2016-09-17 17:04:00

ሰንበት ዘዘካሪያስ፣ ቃለ እግዚአብሔር በአባ ተወልደ ፉጂዬ


ሰንበት ዘዘካሪያስ

የ08/01/2009 እለተ ሰንበት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት፣

  1. ወደ ዕብራዊያን ሰዎች 11.32-46

  2. የዩሐንስ ራእይ 6.9-11

  3. የሐዋሪያት ሥራ 19.1-5

  4. የማቴዎስ ወንጌል 23,23-39

የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

የዛሬው እለተ ሰንበት በቤተ ክርስቲያን አበው አባባል ዘዘካሪያስ ተብሎ ይጠራል። ይህም በሰባት ዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ የሚመጣ እሑድ “ለእመ ኮነ” በመባል ይታወቃል። በመስከረም 8 የመጥምቁ ዩሐንስ አባት የነበረው የእግአብሔር ሰው ዘካሪያስ በግፍ በቤተ መቅድስ ውስጥ መገደሉን የምናስብበት ሰንበት ነው። በዛሬው ሰንበት የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የሚያስተላልፉልን መልዕክት በእምነት አሸናፊ መሆን እንደ ሚቻል ነው፣ የዕብራዊያን መልዕክት ጸሐፊ እንዲህ ይላል “እንግዲህ ሌላ ምን እላለሁ! ስለ ጌዴዎን፣ ስለ ባራቅ፣ ሰለ ስምሶን፣ ስለ ዮፍታኤ፣ ስለ ዳዊት፣ ስለ ሳሙኤል፣ ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል” (ዕብ. 11, 32) ይላል።

እነዚህ ሰዎች እነ ማን ናቸው ብለን እራሳችንን የጠየቅን እንደሆን በእምነት አሸናፊ ሆነው በዘመናቸው ከፍተኛ ምስክርነትን የሰጡ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው። የእግዚአብሔር ሕያው ቃል በዘመናቸው እንዲሠራ እና እንዲቀጣጠል ክፉ የሚሠሩትን ወደ መልካም መንገድ እንዲመለሱ በመምከር፣ ከእምነት ጎዳና የወጡትን ፍቅርን እየለገሱ በመመልስና በመምከር፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥለው መልካም የሆነውን መርጠው በእመንት አሸናፊ የሆኑ በልዑል እግዚአብሔር የተመረጡ የእምነት አንባሳደሮች ናቸው።

ዛሬም በዘመናችን እንደነዚህ አንባሳደሮች እኛም የእነርሱን ፈለግ በመከተል በእምነት ማሸነፍ የሚቻልበት ሰፊ የሆነ እድል ስላለ ለዚህ ተጠርተናል።

እነዚህ ቅዱስና አባቶች በዘመናቸው የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት በደልን በፈጸሙበት ወቅት፣ በእግዚአብሔር እና በቃሉ ስያምጹ፣ እውነት የሆነውን ነገር ሲጠሉ፣ የፀደቀውን ሲሽሩ፣ የቆመውን ሲጥሉ ተመልክተው በዝምታ ማለፍ ከበዳቸው እጅግ በጣምም አዘኑ። ነገር ግን ከብዶናል አንችለውም፣ አዝነናል ምንም ለማድረግ አንችልም ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አለተቀመጡም። ይልቅ እግዚአብሔርን ተገን አድርገው እውነት የሆነውን በመመስከርና በማስተማር እምነት ምንግዜም አሸናፊ መሆኑን መሰከሩ፣ የሚገሰጸውን ገሰጹ፣ የሚመከረውን መከሩ የእስራኤልን ሕዝብ ታደጉ።

ከእነርሱ መካከል የአንድ የአንዳንዶቹ ቤተሰቦች የተናቁ ነበሩ እግዚአብሔር ግን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፣ ረዳቸው የአሸናፊነትን ማዕረግ ሰጣቸው፣ የድል አድራጊነት ካባን አለበሳቸው። አያችሁ እግዚኣብሔር ሲጎበኘን ፣ እግዚአብሔር ሲደግፈን እንበረታለን፣ ጠንካራ እንሆናለን፣ እናሸንፋለን፣ ድል እንቀናጃለን ምክንያቱም እርሱ አሸናፊ ነው፣ እኛም የአሸናፊው ልጆች ነንና።

