2016-09-10 11:08:00

ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ለመላው ምዕመናን የ2009 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት


ብፅ ካርዲናል ብርሃነየሱስ  በኢትዮጲያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ለመላው ምዕመናን የ፳፻፱ (2009) . የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

 

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

 

 

ግዚአብሔር ሆይ ከዘመናት እስከ ዘመናት መጠጊያ ሆነኸናል; (መዝ.901)

 

 

ብፁዐን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናትና ገዳማውያን/ዊያት

ክቡራትና ክቡራን መዕመናን

መላው ሕዝበ እግዚአብሔር

በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ

 

 

የተወደዳችሁ ምዕመናን ከሁሉ አስቀድሜ በራሴና በኢትዮጲያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ከዘመነ ዩሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ የ፳፻፱  (2009) ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን እገልጽላችኃለሁ፡፡

 

የልዑል እግዚአብሔር ስጦታ ምንኛ ትልቅ እንደሆነ በተፈጥሮ ውስጥ እያየን የእግዚአብሔርን ታላቅነት እርሱ በሰጠን የጊዜ መለያ መሰረት አሮጌውን ዓመት አሳልፈን አዲሱን ዓመት ስንቀበል በክብር የተሞላ የእግዚአብሔርን ሥራ በማየት ሁሉን ለፈጠረና ለሰጠን ከዘመናት እስከ ዘመናት መጠጊያችን የሆነውን እግዚአብሔርን በማመስገን ነው፡፡

 

በአዲሱ ዓመት ሁላችንም የግልና የቤተሰብ ሕይወታችንን የምናስተውልበትና መልካም የሆኑ ባህሪዎችንና ሥራዎችን ለመፈፀም የምንነሳሳበት እንዲሁም ተግዳሮት የሆንብንን የምንወጣበት የምንወጣበት ሊሆን ይገባል፡፡ የቤተሰብ ሕይወት በእግዛአብሔር ዘንድ ከፍያለ ዋጋ እንዳለው ተገንዝበን ቤተሰባዊ ትስስርነት እንዳይጠፋ ትኩረት በመስጠት ጥሩ ምሳሌ ሰጭዎች ሆነን መገኘትይኖርብናል፡፡ ለዚህም ከእኔነትና ከግላዊነት አሰተሳሰብ መውጣት ያስፈልጋል፡፡በመሆኑም ለሥነ-ምግባርና የእምነት ትምህርቶችን ከፍተኛ ዋጋ መስጠት ይኖርብናል ፡፡ለዓለም ነዋሪ የሆነው እግዚአብሔር ሁሉንም ነገሮች ዘለቄታና የሚጨበጥ ኑሮ እንዲኖሩ እንደጠራቸው ሁሉም የሚማረውና የሚሰራው በሕይወት እይታ ጥሩ አመለካከትን ይዞ እንደመሆኑ ሁላችንም አዲሱን ዓመት በደስታ እንደምንቀበለው ጥሩና የተሻለ ለመሥራት በእርሱ ላይ በመተማመን እንጠቀምበት፡፡እግዚአብሔር አዲሱን ዓመት ሲሰጠን ልንጠቀምበት ነውና በጊዜያት ውስጥ መጠቀምና ማትረፍ የእኛ ድርሻ መሆኑን ልብ ልንል ያስፈልግል፡፡

 

አምስት ብር የተቀበለው አገልጋይ ወደ ጌታው መጣና ሌላም አምስት ብር አቅርቦጌታ ሆይ! አምስት ብር ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት ብር አትርፌያለሁ!’ አለ፡፡ ጌታውም  መልካም አደረግህ፤ አንተ ታማኝና ደግ አገልጋይ! በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ና የጌታህን ደስታ ለመካፈል ግባ!’አለው፡፡;  (ማቴ፡ 2521-22)                          

 

 

 

በእኛ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ተስፋ ታላቅ ሚና ያለው እንደመሆኑ ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን አንድነት ትስስራችን ከፍ ያለ ነው፡፡የሰው ልጆች ሁላችን በእርሱ እጅ እንደመሆናችን የዓመታት ዑደትና የከዋክብት አቀማመጥ የጊዜያት መጀመሪያ ማብቂውና አጋማሽ፣ የቀናት እርዝማኔ ልውውጥና፣ የወቅቶች መፈራረቅ ሁሉም የእርሱ ነውና እርሱን በማመስገንና በሃይማኖት መንፈስ ቡራኬን ለማግኘት የመንፈሳዊ  ልምድ  ስሜታችንን ጠብቀን ማቆየት ወሳኝ ግዴታችን ነው፡፡

ቅዱስ አባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የምህረት ዓመት ብለው ለመላው ዓለም የካቶሊካዊት እምነት ተከታዮች በአወጁልን ዐዋጅ መሠረት ይህንታላቅ ፀጋ በመቀበል የተለያዩ  መንፈሳዊ በረከቶችን ለማግኘት በመንፈሳዊ ትሩፋቶች እንድንበረታና እንድንጓዝ መሐሪዎችም እንድንሆን አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡

 

አዲሱን ዓመት ሁላችንንም ባሳተፈ መልኩ ስናከብር አብሮ በመኖር ደረጃ ኢትዮጲያዊነታችን ትልቅ ዋጋ ያለው በመሆኑ አንድነትንና ህብረታችንን በማጠናከር የመቻቻል ባህላችንን በበለጠ በመስተሳሰር የእምነት ዕሤቶቻችንን ጠብቀን  እንድንጋዝ አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡

