2016-12-17 12:02:00

የታኅሣሥስ 9/2009 ዓ.ም. የእለተ ሰንበት የመጻሐፍ ቅዱስ ምንባባት።


ወደ ዕብራዊያን ሰዎች የተላከ መልዕክት ምዕራፍ 1: 1-14

1እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ 2በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። 3እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራ ቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዞአል፤ የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ። 4ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ፣ እርሱም ከመላእክት እጅግ የላቀ ሆኖአል።

5እግዚአብሔር፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤” ወይስ ደግሞ፣ “እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? 6ደግሞም እግዚአብሔር በኵሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ፣ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት” ይላል። 7ስለ መላእክትም ሲናገር፣ “መላእክቱን ነፋሳት፣ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል።

8ስለ ልጁ ግን እንዲህ ይላል፤ “አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ጽድቅም የመንግሥትህ በትር ይሆናል፤ 9ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከባልንጀሮችህ በላይ አስቀመጠህ፣ የደስታንም ዘይት ቀባህ።”

10ደግሞም እንዲህ ይላል፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በመጀመሪያ የምድርን መሠረት አኖርህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። 11እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ 12እንደ መጐናጸፊያ ትጠቀልላቸዋለህ፤ እንደ ልብስም ይለወጣሉ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።”

13እግዚአብሔር፣ “ጠላቶችህን የእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? 14መላእክት ሁሉ መዳንን የሚወርሱትን ለማገልገል የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን?።

 

2ኛው የሐዋሪያው ጴጥሮስ መልዕክት ምዕራፍ 3:1-9

የጌታ ቀን

1ወዳጆች ሆይ፤ ይህ አሁን የምጽፍላችሁ ሁለተኛው መልእክት ነው። ሁለቱንም መልእክቶች የጻፍሁላችሁ ቅን ልቦናችሁን እንድታነቃቁ ለማሳሰብ ነው፤ 2ደግሞም ቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል እንዲሁም በሐዋርያት አማካይነት በጌታችንና በአዳኛችን የተሰጠውን ትእዛዝ እንድታስቡ ነው።

3ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ዕወቁ፤ በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። 4እነርሱም፣ “ ‘እመጣለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል” ይላሉ። 5ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ሰማያት ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ቃል ተፈጥረው እንደሚኖሩ፣ መሬትም በውሃ መካከልና በውሃም እንደ ተሠራች ሆን ብለው ይክዳሉ፤ 6በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ። 7በዚያው ቃል ደግሞ አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር፣ ኀጢአተኞች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀዋል።

8ወዳጆች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር አትርሱ። 9አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል።

 

የዩሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1:44-51

ኢየሱስ ፊልጶስንና ናትናኤልን ጠራቸው

43በማግሥቱ፣ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አግኝቶ፣ “ተከተለኝ” አለው። 44ፊልጶስም እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ ሁሉ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። 45ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፣ “ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስን አግኝተነዋል” አለው።

46ናትናኤልም፣ “ከናዝሬት በጎ ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለ። ፊልጶስም፣ “መጥተህ እይ” አለው። 47ኢየሱስም፣ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ፣ “እነሆ፤ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” አለ።48ናትናኤልም “እንዴት አወቅኸኝ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ፣ ገና ፊሊጶስ ሳይጠራህ አየሁህ” ሲል መለሰለት።

49ናትናኤልም መልሶ፣ “ረቢ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለ።50ኢየሱስም፣ “ያመንኸው ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስላልሁህ ነውን? ገና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ” አለው፤51ጨምሮም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ተከፍቶ፣ የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።

 

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.