2016-11-08 10:19:00

በመጀመሪያ የእግዚኣብሔርን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ ከእዚያን ሌላው ነገር ይጨመርላችኋል (ማቴ. 6.25-34)።


የጠበቀን የደገፈን፣ እንደ መልካም ተግባሮቻችን ሳይሆን በምሕረቱ ሁል ጊዜ በሚጎበኘን በእግዚኣብሔር ብርታትና ድግፍ ለዛሬው ቀን ስለደረስን ለእግዚኣብሔር አብ፣ ዓለምን እንዲያድን የተላከው ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም አጽናኝ ለሆነው ለመንፈስ ቅዱስ፣ በአጠቃላይም ለቅድስት ሥላሴ ምስጋና ክብር ለዘላለም ይሁን። አሜን!

ዛሬ የመድኋኔ ዓለም በዓልን እናከብራለን። መድኋኔ ዓለም የሚለው ቃል በድኋኔ በሚለው እና ዓለም በሚሉት ሁለት ቃላት የተዋቀረ ነው። ስለዚህም በይበልጥ ይህንን ጭብጥ በሚገባ ለመረዳት ያስችለን ዘንድ ሁሉቱን ቃላት ለያይተን ማያት ያስፈልጋል።

በመጀመሪያ መድኋኔ የሚለውን እንመልከት። የእዚህ ቃል ስር መሰረት መድኋኒት የሚለው ቃል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃል እንደ ሚያስረዳው መድኋኒት ማለት አዳኝ፣ በሥጋም በኩል ሆነ በመንፈስ በኩል ከማንኛቸውም ክፋትና ጉዳት የሚያድን ወይም የሚጠብቅ መድኋኒት አዳኝ፣ ታዳጊ ይባላል። በብሉይ ኪዳን እግዚኣብሔር የእስራኤል መድኋኒት ይባላል (ኢሳያስ 43.11, 45.21) ላይ እንደ ተጠቀሰው። በእግዚኣብሔር እየተመራ የእስራኤልን ሕዝብ ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነ ሰው አዳኝ ወይም ታዳጊ ይባላል። በቡልይ ኪዳን የተጠቀሱት ማሳፍንትና ነገሥታ እውነተኛ አዳኝ የሆነውን የክርስቶስ ምሳሌ ወይም ጥላ ነበሩ። ሁሉም በትንቢት መልክ ወደ ክርስቶስ አመለከቱ።

በአዲስ ኪዳን መዲኋኒት የሚለው ቃል በቀጥታ የሚያመልክተው ስለ እግዚኣብሔር አብ ወይ ስለክርስቶስ ብቻ ነው። (ሉቃስ 1.47, 1ጢሞ 1.1 ቲቶ 1.3) ማግኘት ይቻላል። ክርስቶስ ዓለምን ከኋጥያትና ከዘላለም ሞት ስላዳነ ምድኋኒት ይባላል። ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከኋጥያት እንዲያድን ወደ ዓለማችን ተላከ። ለእዚህም ነው እንግዲህ የክርስቶስ አዳኝነት ለሰው ልጆች ሁሉ ስለሆነ ክርስቶስ የዓለም መዳኒት (አዳኝ) የምንለው እና ይህንን በዓል ዛሬ የምንዘክረው።

በዩሐንስ ወንጌል 3.16 ላይ “እግዚኣብሔር ዓለምን እጅግ ስለወደደ አንድ ልጁን ሰጠን። ስለዚህ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይኖረዋል እንጂ አይጠፋም” ይለናል። ኢየሱስ የዓለም መድኋኒት ሆኖ ተልኮ ራሱን ለእኛ መስዋዕት በማድረግ አዳነን።

