2016-06-11 12:56:00

የኢየሱስ የዕርገት በዓል ቃለ እግዚኣብሔር


7ኛው የፋሲካ ሳምንት እሁድ

የተወደዳቸሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

የእግዚአብሔር አባታችን እና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ እና ሰላም ለሁላችሁም ይሁን።

በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊጡርጊያ መሰረት የጌታችን የኢየሱስን የዕርገት በዓልን እነሆ ዛሬ እናከብራል፣ በእዚሁም አጋጣሚ ሁላችሁንም እንኳን አደረሳችሁ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ምናነበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤው ቡኋላ ለ40 ቀናት ያህል አልፎ አልፎ በደቀመዛሙርቱ መኋል ተገኚቶ ስያሰምራቸው ከቆየ ቡኋላ ከ40 ቀን ቡኋላ ደግሞ ስለ እርሱ እንዲመሰክሩ ለሐዋሪያቱ ኋላፊነት ስጥቶዋቸው ወደ አባቱ ወደ ሰማይ ዐረገ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ተክተው እርሱ የጀመረውን የእግዚአብሔርን መንግሥት የማስፋፋት ሥራን እንዲያከናውኑ ኋላፊነትን ለሐዋሪያቱ ሰጥቶ ነበር ወደ ሰማይ ያዐረገው። እንደሚታወቀው ለምስክርነት የሚበቃ ሰው አንድ ነገር ሲደረግ የሰማ እና ሲደረግ ያየ ሰው ነው። በእለተ ዕርገት ይህ ኋላፊነት የሚሰጣቸው ሐዋሪያት በመጀመሪያ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ-መዝሙር ነበሩ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥምቀቱ እና ከ40 ቀናት የበረሃ ፆም ቡኋላ በገሊላ አከባቢ የምድር ላይ አገልግሎቱን በይፋ ሲጀምር በፈውስ ተግባሮቹ እና በትምህርቱ ተማርከው እርሱን ለመከተል የወሰኑ ሰዎች ናቸው።

አንድአንዶቹ ደግሞ ኢየሱስ እራሱ “ተከተሉኝ” ብሎ ሲጠራቸው ለጥሪው ምላሽ ስጥተው ከኢየሱስ ጋር የሰነበቱ ሰዎች ናቸው። ከገሊላ እሰከ ኢየሩሳሌም ባደረጉት ጉዞ ወይም ቆይታቸው ደቀመዛሙርቱ ለሙሉ ኋላፊነት ወይም ምስክርነት አልበቁም ነበር ኢየሱስ ክርስቶስንም በጥልቅ አላወቁትም በከፊሉ ነው እንጂ።

ኢየሱስን መከተል ለአንድአንዶቹ ሥልጣንን የማግኘት ያህል መስሎዋቸው ነበር። ከሁሉም የሚበልጥ ማነው? የሚል ጥያቄም በደቀመዛሙርቱ መኸከል ክርክር አስነስቶም ነበር። (ሉቃ. 22,24) የዘብዲዎስ ልጆች የዕቆብ እና ዩሐንስ ከስልጣን ጥማት የተነሳ “በክብር ዙፋንህ ላይ በምትቀመጥበት ጊዜ አንዳችንን በግራህ አንዳችንን ደግሞ በቀኝህ አስቀምጠን” (ማር. 10,35) ብለው ጥያቄን አቅርበው እንደ ነበር ይታወሳል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ጎዞኋቸው ደቀ-መዛሙርትነት አገልግሎት መሆኑን አልተገነዘቡም፣ ለምስክርነትም አልበቁም ነበር። ለምስክርነት ብቁ እስከ ሚያደርጋቸው የዕርገት ቀን ድረስ ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ እርሱ እንዲመሰክሩ አልፈቀደላቸውም ነበር። ለምሳሌም በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ እና ዩሐንስ የኢየሱስ መልክ መለወጥ መለኮታዊ ክብሩን ባዩበት ወቅት ኢየሱስም እንድህ አላቸው “የሰው ልጅ ክርስቶስ ከሞት እስኪነሳ ድረስ ይህንን ያያችሁትን ለማንም አትናገሩ” (ማቴ. 17,9) ብሎ ደቀ-መዛሙርቱን አዞኋቸው ነበር።

“እኔን ሰዎች ማን ይሉኛል?” ብሎ ደቀ-መዛሙርቱን በጠየቀ ጊዜም ጴጥሮስ “አንተ የእግዚአብሔር መሲህ ነህ” (ሉቃ. 9, 20-21) ሲል መለሰለት። ኢየሱስም ይህንን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚደረስበት መከራ እና ሞት ሲናገር ጴጥሮስም ኢየሱስን ለብቻው ገለል አድርጎ “ጌታ ሆይ ይህ ነገር ከቶ አይሆንም ይህ ነገር በአንተ ላይ አይድረስብህ እያለ ይከለክለው ነበር” (ማቴ. 16,22)።

