2017-01-03 10:17:00

ር.ሊ.ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቱርክ በደረሰው የአሸባሪዎች ጥቃት ነብሳቸውን ላጡ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ሐዘን እንደ ተሰማቸው ገለጹ።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በታኅሣሥ 23/2009 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመልዕከ እግዚኣብሔር ጸሎት ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር የተከበረውን አዲስ ዓመት እና 50ኛውን የዓለም የሰላም ቀንን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክታቸው እንደ ገለጹት በአዲስ ዓመት ዋዜማ በቱርክ በደረሰው የአሸባሪዎች ጥቃት ነብሳቸውን ላጡ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ሐዘን እንደ ተሰማቸው መግለጻቸው ታውቁዋል።

በእዚህ በቱርክ በደረሰው የአሸባሪዎች ጥቃት 39 ሰዎች ነብሳቸውን ማጣታቸው እና ከ60 በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ቆስለው በእየ ሆስፒታሉ እንደ ሚገኙም የታወቀ ሲሆን ይህንንም ድርጊት ትኩረት ባደረገው መልዕክታቸው ቅዱነታቸው እንደ ገለጹት “ያለ መታደል ሆኖ በዛሬው ምሽት ነውጠኞች በፈጠሩት አደጋ የእንኳን አደረሳችሁ እና  የተስፋ መልእክት በሚተላለፍበት እለት ይህ አደጋ መድረሱ በጣም ያሳዝናል” ካሉ ቡኋላ የእዚህ አደጋ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ሐዘን እንደ ሚጋሩም ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው እንደ ገለጹት በብጹዕ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ አነሳሽነት የዓለም የሰላም ቀን ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት መከበር መጀመሩን አስታውሰው የእዚህ በዓል ዋንኛው ዓላማ “ሰላማዊ የሆነ እና የወንድማማችነት ስሜት የሰፈነበት ዓለም ለመመስረት ሁሉም የራሱን ድርሻ ይወጥ” በሚል ዓላማ ያነገበ በዓል እንደ ሆነም ጨምረው ገልጸዋል።

“ነውጥ አልባ የሆነ እንቅስቃሴ ለሰላማዊ ፖሌቲካ” አስፈላጊ መሆኑን በአጽኖት የገለጹት ቅዱስነታቸው እንደ ጎርጎሮሳዊያን የቀን አቆጣጠር የተከበረው አዲስ አመት የሰላም እና የጤና እንዲሆን ተመኝተው ይህ አዲሱ አመት በሰላም ሊጠንቀቅ የሚችለው እያንዳንዳችን በምናደርገው ጥረት እና በእግዚኣብሔር ድጋፍ ላይ ተመርኩዘን ነው ካሉ ቡኋላ እያንዳንዳችንም በእግዚኣብሔር ኋይል ተደግፈን በእየለቱ መልካም ነገሮችን ለማከናወን መትጋት ይኖርብናል ሰላም ሊመጣ የሚችለውም በእዚሁ መንገድ ብቻ ነው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በእለቱ ከአዲስ አመት በዓል ጋር ተያይዞ በተከበረው ማሪያም የእግዚኣብሔር እናት የተሰኘውን በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው እንደ ገለጹት ማሪያም ለእግዚኣብሔር የደኅንነት ሚስጢር ተባባሪ ነበረች ካሉ ቡኋላ “ትዕቢተኞችን ከእነ ሐሳባቸው በትኖዋቸዋል፣ ታላላቅ ግዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዱዋቸዋል” ትሁት የሆነችውን እናት ግን በክብር ከፍ አድርጉዋታል” ብለዋል።

“የእግዚኣብሔር ልጅ እናት ለሆንሽው ማሪያም ምስጋና ይግባሽ! የእግዚኣብሔርን ቀልብ ለሳበው ትህትናሽ እናመሰግንሻለን፣ በእመነት ቅሉን አምነሽ ስለ ተቀበልሽ እናመሰግንሻለን፣ እንዳልከኝ ይሁንልኝ በማለት ላሳየሽው ብርታት እናመሰግንሻለን፣ የማሪያም ልጅ የሆንከው ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እናመሰግንሀለን፣ በሰላም መንገድ ላይ መመላለስ እንድንችል እርዳን” ካሉ ቡኋላ ለምዕመናን ቡራኬን ሰጥተው እና መልካም አዲስ አመትን ተመኝተው መሰናበታቸው ታውቁዋል።  

 








All the contents on this site are copyrighted ©.