በሁለተኛነት የምንጋኘው ቃል ዓለም የሚለውን ነው።

ዓለም የሰው ልጆች የሚኖሩበት ሥፍራ ሲሆን በዚህ ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እንደየመልካቸው በሕሪያቸውም የተለያየ ነው። በተለይም ደግሞ አሁን በምንኖርበት ዓለማችን በፍጥነት እየተለወጡ የሚገኙ ነገሮችን እናያለ። በጣም ብዙ ሊባሉ የሚችሉ ሰዎች በጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ። በዓለማችን ብዙ መልካም ነገሮች እንደ ሚገኙ ሁሉ፣ ብዛት ያላቸው ክፋቶችንም የምታስተናግድ ሥፍራ በመሆኑዋ ምክንያት ነው ክርስቶስ አዳኝ ሆኖ ሊመጣ የቻለው።

በተለያዩ ምክንያቶች ከእግዚኣብሔር እንሸሻልን፣ እርስ በእርሳችን እንጋጫለን፣ ሰዎችን እንበድላለን፣ ክፋትን እንስባለን፣ በአጠቅላይ ዓለማችን የሰላም እና የጤና ቦታ መሆን ሲገባት የጥል እና የክርክር ሥፍራ ሆና ትገኛለች። ይህ ተግባራችን ደግሞ በቀዳሚነት የሚያሳምመን፣ የሚያሸብረን፣ እንቅልፍ የሚነሳን ወዘተ እኛ ራሳችንን ነው። የስህተታችን ሰለባ የምንሆነው ራሳችን ነን። ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በጻፈው ምልዕክቱ “ሰዎች ሁሉ ኋጥያትን ሠርተዋል እግዚኣብሔር የሰጣቸውን ክብር አጥተዋል። ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በፈጸመው የአዳኝነት ሥራ በእግዚኣብሔር ፀጋ ይጸድቃሉ። እግዚኣብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ምስዋዕት አድርጎ ያቀረበው በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ በደሙ የኋጥያታቸውን ይቅርታ እንዲያገኙ ነው” ይለናል ወደ ሮም ሰዎች 3.23,24።

ሁላችንም ኋጥያትን ስለፈጸምን የእግዚኣብሔር ክብር ጎሎናል የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ። ታዲያ ዛሬ ራሳችንን መጠየቅ የሚገባን ትልቁ ጥያቄ አጥያትን በመሥራታችን ምክንያት ያጣነውን የእግዚኣብሔር ጸጋ ወይም ክብር እንዴ ነው መልሰን መጎናጸፍ የምንችለው? በዛሬው የወንጌል ቃል ላይ እንደ ተጠቀሰው “ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን ብላችሁ አትጨነቁ ይልቁንም በመጀመሪያ የእግዚኣብሔርን መንግሥት እና ጽድቁን ፈልጉ ሌላው ነገር ይጨመርላችኋል” እንደ ሚለው ከምንኖርበት የጭቀት ሕይወት እንዴት ነው ተላቀን በሰላም እና በደስታ በቅድሚያ የእግዚኣብሔርን መንግሥት እና ጽድቁን መፈለግ የምንችለው እንዴት ነው?  የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ነው።

