2016-09-15 14:58:00

ቅዱስ አባታችን “የወላጅ አልባነት መንፈስ ተጋርጦባት በታላቅ ስቃይ ውስጥ በምትገኘው ዓለማችን” የማሪያም እናትነት ያስፈልጋል።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በዛሬው እለት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳዊያን የቀን አቆጣጠር በመስከረም 15/2016 በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ካህናት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት ባሳረጉት ሰርዓት ቅዳሴ ወቅት በእለቱ የተከበረውን “የአዛኝቱ ማሪያም” በዓልን ባማከለ ሰብከታቸው “የወላጅ አልባነት መንፈስ አደጋ ተጋርጦባት በታላቅ ስቃይ ውስጥ በምትገኘው ዓለማችን” አብራን የምትጓዝ እና የምትከላከልን እናት አለችን” ማለታቸው ተገለጸ።

የዛሬው ወንጌል (ዩሐንስ 19,25-27) የኢየሱስ ወደ ተጋፈጠው የምስቀል ሞትን እንድንመለከት ይጋብዘናል በማለት ስብከታቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ሁሉ ሸሽተው በነበሩበት ወቅት ዩሐንስ እና የተወሰኑ ሴቶች ብቻ በኢየሱስ መከራ ወቅት አብረውት እንደቀሩ ገልጸው በተለይም ደግሞ የኢየሱስ እናት ማሪያም በመስቀሉ ሥር ቁማ የነበረች ሲሆን ሁሉም ወደ እርሷ እየተመለከቱ “ይቺህ የእዚህ የዘራፊ እናት ናት፣ ይችህ የእዚህ አመጸኛ እናት ናት” ይሉ እንደ ነበር አስታውሰዋል። 

“ማሪያም እነዚህን ነገሮች ታዳምጥ እና በልቧም ታሰላስል ነበር” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉ ቅዱስነታቸው “በእዚህም ምክንያት ከፍተኛ የውርደት ስሜት ይሰማት ነበር፣ በተጨማሪም እርሷ ካህናት በመሆናቸው ብቻ ታከብራቸው የነበር አንድ አንድ ካህናትም ስይቀሩ ‘አንተ በእውነት ጎበዝ ከሆንክ እስቲ ከእዚህ መስቀል ላይ ውረድ!’ ብለው በሚያፈዙበት ወቅት እና እራቁቱን በመስቀል ላይ የነበረውን አንድኛ ልጁዋን በምታይበት ወቅት ማሪያም ከፍተኛ የሐዘን ስሜት ውስጥ ገብታ የነበረች ቢሆንም ቅሉ ኢየሱስን ብቻውን ጥላው ለመሄድ ግን አልፈለገችም፣ ምንም እንኳን አካላዊ ስቃይ ብበዛባትም ልጇን ግን መካድ አልፈለገችም” በለዋል።

ቅዱስነታቸው የቦነስ አይረስ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት እስረኞችን ለመጎብኘት በሚሄዱበት ጊዜ ሁሉ ብዙ ሴቶች ታሳሪ የሆኑ ወገኖቻቸውን ለመጎብኘት ሰልፍ ይዘው ሲጠባበቁ ማየታቸውን አስታውሰው “እነዚህ እናቶች ምንም አይነት የአፍረት ስሜት ስይሰማቸው ሁለንተናቸውን በእስር ቤት ውስጥ ባሉት ወገኖቻቸው ላይ አድርገው ነበር። እነዚህ እናቶች እስር ቤት በመገኘታቸው ከሚሰማቸው እፍረት ባሻገር ‘ተመልከት/ች አስቲ ያኛውን! ምን ሰርቶ ይሁን የታሰረው?’ እያሉ በስስት ከመመልከት አልፈው ተርፈው እስር ቤት ውስጥ ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት ውርደት ይገጥማቸዋል ይህ ሁሉ መከራ ቢኖርባቸውም እንኳን እናቶች በመሆናቸው እና የገዛ ስጋቸውን ለማግኘት ብቻ ሲሉ ወደ እስር ቤት ይሄዱ ነበር፣ ማሪያምም ያለፈችሁ ይህንን ታላቅ መከራ ነው” ብለዋል።

“ኢየሱስ” አሉ ቅዱስነታቸው “ኢየሱስ እንደ ወላጅ አልባ ልጆች ብቻንን ላይተውን ቃል በመግባቱ የተነሳ በመስቀል ላይ ሳለም እንኳን እናቱን እናት እንድትሆነን ሰጠን” በማለት ስብከታቸውን ቀጥለው “እኛ ክርስቲያኖች ለኢየሱስ እናቱ የሆነች ለእኛም እናት እንድትሆን የተሰጠችን እናት አለችን! ወላጅ አልባ አይደለንም! በታላቅ መከራ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ወልዳናለች፣ እውነትም ሰማዕት ናት፣ የሐዘን ሰይፍ ልቧን ውግቶ የነበር ቢሆንም እንኳን በእዚያም መከራ ውስጥ ሆና እኛን ሁላችንን ለመውለድ ፈቃደኛ ሆነች ብለው  ከእዚያን ጊዜ ቡኋላ እኛን ያለምንም አፍረት ለመንከባከብ እና ለመጠባበቅ ለሁላችን እናት ሆነችን” በማለት ገልጸዋል።

በመጀምሪያው ምዕተ ዓመት የነበሩ የሩሲያ መናኒያን መንፈሳዊ ቀውስ በሚገጥመን ወቅት ሁሉ “በእግዚአብሔር እናት እጅ ከለላ ውስጥ መጠለል” አስፈላጊ መሆኑን ይመክሩ እንደ ነበር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው “የእርሷን ከለላ አልፎ የሚገባ ምንም አይነት የሰይጣን ኋይል የለም፣ ምክንያቱም እርሷ እናት ናት እንደ አንድ እናት ትከላከለናለች” ብለው በአሁኑ ጊዜ ግን የምዕራቡ ዓለም ‘እናት ሆይ! ባንች ከለላ ሥርና  በጥበቃሽም እንታመናለን በእዚህም እርግጠኞች ነን’ የሚለውን ይህንን ምክር ዘንግቶ ይገኛል” በለዋል።

“ስለዚህም ይህንን ዓለም ወላጅ አልባ ዓለም ልንለው እንችላለን” በማለት የማጠቃለያ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ይህ በወላጅ አልባነት በሚሰቃየው ዓለማችንን ምን አልባት መርዳት የምንችለው የምትጠብቀንን፣ የምታስተምረንን፣ በጉዞዋችን አብራ የምትሆነውን እንዲሁም በኋጥያታችን የማታፍረውን “እናትህን ተመልከታት!” ማለት ብቻ ነው ብለው እናት ስለሆነች ማፈር አይገባንም ለዚህም አጋራችን፣ በጉዞዋችን የሚያጅበን፣ ጠበቃችን ይሆን ዘንድ ጌታ የላከልን መንፈስ ቅዱስ የማሪያምን እናትነት በጥልቀት መረዳት እንድንችል ይረዳን ዘንድ መማጸን ያስፈልጋል ብለው የእለቱን ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.