2016-09-20 10:37:00

ቅዱስነታቸው በሁሉም አቅጣጫ ጦርነት በበዛባት ዓለማችን ምዕመናን ጸሎት እንድያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸው ተገለጸ።


ቅዱሰ አባታችን ፍራንቸስኮ በሁሉም አቅጣጫ ጦርነት በበዛባት ዓለማችን ምዕመናን ጸሎት እንድያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸው ተገለጸ። ቅዱስነታቸው እንደ ጎርጎሮሳዊያን የቀን አቆጣጠር በመስከረም 18/2016 በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጠቅላላ አስተምህሮ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች፣ ከምዕመናን ጋር ከደገሙት የመልዐከ እግዚአብሔር ጸሎት ቡኋላ ባሰሙት ንግግራቸው በመጭው ማክሰኞ ለአንድ ቀን በአሲዚ ለሰላም በሚካሄደው ጸሎት ላይ ለመሳተፍ እንደ ሚሄዱም ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።



“ከመቼውም ጊዜ በላይ ጦርነት በየቦታው በበዛበት ዓለማችን ሰላም ይወርድ ዘንድ መጸለይ ይገባናል” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የዛሬ ሰላስ ዓመት ገደማ ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዩሐንስ ጳውሎስ ጸሎት ለዓለም ሰላም በአሲዚ እንዲደረግ መወሰናቸውን አስታውሰው የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል ለሰላም ጸሎት ለማድረግ ወደ አሲዚ እንደ ሚሄዱ ገልጸው ሁሉም ቁምስናዎች፣ የቤተ ክርስቲያን ማሕበራትና እንዲሁም እያንዳንዱ በዓለም ውስጥ የሚገኝ ምዕመናን በእለቱ በሚደረገው ጸሎት በእያሉበት ሆነው እንዲሳተፉ ጥሪ አድርገዋል።

“የወንድማማችነት እና የትሕትና ተምሳሌት የሆነውን የአሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮን ፈለግ በመከተል በሕዝቦች መካከል ሰላም እና እርቅ ይሰፍን ዘንደ ስለሰላም በጋራ ለዓለም ልንመሰክር ይገባናል” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “በእለቱ ሁላችንም የተወሰነ ጊዜ ለጸሎት መስዋዕት ማድረግ እንደ ሚገባና  በመላው ዓለም የሚገኙ ሁሉ ይህንን ጥሪ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ በዓለማቀፍ ደረጃ ለሰላም የሚደረግ ጸሎት በቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር አስተባባሪነት የተዘጋጄ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ዓላማውም የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎችን በአንድነት በማሰባሰብ ለዓለማችን ሰላም ጸሎት የሚደረግበት እና እንዲሁም አጋጣሚውን ተጠቅመው ወሳኝ ዓለማቀፋዊ የሰላም ጉዳዮች ላይ መወያየት፣ ሕብረትን መፍጠር እና በተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መካከል ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረግን ጭምር ዓላማ አድርጎ ያነገበ መሆኑን ለመረዳት ተችልኋል።

ከተካሄደው የመልዐከ እግዚአብር ጸሎት በፊት ቅዱስነታቸው በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመሥርተው አድርገውት በነበረው ጠቅላላ አስተንትኖ ወቅት “የዓለም መንፈስና የኢየሱስ መንፈስ የማይገናኙ ነገሮች” መሆናቸውን ገልጸው የነበረ ሲሆን የዓለማዊነት መገለጫው ሙስና፣ ማጭበርበርና  ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ወደ ኋጥያት የሚወስደውን መንገድ መያዝ መሆናቸውን ገልጸው የነበረ ሲሆን ትክክለኛ የክርስቲያን ሕይወት መገለጫ መሆን የሚገባው “ከባድ፣ ነገር ግን በደስታ የተሞላ፣ ለታማኝነት ያደረ፣ ትክክለኛ፣ ሌሎችን ማክበር እና መብታቸውን መጠበቅን ማዕከል ያደረገ እና የአገልጋይነት መንፈስ የተሞላበት” መሆን እንዳለበት ማሳሰባቸውም ተገልጽኋል።

በስተመጨረሻም ቅዱስነታቸው እኛ ክርስቲያኖች ሁላችን እየታየ ላለው ዓለማዊ ብልህነት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በሆነው ክርስቲያናዊ ምልከታ መልስ መስጠት እንደሚገባ” ገልጸው በዓለማችን እየተስፋፋ እና ሰፊውን የማሕበረሰብ ክፍል እየጎዳ የሚገኘውን ሙስና ክርስቲያኖች የወንጌልንና የወንድማማችነትን መንፈስ  የሚያጠናክርውን ስነ-አመክንዮ (Logic) ተከትለው የተኛውን አቅጣጫ መያዝ እንዳለባቸው መወሰን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው “ፍትህ  ይሰፍን ዘንድ የራሳችንን ሚና እንድንጫወት እና ለሰው ልጆች የተፋን አድማስ” መክፈት እንደ ሚኖርብን አሳስበውና ቡራኬን ሰጥተው የእለቱ ፕሮግራም ተጠናቁዋል።  








All the contents on this site are copyrighted ©.