2016-08-22 12:28:00

የነሐሴ 15-2008 ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር


የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

መሐሪ የሆነው እግዚአብሔር አባታችን ከክፉ ነገር ሁሉ ሰውሮን እንደ መልካም ሥራችን ሳይሆን በደግነቱ እና በምሕረቱ ጠብቆን ለዛሬው እለት ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለዘላለም ለእርሱ ይሁን።

የዛሬ ማለትም የነሐሴ 15-2008 በኢትዮጲያ የካቶሊክ ስርዓተ-ሉጥርጊያ አቆጣጠር መሰረት የሚነበቡት የእግዚአብሔር ቃላት በቀዳሚነት የተወሰደው ከመጀመሪያው የሐዋሪያው የጳውሎስ መልዕክት ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች ከምዕራፍ 12: 8-31 ያለው ስሆን ይህም በአንድ አካል ላይ ብዙ ብልቶች እንዳሉ እና አንዱ አንዱን ለምሳሌም “ዐይን እጅን አታስፈልገኝም” ሊል እንደ ማይችል የሚያውሰው ቀዳሚ ምንባብ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ የምናገኘው የእግዚአብሔር ቃል የተወሰደው ከሐዋሪያት ሥራ ከምዕራፍ 1,12-14 ስሆን  ይህም በይሁዳ ምትክ ሐዋሪያት ተሰብስበው ማትያስን እንደ መረጡ የሚያውሳ ስሆን በመጨረሻም የእለቱ ቅዱስ ወንጌል የተወሰደው ከማቴዎስ ወንጌል ከምዕራፍ 10,1-14 የሚገኘው እና ኢየሱስ 12ቱን ሐዋሪያት ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሄዱ እንደ ላካቸው የሚያወሳ ነው።

በእነዚህ የዛሬ ሦስት ምንባባት መካከል ከፍተኛ የሆነ ትስስር እናያለን። በመጀመሪያው ምንባብ ላይ እንደ ምናገኘው ሐዋሪያው ጳውሎስ በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ የሰው አካል የተለያዩ ብልቶች እንዲኖሩት የተደረገበትን ምክንያት ይናገራል። የአካልን ክፍል ምሳሌ በማድረግ እና ከግንዛቤ በማስገባት እግዚአብሔር በክርስቶስ አካል ውስጥ አንድ ዓይነት ስጦታ ሳይሆን ልዩ ልዩ ስጦታ ያላቸውን ክርስቲያኖች እንዳስቀመጥ ያወሳል። የተለያዩ ስጦታዎች እንዲኖሩ የተደረገውም የእንዱን እግዚአብሔር ዓላማ እውን ለማድረግ ነው። እግዚአብሔር አንድነትን ለማምጣት ልዩነትን እንደ ሚጠቀምም ያሳያል።

እያንዳንዱ ክርስቲያን ትንሽ ትልቅ ሳይል፣ ደካማ ጠንካራ ሳይባል፣ መልክ እና ቁመና ሳይታይ ሁሉም አንዱን የእግዚአብሔር ዓላማ “ይህም እግዚአብሔርን መውደድ እና ባልንጀራችንን እንደ ራስህ አድርገህ ወደድ” የሚለውን ለማሳካት እና የአንዱ የክርስቶስ የአካል ክፍሎች ሆነን መኖር እንደ ሚጠበቅብን እና ሁሉም ክርስቲያኖች ይነስም ይብዛም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ድርሻ እንዳላችውም ያስተምረናል። በአንድ የአካል ክፍል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ብልቶች እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህሪ እንዳላቸው ሁሉ በክርስቶስ አካል ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖችም የተለያዩ ተግባራትን በሚያከናውኑበት ወቅት ሁሉ እርስ በእርስ ተደጋጋፊ ይሆናሉ፣ ስለዚህም ክርስቲያኖች ህብረት ሊኖራቸው ያስፈልጋል ማለት ነው።

በአንደኛ ቆሮንጦስ በምዕራፍ 12,23 ላይ “የተናቁ ለሚመስሉ ብልቶች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋልን” ይላል። ከእዚህ የምንረዳው እምብዛም ስፍራ ለሌላቸው የሰውነታችን ክፍሎች የተለየ እንክብካቤን እንደ ምናደርግ ሁሉ ጎልቶ የማይታይ ስጦታ ያላቸውን ክርስቲያኖች ሁሉ ማክበር እና ማገዝ ያኖርብናል፣ በተለይም ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎታቸው በሰው ፊት ጎልቶ ለማይታይ ክርስቲያኖች የተለየ አክብሮት መስጠት ያስፈልጋል።

