2016-09-10 09:38:00

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው "የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት እንደ አንድ ተራ አገልግሎት መቁጠር አይገባም" አሉ።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸኮ እንደ ጎርጎሮሳዊያን የቀን አቆጣጠር በመስከረም 9.2016 በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ባሰሙት ስብከታቸው፣ የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት እንደ አንድ ተራ አገልግሎት መቁጠር እንደ ማይገባ ማሳሰባቸው ተገለጸ።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው አጽኖት ሰጥተው የነበረው ክርስቲያኖች የሕይወት ምስክርነትን በሚያደርጉበት ወቅት ማንኛውንም አይነት ፈተና በመጋፈጥ መለወጥ እንዳለባቸው እና እንዲሁም በቃሉ መታመን ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን ዝግጅቱን የተከታተለው የቫቲካን ሬዲዮ ጋዜጠኛ አሌክሳንድሮ ጂዞቲ ዘግቡኋል።

“ወንጌልን መስበክ ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ነው ማከናወን የሚጠበቅብን?” የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በእለቱ በቀዳሚነት በተነበበው እና ከመጀመርያው የሐዋሪያ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ቆሮንጦስ 9,16-19፣22-27 በተወሰደው ቃል ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ ክርስቶስን መመስከር ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ በገለጹበት ወቅት ስብከተ ወንጌልን አንደ “አንድ የሥራ ተግባር ነው መፈጸም የሚገባው” ወደ ሚለው አስተሳሰብ ልናሳንሰው እንደ ማይገባ ገልጸዋል።

“ያለመታደል ሆኖ ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ይህንን የወንጌል አገልግሎት እንደ አንድ የሥራ ተግባር ሲቆጥሩ ይታያል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ብዙ ምዕማናን እና ካህናት በምያከናውኑት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲኩራሩ ይታያል ብለው “ይህ መመካት ይባላል። እኔ እመካለሁ። ለመስበክ  እሄዳለሁኝ በስብከቴም ብዙ ሰዎችን ወደ ቤተ ክርስቲያን መልሻለሁኝ ወደ ሚለው አስተሳሰብ ውስጥ በመግባት ስብከተ ወንጌልን ወደ አንድ የሥራ ተግባር ወይም ደግሞ ወደ መመካት እንቀይረዋለን” ብለዋል።

“ብዙ ሰዎች እንዲለወጡ አድርጊያለሁኝ ማለት በእራሱ እንደ መመካት ይቆጠራል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ወንጌልን መስበክ ማለት መመካት ማለት አይደለም እንዲህ ካሰብን ደግሞ ትምከተኞች እንሆናለን ማለት ነው፣ ይህ ደግሞ የወንጌል ሰባኪዎች ልያስብለን አይችልም” ካሉ ቡኋላ ሐዋሪያው ጳውሎስ እንደሚለው “ወንጌልን መስበክ አያስመካኝም፣ የምሰብከው ግዴታዬ ስለ ሆነ ነው፣ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዩልኝ” (1ቆሮ. 9, 16-19) እንዳለ ሁሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ወንጌልን የመስበክ ግዴታ እንዳለብን አውቆው እና አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ተገንዝበው በኢየሱስ መንፈስ በመታገዝ ከልብ በመነጨ መንፈስ ሊተገብረው ይገባል ብለዋል።

“ወንጌልን መስበክ ልንመካበት የሚገባ ተግባር ሳይሆን ሐዋሪያው ጳውሎስ እንደ ሚያሳስበን ግዴታችን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል” በማለት ስበከተ ወንጌላቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ታዲያ የአሰባበክ ዘዴያችን ምን ሊሆን ይገባል?” የሚለውን ጥያቄ አንስተው መልሱ አንድ እና አንድ ነው “ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር መሆን ነው” ይህም ማለት ደግሞ ወጣ ብሎ የሌሎችን ሕይወት መጋራት፣ ወደ እምነት የሚያደርጉትን ጉዞ ማጀብ፣ ሰዎች በእመንት ጎዞዋቸው እንድያድጉ ማድረግ ማለት ነው” ብለዋል።

እራሳችንን በሌላው ሰው ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ በማስገባት “ታሞ የሆነ እንደሆነ እንቅረበው፣ እንርዳው፣ እናግዘው፣ “ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆኖ መገኘት ታላቅ የወንጌል ምስክርነት ነው” በማለት ስብከታቸውን  የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የእዚህ አይነት ምስክርነት ብቻ ነው ቃሉን ውጤታማ በሆነ መንገድ መመስከር የሚቻለው በማለት የእለቱን ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.