2017-01-26 11:36:00

የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ማለት ፈጽሞ በአምላክ ላይ አለማጉረምረም ማለት አይደለም!


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በጥር 16/2009 ዓ.ም. በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ባሰሙት ስብከት የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ማለት ፈጽሞ በአምላክ ላይ አለማጉረምረም ማለት አይደለም ማለታቸው ተገለጸ።

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለታደሙ ካህናት፣ ደናግላንና ምዕመናን ባሰሙት ስብከት  አጽኖት ሰጥተው እንደ ገለጹት ከእግዚኣብሔር ጋር ያለን ግንኙነት በእውነት ላይ የተመሰረት መሆን እንዳለበት ጠቅሰው “እነሆ አለሁኝ!” በምንልበት ወቅቶች ሁሉ በእውነት የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ተዘጋጅተን መሆን እንዳለበትም ጨምረው ገልጸዋል።

በእለቱ በተነበበውና ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ዕብራዊያን (10.1-10) በጻፈው መልዕክቱ በተወሰደው ምንባብ ላይ ተመርኩዘው ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ወደ እዚህ ምድር በመጣበት ወቅት “መሥዋዕትንና መባን አልፈልግም ሰውነትህን ግን አዘጋጅልኝ፣ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኋጢያት ስርየት በሚሰዋ መሥዋዕት አልተደሰትህም፣ ስለ እዚህም ‘አምላኬ ሆይ! በመጽሐፍ ስለ እኔ እንደ ተጻፈ ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁኝ’ አልኩኝ” ብሎ እንደ ነበረ ጠቅሰዋል።

“ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ!” የሚለው የኢየሱስ ቃል ከደኅንነት ታሪካችን ጋር የተያያዘ መሆኑን በመግልጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በታሪክ ሂደት ውስጥ ለእግዚኣብሔር ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ እንደ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ኤሊያስ፣ ኢሳያስ፣ ኤርሚያስ የመሳሰሉ ታላላቅ ነቢያት እንደ ነበሩ አስታውሰው “እነሆ እንዳልከኝ ይሁንልኝ” እስካለችሁ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምና በመጨረሻም ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ እስካለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድረስ ይህ አዎንታዊ ምላሽ ቀጥሎ እንደ ነበረም ገልጸዋል።

እነዚህ ነብያት የእግዚኣብሔርን ጥሪ ቅጽበታዊ በሆነ መልኩ የተቀበሉ ሰዎች ሳይሆኑ ነገር ግን ጥሪያቸው ከእግዚኣብሔር ጋር በነበራቸው ቀጣይ ውይይት ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ በመጠቅስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እግዚኣብሔር ማንኛውንም ሰው ከመላኩ በፊት በቅድሚያ በትዕግስ እንደ ሚደራደርም ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው ይህንን አሳባቸውን ለማጽናት በማሰብ እግዚኣብሔር ከኢዩብ ጋር ያደርገውን ተከታታይ ውይይት በዋቢነት የጠቀሱ ሲሆን ኢዮብ በሕይወቱ ውስጥ እየተከሰቱ የነበሩ ነገሮችን ባለመረዳቱ የተነሳ እግዚኣብሔር በታላቅ ትዕግስት ለእዮብ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ትክክለኛውን ጎዳና እንዲይዝ አድርጎት እንደ ነበረም ጠቅሰው ኢዮብም በመጨረሻ ይህንን አቅ በተረዳበት ወቅት “አምላኬ ሆይ! አንተ ሁሌም ትክክል ነህ፣  በድምጽህ ብቻ ነበር የማውቅህ፣ ነገር ግን አሁን አየውህ፣ ፈቃድህን ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ! ብሎ እንደ መለሰለትም አብራርተዋል።

“የክርስቲያኖች ሕይወትም ፈቃድህን ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ!” ከሚለው ሀረግ ሊጀምር ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም በቀጣይነት የእግዚኣብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ዝግጁ መሆናችንን ያሳያል ብለዋል።

እኛ ‘ፈቃድህን ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ!’ ብለን እስክንመልስ ድረስ አምላካችን ጥሪውን ዘወትር ከማቅረብ አይታክትም ያሉት ቅዱስነታቸው እግዚኣብሔር ለሚያቀርብልን ጥሪዎች ሁሉ መልስ በመስጠት ከእርሱ ጋር መነጋገር መቻል ይኖርብናል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ እንደ ገለጹት “ብዙን ጊዜ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው ‘በአብዛኛው በሚጸልዩበት ወቅቶች ሁሉ በእግዚኣብሔር ላይ እንደ ሚናደዱ ይነግሩኛል’ ያሉት ቅዱስነታቸው እኔም በእግዚኣብሔር ፊት በምትሆኑበት ወቅቶች ሁሉ የሚሰማችሁን ሁሉ ንገሩት ምክንያቱም እርሱ አባት ስለ ሆነ በትዕግስት ያዳምጣችኋል’ ብዬ እመልስላቸዋለው ካሉ ቡኋላ ስሜታችንን ከመደበቅ ይልቅ ወይም ደግሞ አስመሳይ ከመሆን ይልቅ ፈቃድህን ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ! በማለት የጌታን ፈቃድ በሕይወታችን ለመፈጸም መትጋት ይኖርብናል ብለው ይህንንም መተግበር እንድንችል “መንፈስ ቅዱስ ፀጋውን አብዝቶ ይስጠን” ካሉ ቡኋላ ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.