2016-08-06 15:49:00

የዕለተ ረቡዕ ይፋዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህርቶ


በፖላንድ የተከበረውን የዓለም ወጣቶች ቀን በዓል አክብረው ወደ መንበረ ጵጵስናቸው የተመለሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለምዕመናን ባቀረቡት የዕሮብ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ በሽብርና በጦርነት የቆሰለውን ዓለም ለመለወጥ፣ ወጣቶች በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ተስፋን አሳይተዋል ብለዋል። ቀጥለውም በፖላንድ አውሽዊትዝና ቸስቶኮቫ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የዓለም ወጣቶች ቀን በዓል ከተካፈለች በኋላ ወደ አገሯ ስትመለስ መንገድ ላይ የሞተች የሮም ከተማ ነዋሪዋን በጸሎት እንድናስታውሳት መጠየቃቸውን ባልደረባችን አሌሳንድሮ ጂሶቲ ዘግቧል።

ቅዱስነታቸው ዘንድሮ በክራኮቪያ ከተማ የተከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን በዓል ለአውሮጳና ለመላው ዓለምም ትንቢታዊ ምልክት ነው ብለዋል። በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተገኙት ነጋድያን ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ አዲሱ ትውልድ ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በወረሱት መንፈሳዊ ጉዞ ልምድ በመታገዝ በዓለም ሰላምን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ጥሩ ተስፋን አሳይተዋል፤ ይህ ተስፋም የወንድማማችነት ተስፋ ነው ብለዋል።

በጦርነት ውስጥ ለሚገኝ ዓለማችን፣ ወንድማማችነት፣ መቀራረብና የእርስ በርስ ውይይት ያስፈልጋል ካሉ በኋላ ይህ ካለ ደግሞ ሰላምን የማምጣት ተስፋም አለ ብለዋል። ቅዱስነታቸው፣ ወጣቶች በደስታ መገናኘታቸው እና አንድ ላይ መሆናቸው በመካከላቸው ወንድማማችነትን መፍጠራቸውን ያመለክታል ብለዋል። በበዓሉ ላይ የተገኙት ወጣቶች ይዞአቸአው ከመጡት ሰንደቅ ዓላማዎች መካከል አንዳንዶቹ እርስ በርስ በጦርነት ውስጥ ያሉ አገሮች ሰንደቅ ዓላማዎች ቢሆኑም፣ አጠገብ ለአጠገብ ሆነው መውለብለባቸውን መመልከት ደስ አሰኝቷል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በፓላንድ ክራኮቪያ ያስተላለፉትን የምሕረት መልዕክት ወጣቶች በሚገባ ተረድተው ለምስክርነትም እንደሚበቁ ያላቸውን እምነት ገልጸው ወደ አገሯ ለመመለስ በጉዞ ላይ እያለች በማጅራት ገትር በሽታ ሕይወቷን ያጣች ወጣት አስታውሰው እግዚአብሔር ነፍሷን በመንግሥቱ እንዲቀበል፣ ለወላጆቿ እና ለጓደኞችዋ መጽናናትን ተመኝተውላቸዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ሐዋርያዊ ጉዞአቸው ወቅት የጎበኟቸውን የተለያዩ ሥፍራዎችን አስታውሰው ከእነዚህም መካከል በቸስቶኮቫ የሚገኘውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ስፍራና የአውሽዊትዝ ብርከናው የናዚዎች ወኅኒ ቤት የሚገኝበት መንደር ሲሆኑ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ፊት ተገኝተው ጸሎት ካደረሱ በኋላ ባሰሙት ንግግር መላው አውሮፓ ዛሬም ቢሆን ወደፊት ፖላንድ ካሏት ክርስቲያናዊ እሴቶች ተለይቶ መታየት አይችልም ካሉ በኋላ ከእነዚህ መንፈሳዊ እሴቶች መካከል ከፖላንድ ሕዝብ አብራክ የተገኙ የፖላንድ ምድር ተወላጆች፣ ቅድስት ፋውሲናና ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው በአውሽዊትዝ ባደረጉት ቆይታቸው በዚህ ስፍራ የተከናወነውን የጭካኔ ተግባር በጽሞና አስታውሰው ዛሬም በጭካኔ ተግባር ለተዋጠው ዓለማችን እግዚአብሔር ሰላምን እንዲያወርድ ጸሎታቸውን አቅርበውል።

በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሁለት ቋንቋዎች ማለትም በጣሊያንኛና በፖላንድኛ፣ ዘንድሮ የተከበረውን 31ኛ የዓለም ወጣቶች ቀን በዓል በድምቀት ተከብሮ በስኬታማነት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉትን የአገሩን መንግስትና ቤተክርስቲያን አመስግነው፣ በጉብኝታቸው ማግስት ያረፉትን የፖላንድ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማካሪስኪና፣ በወጣቶች በዓል ወቅት በሥራ ላይ እያለ በሞት የተለየውን ጋዜጠኛ አና ማርያ ጃኮቢንን በጸሎታቸው አስታውሰው፣ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተገኘው ምዕመናን ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ችረዋል።                      








All the contents on this site are copyrighted ©.