በሕማማት ሳማንት አስቆርታዊው ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ሰጠ። ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ ካደው። የኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ እና ሞት ደቀ-መዛሙርቱን ተስፋ አስቆረጣቸው፣ ተረባበሹ በፍርሃትም እንዲዋጡ አደረጋቸው። የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መስነሳቱን መልካም ዜና ከሰሙ ቡኋላም እንኳን አንድአንዶቹ በእዚህ መልካም ዜና አላመኑም ነበር። ለቶማስ “ጌታን እኮ አየነው!” ብለው ሌሎች በነገሩት ወቅት እርሱም በሚስማር የተወጉ እጆቹን እና የጎኑን ቁስሉን ካላየው በቀር አላምንም ብሎኋቸው ነበር።

ሁለቱ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩ የኢየሱስ ደቀ-መዝሙሮች ኢየሱስ ከሙታን ተንስቱኋል የሚል ዜና ከሰሙ ቡኋላም እንኳን እውነት አልመሰላቸውም ነበር፣ ወደ መጡበት ሀገራቸውም እየተመለሱ ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስይቶስ ከትንሳኤው ቡኋላ በደቀ-መዛሙርቶቹ መኋል መገኘት ከጥርጣሬ ወደ ሙሉ እምነት እንዲሻገሩ መንገድ ከፍቶላቸው ነበር፣ ፍርሃታቸውም ተወግዶ በደስታ እንዲሞሉም አደረጋቸው።

ከትንሣኤ እስከ ዕርገት ያለው ጊዜ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ-መዝሙር ወሳኝ ጊዜ ነበር። የተአድሶ እና የለውጥ ጊዜም ነበር። በቅዱሳት መጽሐፍት የተጻፉት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማራቸው ትምህርት በትክክል ያስተዋሉትም በእዚሁ ጊዜ ነበር።

“መጽሐፍን ያስተውል ዘንድ አእምሮዋቸውን ከፈተላቸው” (ሉቃ. 24,24) ማስተዋልን ከአገኙ ቡኋላ ኋላፊነት ሰጣቸው፣ ከደቀ-መዛሙርትነት ወደ ሐዋርያነት የሚሸጋገሩበት ወቅትም ደረሰ። “ክርስቶስ መከራን ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሳል። በስሙም ንስሐ እና የሐጥያት ስርዬት ከኢየስሩሳሌም ጀምሮ ለአህዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ ተጽፏል እናንትም ለእዚህ ምስክሮች ናችሁ”።

ከትንሤው ቡኋላ በአርባኛው ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተልዕኮ እና የምስክርነት ሥልጣን ለሐዋሪያቶቹ ሰጣቸው። ይህ ምስክርነት ወይም ተልዕኮ የሚጀምረው እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት በመንፈስ ቅዱስ ኋይል ሲሞሉ መሆኑንም ነገራቸው። በታዘዙት መሠረት ሐዋሪያቶቹ በ50ኛው ቀን በመንፈስ ቅዱስ ኋይል ሲሞሉ ከሞት ተነስቶ ህያው የሆነውን ክርስቶስን መመስከር ጀመሩ። በሐዋሪያት ሥራ በምዕራፍ 2: 32 ላይ እንደ ተጠቀሰው ሐዋሪያው ጴጥሮስ በንግግሩ “እኛ ሁላችን ለእዚህ ምስክሮች ነን” ይላል። የሐዋሪያት አስተምህሮ ፍሬ ሐሳብ የነበረው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት፣ ሞት እና ትንሣኤ እንዲሁም የንስሐ ጥሪ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር።

 

ከሐዋሪያት ዘመን ጀመሮ እስከ ዛሬ ድረስ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ይህንን እውነተ እየመሰከሩ ይገኛሉ። የክርስቶስ ሕማማት፣ ሞት፣ እና ትንሣኤ እና ዳግመኛ መምጣቱ ሁሌም በጸሎተ ሕይማኖት እንደ ምንደግመው የእመነታችን መሠረት ነው። በእየ ዓመቱ የዕርገትን በዓል ስናከብር ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረን ሁላችን ለምስክርነት መጠራታችንን ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጀመረው የእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ የሚቀጥለው በእኛ ተከታዮቹ አምካይነት ነው። የቀደምት የእምነት አባቶቻችን ከሐዋሪያት ተቀብለው ለእኛ ያስረከቡት እምነት እኛም ጠብቀን ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው።

ኢየሱስ ከዕርገቱ በፊት የተናገረው ቃል “በኢየሩሳሌም እና በይሁዳ ሀገር ሁሉ፣ ከሰማሪያ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” (ሐዋ. 8,1) ለሐዋሪያቶቹ ብሎኋቸው ነበር። በዚህ ቃል ላይ ተመሥርተው ከሐዋርያት ዘመን ጀመሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ሚሲዮናዊያን ባህር ተሻግረው፣ በረሐን አቋርጠው የክርስትናን እማነት አስረጭተዋል መስክረዋልም።

