2016-11-30 13:33:00

ቅዱስነታቸው ክርስቲያኖች ትርዒታዊ የሆነ ትሕትናን በማስወገድ እንደ ሕፃናት እውነተኛውን ትህትናን መላበስ ይኖርባቸዋል አሉ


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በትላንትነው እለት ማለትም በኅዳር 20/2009 ዓ.ም. በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ካህናት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ባሰሙት ስብከት ክርስቲያኖች ትርዒታዊ የሆነ ትሕትናን በማስወገድ እንደ ሕፃናት ልጆች እውነተኛውን ትህትናን መላበስ ይኖርባቸዋል ማለታቸው ተገለጸ።

በእለቱ በተነበበው ከሉቃስ ወንጌል በተወሰደው ቃል ላይ ተመርኩዘው እግዚኣብሔር ራሱን የሚገልጸው ጥበበኛ ለሁኑና ለአዋቂ ሰዎች ሳይሆን ትሑትና እንደ ሕጻናት ለሆኑ ሰዎች ነው በሚለው ጭብጥ ላይ በማተኮር ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በእለቱ ከትንቢተ ኢሳያስ የተነበበው የመጀመሪያ ምንባብም ይህንኑ አቅ የሚያጠናክር እና ከአንድ የጦር አበጋዝ ዘር ሳይሆን በጣም ትንሽ ከሚባለው ከእሴይ ዘር ነፃ የሚወጣን ንጉሥ እንደ ሚመጣ የሚያሳስብ እንደ ነበረም ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸው ይህም በመጭው የገና በዓል ወቅት የታሪኩ ተዋኒያን የነበሩት ትንሽና ትሁት የሚባሉ ሰዎች መሆናቸው የሚያሳየው የጉዳዩን እውነተኛነት ነው ብለዋል።

“ስለዚህም በገና በዓል ይህንን ትንሽነት፣ እነዚህን ትንንሽ ነገሮችን ማለትም ትንሽ ልጅ፣ ጽናት ያለው፣ እናት፣ አባት. . .ወዘተ ሁሉም ትንሽ የሆኑ ነገሮችን እናያለን፣ ትልቅ ልብ አላቸው ነገር ግን ባሕሪያቸው እንደ ትንሽ ልጅ ነበር” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “የእግዚኣብሔር መንፈስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ በእዚህ ትንሽ ዘር ላይ በማረፉ ይህ ዘር የሕጻንነትንና የፈርሃ እግዚኣብሔርን ምግባር ተላብሶ እንደ ነበረም ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ይህ በገና የሚወለደው ሕጻን እግዚኣብሔርን በመፍራት የሚመላለስ መሆኑን ገልጸው እግዚኣብሔርን መፍራት ማለት በመሸበር መኖር ማለት አይደልም ነገር ግን ለአብርሃም የተሰጠውን የእግዚኣብሔር ትዕዛዛት መተግበር ማለት ነው ካሉ ቡኋል ይህም “ፍጹማን በመሆንና ከእርሱ ጋር በመኖር” እግዚኣብሔርን መፍራት፣ ትሑት መሆን ማለት ነው” ብለዋል።

የሕጻንነትን ባሕሪ መላበስ ትሕትናና እግዚኣብሔርን መፍራት ማለት ምን እንደ ሆነ በሚገባ እንድነረዳ ያስችለናል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ምክንያቱም በእግዚኣብሔር ፊት ስለሚመላለሱ፣ በእርሱም ስለሚታዩና ስለሚጠበቁ በተለይም ደግሞ እግዚኣብሔር ወደ ፊት እንዲጓዙ ብርታቱን እንደ ሚሰጣቸው ስለሚሰማቸው ይህም እውነተኛው ትሕትና ነው ብለዋል።

“ክርስቲያናዊ ትሕትና ማለት እግዚኣብሔርን መፍራት ማለት ነው፣ በድጋሜም ማለት እፈልጋለሁ እግዚኣብሔርን መፍራት ማለት ግን መሸበር ማለት አይደለም” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ነገር ግን አንተ እግዚኣብሔር ነህ፣ እኔ ደግሞ ሰው፣ የሕይወቴን ጥቂት ነገሮችን ይዤ በአንተ መንገድ እጓዛለሁ ነገር ግን የምጓዘው ከአንተ ጋር በመሆን እና ፍጹም ለመሆን በመሞከር ጭምር ነው” በትሕትና አምላክን ልንለው ይገባል ብለዋል። ትክክለኛ ትሕትና ማለት የሕጻናትን ባሕሪ መላበስ ማለት ነው እንጂ ትያትራዊ በሆነ መልኩ እኔ ትሑት ነኝ የሚሉትን አይመለከትም ካሉ ቡኋላ አንድ አንዴም እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች እኔ ትሑት ነኝ ይሉና ትሑት በመሆናቸው ደግሞ ይታበያሉ ይህ ደግሞ ትክክለኛ የትሕትና መግለጫ አይደለም ትክክለኛው ትሕትና የሕጻናትን ባሕሪ መላበስ ማለት ነው፣ በእግዚኣብሔር ፊት መመላለስ ነው፣ ስለሰዎች መጥፎ ነገር አለመናገር ማለት ነው፣ ራሳችንን እንደ ትንሽ አገልጋይ መቁጠር ማለት ነው ከእነዚ ነገሮች ነው የትሕትና ብርታት የሚመነጨው በማለት በአጽኖት ገልጸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ አሉ ቅዱስነታቸው እግዚኣብሔር ልጁን የላከላት ያቺ ወጣት ልጃገረድ ይህንን ፀጋ በተረዳችበት ወቅት በፍጥነት የክስቷ ልጅ ወደ ሆነችሁ ኤልሳቤጥ በሄደችበት ወቅት በሕይወቷ ስለተከሰተው ነገር ምንም መናገር እንዳልፈለገች ሁሉ ትክክለኝ ትሕትናም ይህንን ነው የሚመስለው እግዚኣብሔርን ተላብሶ በደስታ መመላለስ ነው ምክንያቱ በዛሬ ወንጌል እንደ ሰማነው ትሕትና ይህንኑ ነው የሚመስለው ብለዋል።

“እግዚኣብሔር ታላላቅ የሚባሉ ሚስጢሮችን ለትሑታን በመግለጹ የተነሳ ኢየሱስ በጣም ተደስቶ ነበር በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “የትሕትናን ጸጋ እግዚኣብሔር ለሁላችን እንዲሰጠን ልንጠይቅ ይገባል ካሉ ቡኋላ ይህም ፀጋ እርሱን እንድንፈራ፣ ከእርሱ ጋር ሆነን ወደ ፍጽምና ሕይወት እንድንጓዝ እግዚኣብሔርን ልንጠይቀው ይገባል ብለው የእዚህ ዓይነቱ ትሕትና ብቻ ነው በጸሎት እንድንተጋ የሚያደርገን፣ ወንድማማችነትን የሚገልጹ የፍቅር ተግባራትን በማከናወን መደሰት እና ማመስገን ይጠበቅብናል ካሉ ቡኋላ ስብከታቸውን አጠንቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.