በሁለተኛው ምንባብ ላይ ሐዋሪያት የኢየሱስ እናት ማሪያም በተገኘችበት በጸሎት እየትጉ እና ኢየሱስን አሳልፎ በሰጠው ይሁዳ ምትክ ሌላ ሐዋሪያ ለመምረጥ ሲዘጋጁ እናያለን። እናታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በአዲስ ኪዳን ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀሰችሁ በእዚሁ የመጻፍ ቅዱስ ክፍል ስሆን ከሐዋሪያቱ ጋር በመሆን በጸሎት ተግታ መገኘቱዋ የሚያሳየው ሁል ጊዜም ቢሆን በጌታ ስም ተስብስበን በምንጸልይበት ቦታ ሁሉ አማላጃችን የሆነች ቅድስት ድንግል ማሪያም አብራን እንደ ምትሆን እና እንዴት መጸለይ እንደ ሚገባን ልታስተምረን ዝግጁ መሆኑዋን ያሳያል። በተጨማሪም የክርስትያኖች ረዳት የሆነችው እናታችን ሁል ጊዜም ቢሆን ከክርስቲያኖች ጎን ሆና አለኝታነቷን በመግለጽ የደከመን በማበረታታት፣ ያዘነን በማጽናናት፣ የደከምን በመደግፍ ተስፍ ለቆረጥ ተስፋን በመስጠት ለታመመ ፈውስን፣ ለተጨነቀ መጽናናትን ለማጎናጸፍ ሁል ጊዜ አብራን እንደ ምትሆን የምያስይ አብይ ማስረጃ ነው።

ወደ ቅዱስ ወንጌላችን ስናልፍ ደግሞ ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለመንፈሳዊ አገልግሎት  መላኩን እናያለን።

ይህንን የወንጌል ክፍል በይበልጥ ለመረዳት ወደ ሁኋላ መለስ ብለን በምዕራፍ ዘጠኝ የመጨረሻ ክፍል ላይ የተጠቀሰውን “መከሩ ብዙ ነው፣ የመከሩ ሰራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፣ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑ” የሚለውን ማስታወስ ያስፈልጋል። ከእዚህ ቃል እንደ ምንረዳው እና በዛሬው የወንጌል ቃል እንደ አዳመጥነው እየሱስ ይህንን ቃሉን መሠረት በማድረግ ደቀ መዛሙርቱን ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንደ ላካቸው ለመረዳት ይቻላል።

“ደቀ መዝሙር” የሚለው ቃል የሚያሰማው ክርስቶስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይሰብኩ ዘንድ የላካቸው መልዕክተኞች ወይም ተከታዮች የሚለውን ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በላከበት ወቅት እርኩሳን መናፋስትን እንዲያወጡ፣ ደዌን እና ሕመምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጥቶዋቸው ነበር። ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን በመንፈስ እና በአስተሳስብ መብሰላቸውን ካረጋገጥ ቡኋላ ከሐዋሪያነት ወደ ደቀ መዛሙርትነት መቀየራቸውን አብስሮ ታላቅ ሐላፊነትን ሰጥቶዋቸው እንደ ላካቸው ይታወቃል።

በወንጌሉ እንደ ተጠቀሰው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከመላኩ በፊት የሚከተሉትን ተጋባራት ሲፈጽም እናያለን

  1. ታምራትን እንዲፈጽሙ ሥልጣንን ሰጣቸው

  2. ለእዚህ አስቸጋሪ እና የሕይወት መስዋዕትነትን ለሚያስከፍል ተግባር የታጩ እነ ማን እንደ ሆኑ ስማቸውን ይፋ ስያደርግ እንሰማለን. . .ምክንያቱም ይህ ልዩ ሥልጣን የሚፈልግ እና ታላላቅ ታምራትን የማከናዎን ሥልጣን የተሰጣቸው የተወሰኑ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ለማሳየት ፈልጎ ነው።

  3. በሦስተኛ ደረጃ የምናገኘው ይህንን የተሰጣቸው ታላቅ ሥራ እና አገልግሎት እንዴት መወጣት እንደ ሚኖርባቸው የሚገልጽ የሥራ አፈጻጸም መመሪያን እናገኛለን። ይህም መመሪያ. . .

  4. ምን ዓይነት ሥራ መሥራት እንዳለባቸው የምያሳስብ

  5. እንዴት መስበክ እንዳለባቸው የሚገልጽ

  6. ታምራትን እንዴት ማከናወን እንደ ሚኖርባቸው የሚገልጽ

  7. ወደ ማን መሄድ እንዳለባቸውና ለማን ይህንን ታምር መፈጸም እንዳለባቸው የሚያሳይ

  8. ለአገልግሎ በሚሄዱበት ወቅት ምን ዓይነት ባሕሪያትን ማሳየት እንደ ሚኖርባቸው የሚገልጽ

  9. በምን ዓይነት ዘዴ ተግባራቸውን መፈጸም እንደ ሚኖርባቸው የሚያሳስብ

  10. ተግባራቸውን በሚፈጽሙበት ወቅት የሚያጋጥማቸውን መከራ የሚያሳይ እና ይህ መከራ ከየተኛው ወገን እንደ ሚመጣ እና ይህንን መከራ እንዴት መጋፈጥ እንደ ሚኖርባቸው እና በመከራቸው ጊዜ ሁሉ በጽናት በመቆም ከእዚህ ስቃይ እና መከራ የሚመነጨውን ደስታ እንዴት ማጣጣም እንደ ሚችሉ የሚያሳስብ ጠቅላላ ይዘት ያለው መመሪያ ነው።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሰዎች ሁሉ!

