2016-05-26 11:42:00

ቅ.አ. ፍራንቸስኮ ከግብጽ የአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም ከሆኑት ሼኪ ሐህመድ ሙሃማድ አል ታይብ ጋር በቫቲካን መገናኘታቸው ታወቀ።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በግንቦት 15/2008   ከግብጽ የአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም ከሆኑት ሼኪ ሐህመድ ሙሃማድ አል ታይብ ጋር በቫቲካን ተገናኝተው መወያየታቸው ተገለጸ። የቫቲካን የሕትመት ክፍል ኋላፊ የሆኑት አባ ፈሬድርኮ ሎምባርዲ እንደ ገለጹት ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ  ከታላቁ የግብጽ ኢማም ሼኪ ሐህመድ ሙሃማድ አል ታይብ ጋር ለሰላሳ ደቂቃ ያህል የቆየው ውይይታቸው “መግባባት ላይ የተመሰረተ” እንደ ነበር ግልጸዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የግብጹ ኢማም ሼኪ ሐህመድ ሙሃማድ አል ታይብ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ የልዑካን ቡድን ጋር ታጅበው እንደነበር የጠቀሱት የቫቲካን የሕትመት ቢሮ ኋላፊ አባ ፈሬድሪኮ ሎምባርዲ ከእነዚህም የልዑካን ቡድን መካከል የአል-አዝሃር ምክትል ፀሐፊ የሆኑት ዶክተር አባስ ሾውማን፣ የአል-አዝሐር ዩኒቬርሲቲ ከፍተኛ ምሁራን ምክር ቤት አባል የሆኑ ዶክተር ማሐመድ ሐምዲ ዛክዙክ፣ የታላቁ ኢማም አማካሪ የሆኑት የሕግ ምሁር ሙሐመድ ሙሐመድ አብደል ሳላም፣ የኢስላማዊ የምርምር ማዕከል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ዶክተር ሞሄ አፊፊ አፊፊ ሐመድ፣ የታላቁ ኢማም የዲፕሎማሲያዊ አማካሪ የሆኑት አባሳደር ማሐመድ አብደል ጋዋድ፣ የታላቁ ኢማም አማካሪ ክቡር ታመር ታውፊክ እና ሁለተኛ ጸሐፊያቸው የሆኑት ክቡር ሐማድ አልሾርባርጊ በውይይቱ ላይ መገኘታቸው የታወቀ ሲሆን በተጨማሪም የግብጽ የቅድስ መንበር አንባሳደር የሆኑት ክቡር ሐተም ሴኢፍ ኢልናስር ከታላቁ ኢማም ጋር በመሆን ቅዱስነታቸውን መገናኘታቸውም ታውቁዋል።

የግብጽ ታላቁ ኢማም ወደ ቫቲካን በመጡበት ወቅት በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረገውን ውይይት የሚመራው የጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በሆኑ ካርዲናል ጂን ሉዊስ ታውራን እና የእዚሁ ምክር ቤት ጸሐፊ በሆኑት አቡነ ሚጉዌል አንጅል አቀባበል እንደ ተደረገላቸው እና ከእዚያም በመቀጠል ከቅዱስነታቸው ጋር መገኛኘታቸው ተወስቱዋል።

የእዚህ ውይይት ዋነኛው አርዕስ የነበረው በካቶሊክ እና በእስልምና ሐይማኖቶች መካከል ቀጣይነት ያለው ውይይት እንዲደረግ በሚል አርዕስት ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ የጠቀሱት የቫቲካን የሕትመት ቢሮ ኋላፊ አባ ፈሬድሪኮ ሎምባርዲ የሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና የየእምነቱ ተከታዮች ለዓለም ሰላም የእራሳቸውን አስተዋጾ ያደርጉ ዘንድ አጋጣሚውን ተጠቅመው ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በተለይም ደግማ አሸባሪነትን እና ብጥብጥን ማውገዝ እንዳለባቸው እና በተጨማሪም በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ክርስቲያኖች ጥበቃ ይደረግላቸው ዘንድም በጋራ ጥሪ አቅርበዋል።

በግንኙነቱ መጨረሻ ላይ ቅዱስነታቸው ለታላቁ ኢማም የሰላም ምልክት የሆነውን የወይራ ምስል የታተመበትን ሜዳሊያ እና እራሳቸው የጻፉትን ላውዳቶ ሲ የተሰኘውን አዋዲ መልዕክታቸውን በስጦታነት ማበርከታቸውም ታውቁዋል።    








All the contents on this site are copyrighted ©.