የእግዚአብሔር ቃል በድንበር፣ በዘር፣ በቀለም አይገደብም። በሁሉ ቦታ እና ለሁልም ሰው ይሰበካል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ተከታዮቹ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ ብሎ በቃሉ ያሳስበናል። ስለዚህም ምስክርነት የእየአንዳንዱ ክርስቲያን ግዴታ ነው። ከቀድምት አባቶቻችን የተቀበልነውን እምነት ጠብቀን በመያዝ ለተትኪው ትውልድ ማስተላልፍ ይኖርብናል። የክርስትናን እምነት ያወረሱን ሐዋሪያት እና ቅዱሳን በሕይወት ዘመናቸው በቃል እና በተግባር እምነታቸውን መስክረዋል። ለእምነታቸው ሲሉም ተሰደዋል፣ ተገርፈዋል ስማዕታትም ሆነዋል። በአጠቃላይ ዛሬ እኛ በእምነታችን ጸንተን እንድንገኝ መልካም ምሳሌን አሳይተውናል። እየአንዳዳችን ልባችንን ለእግዚኣብሔር ቃል በመክፈት ቃሉን በማወቅ እና በመኖር ለመመስከር ዝግጁዎች እንሁን። ከደቀ-መዝሙርነት ወደ ሐዋሪያነት ደረጃ መሸጋገር ይገባናል።

ሐዋሪያው ጴጥሮስ በመልዕክቱ እንዲ ይላል “የእግዚአብሔርን አስደናቂ ሥራ እንድታውጁ የተመረጥ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ እግዚአብሔር ለእርሱ የመረጣችሁ ቅዱስ ሕዝብ ናችሁ” (1ጴጥ. 2,9) ይለናል። እግዚአብሔር በየአንዳዳችን ሕይወት ውስጥ የፈጸመው አስደናቂ ነገር ይኖራል። ምስክርነት ማለት እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልንን ወይም ለሌሎች ሲያደርግ ያየነውን እና የሰማነውን መናገር ማለት ነው።

በመጸሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ሳምራዊቷ ሴት ከእየሱስ ክርስቶስ ጋር ቆይታን ካደረገች ቡኋላ ዝም አላለችም ነበር። ነገር ግን እየሮጠች ወደ ሰፈርዋ በመሄድ እዚያ ለነበሩት ሰዎች ሁሉ “የሠራሁትን ሁሉ የነገረኝን ኑ እና እዩት” ብላ መስክራ ነበር። እርሷ ባለችሁ መሠረት ሰዎቹ ሄደው ካዩት ቡኋላ እና ከኢየሱስ ጋር ቆይታን ካደረጉ ቡኋላም “ከእንግዲህ ወዲህ እርሱን የምናምነው አንቺ በነገርሽን ቃል መሠረት ብቻ ሳይሆን እራሳችን ስለሰማን እና በእርግጥም የዓለም አዳኝ መሆኑን ስላወቅን ነው” (ዩሐ. 4, 29-42) ብለው መሰከሩ።

በሕይወታችን ያከናወናቸውን ድንቅ ነገሮች ለሌሎች የማካፈል ምስክርነት የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው። መልካም ነገርን ማድረግ፣ ፍቅርን እና ክርስቲያናዊ ትህትናን ለቤተሰብ ማሳየት፣ አባታ እና እናት ለልጆቻቸው ክርስቲያናዊ አብነት በማሳየት እምነታቸውን ለልጆቻቸው ማውረስ ይገባቸዋል። በሥራችን ቦታም እምነታችንን ከሚጋሩ እና ከማይጋሩ የሥራ ባልደረቦቻችን ጋር ጥሩ ሊባል የሚችል ክርስቲያናዊ ሥነ-ምጋባር ማሳየት እና የሕይወት ምስክርነትን መስጠት ሰዎች በእኛ ውስጥ ጥሩ የሆነ የክርስቲያንዊ መንፈስን እንዲመለከቱ ማድረግ ያስፈልጋል።

ሐዋሪያው ጴጥሮስ በመልዕክቱ “የክርስቶስ በመሆናችው ባላችሁ መልካም ጠባይ ላይ ክፉ ነገር የሚናገሩ ሰዎች በክፉ ንግግራቸው እንዲያፍሩ መልካም ሕሊና ይኑራችሁ” (1ጴጥ. 3,16)። በመልካም ሥነ-ምግባር ሌሎችን መማረክ መቻል ትልቅ የሕይወት ምስክርነት ነው።  በሌላም በኩል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቁምስና፣ በክርስቲያን ማህበራት ውስጥ ንቁ የሆነ ተሳትፎ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። በቁምስና ደረጃ የተለያዩ መንፈሳዊ ማሕበራት እና የሥራ ዘርፎች ይኖራሉ። እየንዳንዱ ምዕመናን በእውቀቱ፣ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ በአጠቃላይ በሚችለው መንገድ ሁሉ በመሳተፍ ምስክርነት መስጠት ይኖርብናል።

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት፣ ሞት እና ትንሣኤ የቸሩን እግዚአብሔር አባታችን ምህረትን አግኝተናል።

በተለይም በዚህ በያዝነው ልዩ የምሕረት ዓመት እና በሚቀጥሉት ዘመናት የእግዚአብሔርን ታላቅ ምህረት እንድንመሰክር የመንፈስ ቅዱስ ኋይል እና ጥበብ ይብዛልን።

አሜን!

በአባ ጌታውን ፋንታ የተዘጋጀ








All the contents on this site are copyrighted ©.