ስለዚህ የዕብራዊያን መልዕክት ጸሐፊ “ስለዚህ ሰዎች እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል” እነርሱ በጊዜው በእምነት   አሸናፊዎች ነበሩ ፣ የተሰጣቸውንም ክብር ያገኙ ናቸው እያለ ስእነርሱ ይመሰክራል።

ዛሬም እያንዳንዳችን እምነት አሸናፊ መሆኑን ተረድተንና ተገንዝበን ፍትህ ሲጓደል መጮኽ፣ ስለፍትህ መሟገት ይገባና፣ መከራከር እና መሟገት ለማይችሉት ሁሉ ድምጽ ልንሆን ይገባል ምክንያቱም የተጠራነው ለዚህ ነውና።  ዛሬ ይምንሰማቸው፣ የምናያቸው፣ የምንመለከታቸውና የምንታዘባቸው ነገሮች ሁሉ ለዚህ ጥሪ ምላሽ እንድንሰጥ የሚጋብዙን ናቸው፣ በራቸውንም ከፍተው እየጠበቁን ነው ያሉት።

ከነደካማው ማንነታችን እግዚአብሔር በእኛ በኩል ሊሠራ ይፈልጋል፣ ብዙ የድረሱልን ድምጾች አሉ። የድረሱልን ድምጾች፣ የአግዙን እና የተባበሩን ድምጾች . . . . ይህ ለእኛ ክርስቲያኖች የቀረበ ጥሪ ነው። ችላ ልንለው አይገባም፣ ጥሪውን ተቀብለን የሚገሰጹትን በመገሰጽ፣ የሚመከሩትን በመምከር፣ ፍትህ የሚያጓድሉትን በመቃወምና በኋጥያት የተጨማለቁትን እንዲነጹ በማድረግ፣ እውነት የሆነውን በማስተማር እመነት አሸናፊ መሆኑን ልንመሰክር ይገባናል።

ይህንን ምስክርነት በምንሰጥበት ጊዜ ልንጠላ እና ልንገለል፣ ላንደመጥ እንችል ይሆናል ነገር ግን ሌላ መንገድ የለም ምክንያቱም እውነታቸው መንገድ ይህ ነውና. . . ልያስደነግጠን እና ልያስፈራራን ግን አይገባም ምክንያቱም የሚያከብረን እና የሚወደን፣ የሚረዳን እና የሚጠብቀን ሰማያዊ አምላክ ከእኛ ጋር ነውና፣ ሽልማታችንም ከላይ ከሰማይ ነውና፣ ልንሸበርና ልንደነግጥ አይገባም። እግዚአብሔርም እያለን ያለው ነገር እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ እና “አይዞኋችሁ አትፍሩ” እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ ተናገሩ፣ በእመንት፣ በእውነት መንፈስ ሆናችሁ የሚቃናውን አቅኑ፣ የሚመከረውን ምከሩ አስተምህሩ ይለናል።

አሁን የምንገኝበት ወቅት የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ ጠባቂ የሆኑት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ የምሕረት ዓመት ብለው ሰይመውልናል። እግዚአብሔር የምሕረትና የይቅርታ አባት መሆኑን እያስተማርን ሰዎችን ወደ ንስኋ መጥራት ይገባናል።

ብዙዎች ገና የእግዚአብሔር ምሕረት እና ፍቅር፣ ቸርነት እና ርኅራኄ ያልተረዱ አሉ። ነገር ግን አማኞች ናቸው። የአብ የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ አንድነትንና ሕብረትን ያልተረዱ፣ ያልተገነዘቡም አይጠፉም፣ ነገር ግን አማኞች ነን የሚሉትን የኤፌሶን ጥቂት ሰዎችን ሐዋሪያ ጳውሎስ ባገኛቸው ጊዜ “ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችሁ ነበርን? ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳን ሰምተን አናውቅም” (ሐዋ. 19,2) ሲሉ መለሱለት። ይህ እውነት ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚተርክልን እውነት ነው። ዛሬም ብዙዎቻችን በእምነት ያልጠነከርን እግዚአብሔር የምሕረት እና የፍቅር አባት ነው ብለን የምናስተምር ነገር ግን ምህረትንና የቅርታን የማንወድ ስለእምነታችን ምስክርነት መስጠት ያላቻልን ሰዎች ካለን እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ጥሪውን ያቀርብልናል የሚሰማ ጆሮ ነው የሚያስፈልገው፣ ድምጹን ሰምተን እንደ ቀድሞ አባቶቻችን በእመነት አሸናፊዎች ልንሆን ያስፈልጋል። ይህንን መፈጸም እና በዚህ ጎዳና መራመድ ካልቻልን በወንጌሉ እንደ ተገለጸው እንዲህ እያለ ይገስጸናል “እናተ ፈሪሳዊያን ወዩላችሁ፣ አገልጋዮች ነን ትላላችሁ ነገር ግን አገልግሎታችው ፍሬ የሌለው ዛፍ ነው። ለሌሎች ከማሰብ ይልቅ ስለግል ሕይወታችሁ የምትጨነቁ፣ የወደቁትን፣ የተረገጡትን፣ የተበደሉትን፣ የተጠሉትን እና የተገለሉትን የምትመልከቱባቸው አይኖች ታውረዋልና ወዩላችሁ!” እያለ ይገስጸናል።