 

የሰማዩ አባታችሁ መሀሪ እንደሆነ እናንተም መሐሪዎች ሁኑ!!; (ሉቃ፡- 636 )

 

ባሳለፍነው ዓመት በአገራችን በአንዳንድ ቦታዎች የታዩ ወስጣዊ ግጭቶች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሁኔታዎች ወደ ጥፋትና የማኀበረሰብ ስሜት ማፋለስ እንዳያስከትሉብን በሰከነ መንፈስ ነገሮች የሚፈቱበት መንገድ እንዲደረግ ቤተክርስቲያን አጥብቃ ትማፀናለች፡፡ ቤተክርስቲያን በሰው ሕይወትና በአገር ንብረት ላይ በደረሰው ጥፋት በጣም ታዝናለች፡፡ መንግስት ባለበት የማስተዳ ኀላፊነት መሰረቱን የጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር በጋራ በመወያየት የግንዛቤ ትምህርቶችን በመሰጠት በጥበብና በማስታዋል በዚህ አድስ ዓመት ተግቶ እንዲሰራ፣ የአገሪቱም እድገትና ደህንነት እንዲያስጠብቅ አደራ ትላለች፡፤ ሁላችንም እንደየእምነታቸን ክፉውን ከምንወዳት አገራችን እንዲያርቅልን በፀሎት እንትጋ፡፡

 

እግዚአብሔር ፈጣሪያችን ጽድቅን ያለ አድሎዎ እንደሚያድል እኛም ከድሆችና ከምስኪኖች ጋር ይህን በዓል እንድናከብር ይጋብዘናል፡፡ በመሆኑም በደግነት የሚገኝ ክብር የማይጠፋ በመሆኑ ያለንን ተካፍለን ዐውደ ዓመትን የማክበር ባህላችንን እንተግብር፡፡ አሁንም ከልብ በመነጨ ርኅራኄ፣ በመልካም ፈቃደኝነትና በችሮታ መንፈስ ይህን የዐወደ ዓመት በዓል ስናከብር፣ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያደረግነው ለእግዚአብሔር እንዳደረግነው ይሆንልናልና በደስታ እንድንፈዕመው ለመላው ምዕመናን አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡

 

እንደምናውቀው በዓለማችን ቅድስት ቴሬዛ ዘካልኩታ (እማሆይ ቴሬዛ) የድሆች እናት እና የሰላም መልክተኛ ነበሩ፡፡ ነሐሴ 29/2008 ዓ.ም ቅዱስ አባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ በመንበረ ጴጥሮስ ቅድስናቸውን ማወጃቸው ይታወሳል፡፡ እሳቸው የመሰረቷቸው ማህበራት በኢትዮጵያ ውስጥ 19 ቤቶች ከፍተው ድሆችን የማገልገል ስራ እየቀጠሉ ይገኛሉ ፡፡ ቅድስት ቴሬዛ እኛንም  የድሆች አገልጋዮች እና  የሰላም ልዑካን እንድንሆን እንዲያማልዱን እንፀልይ፡፡

 

በተለይ በዚህ በአዲሱ ዓመት ለሕጻናትና ለወጣቶች መልእክት አለኝ፡፡ መስከረም ወር ትምንርት የሚጀመርበት ጊዜ ስለሆነ በአዲስ ተስፋና በጽኑ ዓላማ ትምህርት  ቤት ገብታችሁ  ትምህርታችሀን በርትታችሁ ተማሩ፡፡ እግዚአብሔር ሕፃናትንና ወጣቶችን ይወዳል ፡፡ እናንተም ውደዱት፡፡ ወላጆቻችሁንና መምህራኖቻችሁን አክብሩ፡፡ ይህን ካደረጋችሁ ለራሳችሁ፣ ለቤተሰቦቻችሁና ለአገራችሁ ኩራት ትሆናላችሁ፡፡

 

የነገሮቻችን ሁሉ መቃናት በእግዚአብሔር እጅ እንደመሆኑ ለራሳችን ስኬትና ለሰዎች ኑሮና ዕድገት ለማዋል ጥረት ማድረግ የሚያስመሰግን ተግባር ነውና መልካም ሰዎች ለመሆን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

 

በመጨረሻ ከአገር ውጪ የምትገኙ ኢትዮጲያዊያንና ትውልደ ኢትዮጲያዊያን፣ የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበርና በተለያዩ አገራት በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ያላችሁ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ፣ በተለያዩ ህመሞች በየሆስፒታሉና በቤታችሁ የምትገኙ ህሙማን፣ በየማረሚያ ቤት ያላችሁ የህግ ታራሚዎች ሁላችሁ እግዚአብሔር አባት እንኳን ለ2009 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ፡፡የእግዚአብሔር በረከት ከሁላችሁ ጋር ይሁን በማለት መልካም ምኞቴን አስተላልፍላችኍለሁ፡፡

 

    አዲሱ ዓመት ለአገራችንና ለመላው ህዝባችን የሰላም፣የጤና፣የደስታና የበረከት ይሁንልን፡፡

     

ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት  ዘካቶሊካውያን ዘኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት

የምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኀብረት ሊቀ መንበር

 

 

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.