2016-12-15 11:13:00

ቅዱስነታቸው ዓለማችን እያጣች ያለውን “ነውጥ አልባ” የሆነ የፖለቲካ ባሕል መልሳ ትጎናጸፍ ዘንድ መትጋት እንደ ሚገባ ገለጹ።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በትላንትናው እለት ማለትም በታኅሣሥ 3/2009 ዓ.ም. ለዓለም የፖለቲካ ኋይሎች ባስተላለፉት የሰላም መልዕክት ዓለማችን እያጣች ያለውን “ነውጥ አልባ” የሆነ የፖለቲካ ባሕል መልሳ ትጎናጸፍ  ዘንድ ጥሪ አድርገው ለግጭቶች ወታደራዊ ምላሽ መስጠት ግጭቶችን የባሰ ከማፋፋም የዘለለ ፋይዳ እንደ ሌለውም ጭምረው አሳስበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ይህንን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ባለፈው ሰኞ እለት ሲሆን ይህም በመጭው ታኅሣሥ 23/2009 ዓ.ም. የዛሬ 50 ዓመት ገደማ በጊዜው የነበሩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ  ዓለማቀፍ የሰላም ቀን ይከበር ዘንድ ጥሪ ባደርጉት መሰረት ሲሆን ቅዱስነታቸው ይህ አሁን ያስተላለፉት የሰላም ጥሪ ይህንን የሰላም ጥሪን የማስቀጠል ባሕልን ተከትሎ የተተገበረና የእዚህን የሰላም ጥሪ 50ኛ ዓመትን ለመዘከር ታስቦ የተላለፈ የሰላም መልዕክት መሆኑም ጨምሮ ተግልጹዋል።

ቅዱስነታቸው በእዚህ መልዕክታቸው ለፓሌቲካ፣ ለሐይማኖት መሪዎች፣ ለዓለማቀፍ እና ለንግድ ተቋማት፣ በተለይም ደግሞ ለመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ ባስተላለፉት መልዕክታቸው እንደ ገለጹት እነዚህ ሁሉ አካላት የእርቅ መሳሪያዎች በመሆንና “ነውጥ አልባ የሆነ” ፖሌቲካ በመጠቀም ለሰላም መስፈን ጥሪ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ካሉ ቡኋላ ዓለማችን ቀስ በቀስ አሰቃቂ ወደ ሆነ ጦርነት እየገባች ነው ይህም አሰቃቂ ነውጥ በጥላቻ ለቆሰለው ዓለማችን በፍጹም መድኋኒት ሊሆን አይችልም ብለዋል።

ነውጥ አሉ ቅዱስነታቸው ነውጥ ሰዎችን ወደ አለተፈለገ ስደትና በቃላት ሊገለጽ ወደ ማይችል መከራ፣ የስነ-ምዕዳር ውድመት፣ ሽብርተኝነት እና የተቀናጀ ወንጄል ወደ የመሳሰሉት እንዲፈጠሩ ያደርጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም ግጭት በአጸፋው ጥቂት የሚባሉ የዓለማችን አበጋዞችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ብዙኋኑን የማኅበረሰብ ክፍል ለከፍተኛ ስቃይን እና መከራ ይዳርጋል ብለዋል።

ነገር ግን አሉ ቅዱስነታቸው ነገር ግን ኢየሱስ ያሳየን ጎዳና ከእዚህ በፍጹም የተለየ ነበር ያሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ራሱ ነውጥ አላባ የሆነ መንገድን በመከተል የእርቅ መሳሪያ ሆኖ እንደ ነበረም ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በታሪክ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ነውጥ አልባ ንቅናቄዎችን አድርገው አልፈዋል ያሉዋቸውን ቅድስት እማሆይ ትሬዛን፣ ማተመ ጋንዲን እና ማሪቲን ሉተር ኪንግን የመሳሰሉ የነውጥ አልባ ንቅናቄዎች እንዲተገበሩ ያደረጉ ሰዎች መሆናቸውን በማሳያነት የጠቀሱት ቅዱስነታቸው ነውጥ አልባ ንቅናቄዎች በነውጥ ከተሞሉ እንቅስቃሴዎች አኳያ ሲታዩ በጣም አመሪቂ ሊባል የሚችል ለውጥ አስገኝተው እንደ ነበር ጨምረው ገልጸዋል።