የሐሰት ክርስትናና የሐሰት አገልጋዮች ውጫዊ ማንነታችን አገልጋይ የሚያስመስለን፣ አማኝ የሚያስመስለን ምልክት ያለው፣ ውስጣዊ ማንነታችን ግን የእግዚኣብሔር ጠላቶች ሆኖ ተሸፍኖ የሚኖር ማንነት ነው። ይህንን የውስጣዊ ማንነታችንን መመልከት የሚችል አማላክችን እግዚአብሔር “ወዩላችሁ!” ይለናል።

“ከአዝሙድ፣ ከእስላል፣ ከከሙን አሥራትን ትሰጣላችሁ ይህ ደግሞ ህግ የሚያዘው ነው። ደግሞም ትፈጽማላችሁ። ነገር ግን በሕግ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ነገሮችን ትተዋላችሁ፣ እነርሱ ፍርድ፣ ምሕረትና ታማኝነት ናቸው” (ማቴ. 23.23)። እንግዲህ በዛሬው ወንጌል ጌታችን መዳኋኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእውነት የማያገለግሉትን፣ ስለፅድቅ የማይሠሩትን ፍርደ ገምድሎችን አመጸኞችን፣ ከእኔ ባልይ ማን አለ? ባዮችን፣ አምባገነኖችን፣ ስለምሕረት እና ታማኝነት ደንታ የሌላቸውን፣ ከእምነት ውጭ የሆኑ ተግባራትን የሚያከናውኑትን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን፣ የሀገር መሪዎችን አማኞች ነን የሚሉትንና ነገር ግን ከእምነት ውጭ የሆኑ ተግባራትን የሚያከናውኑትን በሙሉ እናንተ ግብዞች፣ “እናንተ እባቦች የእባብ ልጆች!” (ማቴ 23,33) እያለ የገስጸናል።

የተወደዳችሁ የልዑል እግዚኣብሔር ቤተሰቦች!

ከእንዲህ ዓይነቱ ግሳጼ ለመዳን ከፈለግን ቅን የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል። ስለምሕረትና ፍቅር፣ ታማኝነትና ደግነት ምስክርነት ልንሰጥ ይገባል። በፍቅር፣ በመግባባት፣ በመዋደድ፣ በመተጋገዝና በመረዳዳት በመዋደድ እና በመከባበር የአብሮነትንና የአንድነትን መንፈስ ይዘን የእግዚአብሔርን የጽድቅ ሥራ ሠርተን በሰማይ ፈጣሪን በምድር ደግሞ ባልንጄሮቻችንን የሚያስደስት ተግባር ልናከናውን ይገባል። ይህ ተግባር መጀመር የሚገባውም ከእያንዳንዳችን ቤት ነው።

ይህንን ከፈጸምን ደግሞ “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፣ እናንተ ጻድቃን ኑ ከጥንት ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን የእግዚአብሔርን መንግሥት ውረሱ” ተብለን እንጠራለን። በዛሬውም ሰንበት ለእዚህ ታላቅ ግብዣ ሁላችንም ተጠርተናል፣ ግብዣውም ንስኋን ገብተን ክቡር የሆነውን ቅዱስ ሥጋውን እና ደሙን ተቀብለን እንደ የእምነት አባቶቻችን በትክክለኛው ፍትህ አስተዳድረን የተሰጠንን ተስፋ፣ አለኝታን፣ የአንበሶችን አፍ ዘግተን፣ የእሳትን ነበልባል አጥፍተን፣ እምነት አሸናፊ መሆኑን እንድንመሰክር ተጠርተናል። ይህንን እንድንፈጽም ጌታ በፀጋው ይርዳን።

አሜን!!
All the contents on this site are copyrighted ©.