያም እንለዋለን እንጅ የምንዘክረው ግን ሞቱዋን (እረፍቱዋን) ነው።

በስርዓተ አምልኮዋችን የምናከብራቸው በዓላት ሁሉ ከመሰረታዊ የክርስትና እምነት ጋር የተያያዙና እምነታችንን የሚያጠናክሩ ናቸው። የእመቤታችን እርፍት እና ፍለሰት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ያለንን እምነት እና እኛም በመጨረሻው ቀን ከሙታን እንደ ምንነሣ ያስታውሰናል። ጸሎተ ሐይማኖታችን “በሙታን ትንሣኤና በዘላለም ሕይወት ተስፋ አደርጋለሁ!” ይለል። የእመቤታችን ሕይወት ይህንን ተስፋችን እና እምነታችን የሚያረጋግጥ እና የሚያብራራ ነው። ምድራዊ ሕይወትን ጨርሳ በነፍስ እና በሥጋ ወደ ዘላለም ሕይወት በክብር ተወሰደች።

እንደ ካቶሊክ እምነት እና ወግ መሰረት በምንደግመው በመቁጠሪያ ጸሎት አራተኛው የክብር ሚስጢር ላይ ይህንን የእመቤታችንን ሚስጢር የሚያስታውሰን ነው።  ዛሬ ይህንን የአስተርዮ ማሪያም ዓመታዊ ክብረ በዓልን ስናከብር የተነበበውን የወንጌል ቃል ተፈጻሚ እንዲሆን እናደርጋለን ማለት ነው። እኛም በዘመናችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን ብጽዕት ነሽ ብለን እናወድስታለን። “ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ነሽ ይሉኛል ምክንያቱም ታላቁ እግዚኣብሔር በእኔ ታላቅ ነገርን አድርጎልኛልና”።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በእዚህ መልኩ የተለያዩ በዓልት ላይ የምንዘክራት እና ብጽዕት ነሽ የምንላት እግዚኣብሔር በእርሱዋ ባደረገው ትልቅ ነገር ምክንያት ነው። ይሄውም የልጁ እናት እንድትሆን እና የደኅንነት እቅዱ ተካፋይ እንድትሆን እግዚኣብሔር ስላደረጋት ጭምርም ነው። ከማሪያም ቃል ሥጋን ለበሰ።  እግዛኢብሔር ስለመረጣት እና ስለ አከበራት እኛም እናከብራታለን። እግዚኣብሔር የከበረውን ማክበር ማለት እግዚኣብሔር ራሱን ማክበር ማለት ነው። ከዛሬ ወንጌል አንድ አንድ ነብጥቦች ለራሳችን መንፈሳዊ አስተንትኖ ይሆን ዘንድ መጥቀስ እፈልጋለሁኝ።

የእመቤታችን የምስጋና ጸሎት! እመቤታችን የወገኖቹዋን ፈለግ በመከተል (1ሳሙ. 2.1-10) ያለፈውን ታሪኳን በመዘርዘር ያለችበትን ሁኔታ እና የወደፊት ተስፋዋን በመመልከት እግዚኣብሔርን ታመሰግነዋለች፣ የምስጋና ሊጣኒያም ትዘረዝራለች። ይህ የማሪያ ጸሎት በሁለተኛው ሳሙኤል 2. 1-10 እናገኘዋልን። ሀና ያደረገች ጸሎት ማለት ነው። በእዚህ ሁኔታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በትህትና በእግዚኣብሔር ፊት ትቀርባለች ምስጋናውዋን ታቀርባለች። እኛም በታሪካችን ውስጥ ውጣ ወረድ ቢገጥመንም ቅሉ እግዚኣብሔር ግን ቃሉን አይረሳም። ስንወድቅ ያነሳናል፣ ብንታበይ ግን እንወድቃለን። እግዚኣብሔር ግን ቃሉን የሚጠብቅ አምላክ ነው። እመቤታችን ቅድስት ማሪያም በምስጋና ጸሎቱዋ የእግዚኣብሔርን ባሕሪ ቁልጭ አድርጋ ታሳያለች፣ የወደቁትን የሚያነሣ፣ በታሪካችን እና በሕይወታችን የሚሠራ አምላክ ነው።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ ምን እንማራለን?

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን!! አሜን!!








All the contents on this site are copyrighted ©.