በእዚህም ረገድ የክርስቲያን ማኅበራት እውነትን እና ፍትህን መሳሪያ አድርገው በመጠቀም የኮሚኒዚም አገዛዝ  እንዲንኮታኮት በማድረግ ሰላማዊ የፖሌቲካ ሽግግር እንዲኖር ማስቻላቸው ታላቅ ታሪካዊ ምሳሌ እንደ ሆነ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው ይህ ታላቅ ምሳሌያዊ ለውጥ እንዲመጣ ያስቻለችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳትሆን ሁሉም የእምነት ተቋማት ባደረጉት ርብርብ መሆኑንም ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

“እኔ በአጽንዖት ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ነገር ማንኛውም የሐይማኖት ተቋም አሸባሪ አለመሆኑን ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው “የእግዚኣብሔርን ስም ተጠቅሞ ነውጥ ማካሄድ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው” ብለዋል።

ነውጥ አላባ የሆነ የፖሌቲካ ሥር መሰረት አስፈላጊ መሆኑን በመልዕክታቸው አጽኖት ሰጥተው የገለጹት ቅዱስነታቸው ትጥቅ የታጠቁ ሰዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ እገዳን መጣል፣ በተለይም ደግሞ በኒውክለር ኋይል የሚሰሩ የጦር መሳሪያዎችን ከነጭራሹ በፍጥነት ማገድ እንደ ሚገባ ጠቅሰው በእዚህም ረገድ ብቻ ነው ሴቶችን እና ሕፃናትን ለስቃይ እየዳረገ የሚገኘውን አከባቢያዊ የሆኑ ግጭቶች ማብቂያ እዲያገኙ ማድረግ የሚቻለው ብለዋል።

ለፖሌቲካ፣ ለሐይማኖት እና ለኢኮኖሚያዊ ተቋማት ዛሬ የማቀርብላቸው ጥሪ ማኅበረሰብን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ተሳታፊ ይሆን ዘንድ እና ንግድን በማስፋፋት፣ የሰላም መሳሪያዎች በመሆን፣ ኅብረትን በመፍጠር፣ ታሪክ ይሠሩ ዘንድ ጥሪየን አቀርባለሁ በማለት አጽኖት ሰጥተው በመልዕክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ሁሉም ነገር በተገናኘበት ወይም በተሳሰረበት ዓለማችን፣ በሕብረት ነውጥ አልባ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን ግጭቶችን ከማስወገድ ባሻገር የበለጠ ኋይል ስለሚሰጥ እና ወጤታማ ሰለሚያደርግ  ይህንን ገንቢ የሆነ አካሄድ በመተግበር “ነውጥ አልባ” እንቅስቃሴ ከሚያመጣው ለውጥ ሁላችንም ተጠቃሚ መሆን እንችላለን ብለዋል።

“ሁላችንም ብንሆን ሰላም ያስፈልገናል” ያሉት ቅዱስነታቸው “እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በሚመጣው የ2017 ዓ.ም. ራሳችንን ለጸሎት በማስገዛት ግጭቶችን ከልባችን፣ ከቃላችን እንዲሁም ከተግባራችን በማስወገድ ሁላችንም የሰላም ተዋኒያን መሆን እንችላለን” ብለዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅታችን ተከታታዮች ቅዱስ አባታችን የዓለም የሰላም ቀንን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት ሙሉ ይዘቱን ከመጭው አርብ ማለትም ከታኅሣሥ 7/2009 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ሰለምንቀርብላችሁ እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።








All the contents on this site are copyrighted ©.