2016-10-31 10:28:00

አራተኛ ሰንበት ዘጽጌ ቃለ እግዚኣብሔር በክቡር አባ መምህሩ መኮንን።


 

የማቴዎስ ወንጌል 12.1-21

ሰንበትን ስለ ማክበር

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር። ፈሪሳውያንም አይተው “እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን? ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን? ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። 
ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና። 

ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ። እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው። ከዚያም በኋላ ሰውየውን እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት። 
 ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው።
በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው “እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ። 








All the contents on this site are copyrighted ©.