2016-12-02 09:22:00

በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ደሴ ሀገረ ስብከት 300 ሰዎችን ማጥመቁ ተገለጸ።


በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ደሴ ሀገረ ስብከት በኅዳር 18/2009 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በኤራዊ ክልል ውስጥ የሚገኙ 300 የጉሙዝ ተወላጆችን የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ በተገኙበት የታምራዊ መዳሊያ በዓል በተከበረበት ዕለት መጠመቃቸው ተገለጸ። እነዚህ አዲስ የተጠመቁ ምዕመናን የክርስትናን እምነትን ከመቀበላቸው በፊት የባሕላዊ አምልኮን ይከተሉ እንደ ነበረ የታወቀ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ባኑሽ ከሚባለው ከአዲስ አበባ 600 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኘው ስፍራ የመጡ መሆናቸው ታውቁዋል።

ከጥመቀት ስነ-ስርዓት ባሻገር የቀብር ቦታ ቡራኬ በሀገረ ስብከቱ ጳጳስ አቡነ ልሳነ-ክርስቶስ የተከናወነ ሲሆን አዲስ በተባረከው የመካነ መቃብር ስፍራም መስቀል የማቆም ስነ-ስርዓትም መከናወኑም ታውቁዋል። በእለቱ ክቡር አቡነ ልሳነ ክርስቶስ በስብከታቸው “እግዚኣብሔር ታላቅ ነው፣ እግዚኣብሔር የሁሉም አባት ነው፣ አባታችን የሚለውን ጸሎት በመላው ዓለም የሚገኙ ምዕመናን በሚጸልዩበት ወቅት እግዚኣብሔር የሁላችን አባት መሆኑን እና ሁላችንንም በእኩልነት እንደ ፈጠረ እንመሰክራለን። ዛሬ ይህንን ታላቅ የጥምቀት ሚስጢር በተቀበላችሁበት ወቅት የእግዚብሔር ልጆች ሁናችኋል፣ የቤተ ክርስቲያን አባሎች ለመሆን በመብቃታችሁ በሰማይ እንዲሁም በምድር ለምትገኘው ለመላው ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ደስታ ነው” ብለው እንደ ነበረም ታውቁዋል።

በእለቱ የተጠመቁ 300 ምዕመናን የክርስትናን እምነት እንዲቀበሉ ምስክር የሆናቸው ታከለ የተባለ አንድ የካቶሊክ ወጣት ምዕመን መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ይህ ወጣት እነዚህን ማለትም አሁን የተጠመቁትን 300 ሰዎችን በማስተማር እና ምስክር በመሆን የክርስትናን እምነት ይቀበሉ ዘንድ መነሳሳትን ከፈጠረባቸው ቡኋላ ይህንንም ፍላጎታቸውን ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች በማስታወቁ በቂ ዝግጅት ከተደረገ ቡኋላ እነሆ በዛሬው እለት ለታላቁ የጥምቀት ሚስጢር በቅተዋል ብለዋል።  

ብጹዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ በእለቱ ባደረጉት ንግግር በቤንሻንጉል ክልል ለመጠመቅ እዱሉን ያላገኙ ብዙ ሰዎች በመኖራቸው የተነሳ ወንጌልን የማስፋፋቱ ተግባር በቀጣይነት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

“የአንድ ሰው ምስክርነት 300 ሰዎች እንዲጠመቁ በማድረግ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባል በመሆን የእግዚኣብሔርን ቤት እንዲቀላቀሉ አድርጉዋል። ይሁን እንጂ  መልካም ዜናውን የመስማት እድል  እስካሁን ያላገኙ  ብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ስለሚገኙ በእግዚኣብሔር ፀጋ ተደግፈን የእግዚኣብሔር ብርሃን የበራላቸው ዘንድና መልካም ዜናው ይስፋፋ ዘንድ መትጋት ይኖርብናል” አቡነ ልሳነ ማለታቸውም ተገልጹዋል።

የባህር ዳር ደሴ ሀገረ ስብከት በኢትዮጲያ ከሚገኙ አገረስብከቶች በመቡኋላ የተመሰረት አዲስ ሀገረ ስብከት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ500 በላይ የሚሆኑ ለሚስጢረ ጥምቀት እየተዘጋጁ የሚገኙ ሰዎች እንዳሉም የተገለጸ ሲሆን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የዛሬ 15 ዓመት ገደማ መንፈሳዊ አግልግሎቷን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መጀመሩዋም የታወቀ ሲሆን በጊዜው ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት የተጀመረው 3 የኮንቦኒ ማህበር ደናግላን በነበሩት ሲስተር ጃሚለቲ፣ ሲስተር ቲልዳ እና ሲስተር በርቴላ የሚባሉ ደናግላን በዘሩት የወንጌል ዘር እንደ ነበረና እነዚህም ደናግላን ማንዱራ በሚባል አከባቢ ስብከተ ወንጌልን ለማካሄድ በቀዳሚነት ተገኝተው እንደ ነበረም ለመረዳት ተችልኋል።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.