አዳምና ሔዋን በገነት በነበሩበት ወቅት አታድርጉ የተባሉትን ነገር አደረጉ ወይም ፈጸሙ። የሰው ልጅ በታሪኩ አታድርግ የተባለውን ነገር ማድረግ ይወዳል፣ ትዕዛዛትን ይተላለፋል፣ በእዚህም የተነሳ ራሱንና ሌሎችን ይጎዳል ይበድላል፣ ከእግዚኣብሔር ጋርም ይጣላል። አዳም አታድርግ የተባለውን ነገር በማድረጉ /አትብላ የተባለውን ነገር በመብላቱ (በነገራችን ላይ የሚበላ ነገር አቶ ተርቦ አይደለም የበላው፣ ያደረገው ያደረገው . . . “እባቡ ሴቲቱን እንዲህ አላት ይህንን ፍሬ በበላችሁ ወቅት አትሞቱም፣ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደ ሚከፈትና መልካምና ክፉን በመለየት እንደ እግዚኣብሔር እንደ ምትሆኑ እግዚኢኣብሔር ስለሚያውቅ ነው አትብሉ ያላችሁ” (ኦሪት ዘ. 3.3)። ስለዚህም እግዚኣብሔርን መሆን ፈለጉ፣ አታድርጉ የተባሉትን አደረጉ፣ ይህንንም በማድረጋቸው፣ የእግዚኣብሔር ክብር ጎደላቸው፣ እራቁታቸውን መሆናቸውን ስለተረዱ ይቅርታን ከመጠየቅ ይልቅ መደበቅን መረጡ።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ። በእውኑ ከእግዚኣብሔር መሰወር ይቻላልን? እግዚኣብሔርን ማታለል ይቻላልን? ከሰዎች ተደብቆ ክፉ ነገርን መፈጸም ቀላል ነገር ሊሆን ይችላል። ከእግዚኣብሔር ግን በፍጹም መደበቅ አይቻልም። አዎን! ስህተቶችን ስንፈጽም፣ ኋጥያትን ሥንሠራ ይቅርታን ነው እንጂ መጠየቅ የሚገባን፣ በንስሐ ነው እንጂ መታጠብ የሚገባን መደበቅ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ከእግዚኣብሔርና ከራሳችን መደበቅ በፍጹም አንችልም። እባቡ በተናገርው መሰረት የአዳምና የኤዋን ዐይን ተከፍቶ ነበር። ነገር ግን ያ የተከፈትው ዐይን ክፉና ደጉን የሚለይ ሳይሆን የእግዚኣብሔርን ጸጋ ብን አድርጎ ያጠፋና እራቁታቸውን እንደ ሆኑ ያዩበት ዐይን ነው። እንደ ሰው ያልሆነው እግዚኣብሔር ግን አዳምን ፍለጋ ወጣ። አዳም ሆይ የት ነህ ያለሄው? ብሎ መጣራት ጀመረ እግዚኣብሔር። ይህ ነው እንግዲህ ታላቁ የእግዚኣብሔር ባሕሪ መገለጫ፣ የጠፋውን ይፈልጋል፣ የፈራውን ያበረታታል፣ የተጨነቀውን አይዞህ ይላል፣ ያዘነውን ያጽናናል፣ የጠፋውን ይፈልጋል፣ ብቸኛ የሆነውን ይት ነህ የት ነሽ ብሎ ይፈልጋል። በተመሳሳይ መልኩ እኛንም ይጠራናል ይፈልገናል። ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ ‘አሁን የምንኖርበት ዓለማችን ዋነኛው ስጋት “ይቅር እባላለሁ ወይ?” የሚል ስጋት መሆኑን ገልጸው ነበር። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለምሕረት ያላት አመለካከትና አስተምህሮ በምዕመናኖቹዋ ልብ ውስጥ ተጠብቆ ይኖር ዘንድ ለማስቻል በማሰብ በኢትዮጲያ አቆጣጠር ከኅዳር 29/2008 ዓ.ም ጀምሮ ለ349 ቀናት ያህል ልዩ ልዩ መንፈሳዊና አካላዊ የምሕረት ተግባራት በማከናወን በእግዚኣብሔር ምሕረት እንዳሰስ ዘንድ ያወጁት ይህም ቀን የዛሬ ሁለት ሳምንት 14 ቀን ቡኋላ ማለት ነው ቡኋላ በኅዳር 11/2009 ዓ.ም ይጠናቀቃልና አጋጣሚውን በመጠቀም ወደ እግዚኣብሔር መመለስ ያስፈልጋል ምክንያቱም እግዚኣብሔር መሐሪ ስለሆነ።