ከዛሬ ቅዱስ ወንጌል የምንረዳው የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ለመሆን ጥልቅ ዝግጅት እንደ ምያስፈልግ ነው። ምክንያቱ ለአገልግሎቱ የሚሰጠው ኋላፊነት ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳና በብቃት ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ኋላፊነት መወጣት እንድንችል ጠለቅ ያለ እና በቂ ዝግጅት ያስፈልገናል። ማንም ሰው በድንገት ተነስቶ የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ነኝ ሊል አይችልም ምክንያቱም መከራን መጋፈጥ  የምያስችል የፀጋ ቅባት ከእግዚአብሔር ልቀበል እና አካላዊ እና መንፈሳዊ ብቃት ስለ ምያስፈልግ ነው ምክንያቱ መንገዱ አስቸጋሪ በመሆኑ።

ማንም ሰው በድንገት የጌታ ደቀመዝሙር ልሆን አይችልም። ኢየሱስ ለሦስት ዓመታት ያህል ደቀ መዛሙርቱን አዘጋጅቶዋቸው ነበረና። ዝግጅት የምያስፈልግበት ዋንኛው ምክንያት ያለምንም ነቀፋ በታላቅ መንፈሳዊነት አገልግሎትን ማከናወን እንዲቻል እና መከራ በምያጋጥምበት ጊዜ እና ወቅት ሁሉ ጸንቶ ለመቆም በቂ ዝግጅት ማድረግ ሁነኛ መሳሪያ በመሆኑ ነው።

የዝግጅቱ ሁሉ መጀመሪያ መሆን የሚገባው ነገር በቅድሚያ ኢየሱስን ማወቅ ነው።

የክርስቲያኖች ጠላት የነበረው ሳሆል ኢየሱስ ፊት ለፊት ስለተገለጸለት እና በውስጡም የኢየሱስን ማንንት ጠንቅቆ በመረዳቱ ነው ለታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት የታጨው። ለማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት በምንዘጋጅበት ወቅት ልናስተምረው ወይም ልናውጀው የተዘጋጀነውን ነገር ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል። የማናውቀውን ነገር መመስከር አስቸጋሪ እና ውሸታሞች ስለ ምያደርገን የምንመሰክረውን ነገር ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል።

እውቀታችን ደግሞ በጸሎት እና በአስተንትኖ በሚታጀብበት ወቅት እውቀታችን ወደ ውስጣችን ጠልቆ በመግባት ብርቱዎች እና በአገልግሎታችን ወቅት ሁሉ መከራ ስያጋጥመን ጸንተን እንድንቆም ይረዳናል።

በሁለተኛነት ደግሞ ከእየሱስ ጋር ህብረት ሊኖረን ይገባል። አንድ ሰው አስተማሪ ከመሆኑ በፊት ጎበዝ ተማሪ መሆን እንዳለበት ይታወቃል። ምክንያቱም ሌሎችን ለማስተማር ከመውጣታችን በፊት እራሳችን የምናስተምረውን ነገር ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል። ቅዱስ ወንጌልን ለማስተማር በቅድምያ ወንጌሉን መኖር ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን አስተምህሮዋችን በሕይወት ምስክርነት የታጀበ ሊሆን አይችልም። ያመነውን ብቻ ነው መምስከር የምጠበቅብን።

የተወደዳቸውሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ።

እግዚኣብሔር እያንዳንዳችንን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለመላክ ይፈልጋል። ይህንን አገልግሎት ለመቀበል ግን ከፍተኛ የሆነ ዝግጅት ያስፈልጋል። በጥምቀት የእግዛኢብሔር ልጆች የሆንን ሁላችን ክርስቶስን ለብሰናል እና ክርስቶስን የማወጅ ከፍተኛ መንፈሳዊ አላፊነት አለብን።

ይህንን አገልግሎት ጌተ በሚፈልገው መልኩ፣ በምንሠራበት ቦታ ሁሉ በአግባቡ በቃል እና በተግባር መመስከር እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንጋል ማሪያም ከልጇ ዘንድ ፀጋን ታስገኝልን ጸንድ እንማጸናለን።

የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን። አሜን!  

 








All the contents on this site are copyrighted ©.