“ምሕረት” የሚለው ቃል  የተከፈተና የሚራራ ልብን ይገልጻል። ይህም ቃል በላቲን ቋንቋ ላይ መሰረቱን ያደረገ ሲሆን misericordia ከሚለው ቃል ውስጥ cor የሚለው ለማንኛውም ስቃይ የሚሳሳ ልብን የሚያመለክትና በተለይም ደግሞ በጣም የሚሰቃዩ ሰዎችን የተመለከተና ልዩነቶችን አስወግዶ የሌሎችን ስቃይ የሚጋራ ልብ ማለት ነው። ታዲያ በዚህ ልዩ ቅዱስ የምሕረት አመት ማድረግ የሚጠበቅብን ተግባራት ምንድናቸው። ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ ደጋግመው እንደ ገለጹት በምሕረት በሩ ማልፍ ብቻ በቂ አይደለም። ይልቁንም ማድረግ የሚጠበቅብን ነገር በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 19. እንደ ተጠቀሰው የዘኬዎስ ታሪክ ንስሐችን በተግባር ሊፈጸም ወይ ሊታጀብ ያስፈልገዋል። ዘኬዎስ ኢየሱስን ስላገኘ ደስ ብሎት “ጌታ ሆይ! እነሆ ካለኝ ሐብት ሁሉ እኩሌታውን ልድኾች እሰጣለሁ፣ በማታለል ከሰዎች ላይ የወሰድኩት ገንዘብ ቢኖር አራት እጥፍ አድርጌ መልሳለሁ” ባለ ጊዜ ኢየሱስም ዛሬ ደኅንነት ለእዚህ ቤት ሆኖኋል” በማለት መለሰ። ምክንያቱም ይህም የደኅንነት ምስጢር ተፈጻሚነትን ያገኘው ዘኬዎስ እምነቱን በተግባር ለመግለጽ ቃል በመግባቱ ምክንያት ነው።

እኛም ለመጠናቀቅ 14 ቀን በቀሩት ልዩ ቅዱስ የምሕረት አመት ልጆቼ ሆይ የት ናችሁ ብሎ ለሚፈልገን እግዚኣብሔር፣ እኔ የመጣሁት የጠፉትን በጎች ለመፈልግ ነው ለሚለው ኢየሱስ በቂ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የምናደርገው ንስሐ ቅዱስ በሩን በማለፍ ብቻ የሚፈጸምና ይህ ልዩ ቅዱስ የምሕረት አመት ከተጠናቀቀ ቡኋላ የሚረሳ ነገር ሳይሆን መሆን ያለበት ንስሐችንን በተግባራችን መግለጽ ይጠበቅብናል።

ይህንንም ለማድረግ ያስችለን ዘንድ 7ቱ አካልዊና መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራትን መፈጸም ያስፈልጋል። ሰባቱ አካልዊ የምሕረት ተግባራት የሚባሉት የተራበን ማብላት፣ የተጠማን ማጠጣት፣ የታረዘን ማልበስ፣ የባዕድ ሀገር ሰውን መቀበል፣ የታመመን መጠየቅ፣ የታሰረን መጎብኘትና ሙታንን በክብር መቅበር የሚሉ ሲሆኑ 7ቱ መንፋስዊ የምሕረት ተግባራት ደግሞ የተሳሳቱ ወይም የማያውቁ ሰዎችን ማስተማር፣ በጥርጣሬ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን መምከር፣ ከሐጥያተኞች ጋር አለመተባበር፣ ክፉ ነገር የሚፈጽሙብንን ሰዎች በትዕግስት ማሳለፍ፣ በደልን ይቅር ማለት፣ የተጎዳን ማጽናናትና በመጨረሻም በሕይወት ላሉና በሕይወት ለሌሉ ሰዎች ሁሉ መጸለይ የሚሉትን ልንፈጽም ያስፈልጋል።

ጌታችን በዛሬ ወንጌል “በቅድሚያ የእግዚኣብሔርን መንግሥት እና ጽድቁን ፈልጉ ሌላው ነገር ይጨመርላችኋል” እንዳለን በቅድሚያ የአዳኛችንን የምድኋኔ ዓለምን መንገድ መገተል ይጠበቅብናል። ይህንንም ተግባራዊ ማድረግ እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያ በአማላጅነቷ ትርዳን፣ አሜን!

 








All the contents on this site are copyrighted ©.