2016-05-10 09:51:00

ቅ. አ. ፍራንቸስኮ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅድሴ "ብዙ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን እንደ ባዕድ ነግር ነው የሚቆጥሩት" ማለታቸው ተገለጸ።


ቅዱስ አባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ዘወትር ጥዋት ብዙ ካህናት እና ምዕመናን በተገኙበት በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት መስዋዕተ ቅዳሴ እነደ ሚያሳርጉ የሚታወቅ ሲሆን በትላንትናው ቀን ማለትም በግንቦት 1,2008 ባሳረጉት ስርዓተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ቤተ ክርስቲያን እንድትንቀሳቀስ ኋይል የሆናት መንፈስ ቅዱስ ቢሆንም ቅሉ፣ ብዙ ክርስቲያኖች ግን መንፈስ ቅዱስን እንደ በዕድ ነገር ነው የሚቆጥሩት ማለታቸው ተገለጸ።

“ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ በነበልባሉ ይመራቸው ዘንድ መፍቀድ ይኖርባቸዋል” በማለት ስብከተ ወንጌላቸውን የቀጠሉት ቅዱስ አባታችን “መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው ወደ ነጻነት የሚመራንን መንገድ ሊያሳየን የሚችለው” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በስርዐተ ቅዳሴ ላይ ለተገኙ እና የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት አገልጋይ ለሆኑ የፍቅር ሥራ ልጆች ማሕበር ደናግላን፣ የፍቅር ልጆች ማሕበር መስራች ለሆነችው ለቅድስት ሉዊዛ ዴ ማሪላክ  ዓመታዊ ክብረ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውም ተመልክቱዋል።

በእለቱ የመጀመሪያ ምንባብ ላይ ተመስርተው በሐዋሪያው ጳውሎስ እና የመጀመሪያዎቹ የኤፌሶን ደቀ መዛሙርት መካከል የተደርገውን ውይይት ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ ባሰሙት ስበከታቸው እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የኤፌሶን ደቀ መዛሙርት “መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳን ሰምተው እንደ ማያውቁ” ለሐዋሪያው ጳውሎስ መናገራቸውን አስረድተዋል።

“ይህ እውነታ ዛሬም ቢሆን ይታያል” ያሉት ቅዱስነታቸው “በኢየሱስ የሚያምኑ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን የማያውቁ ብዙ ሰዎች አሉ” ብለዋል። “ብዙዎቹ ስለ መንፈስ ቅዱስ  ያወቁት እና የቅድስት ሥላሴ አንድ አካል መሆኑን የሰሙት ትምህርተ-ክርስቶስ በተማሩበት ወቅት ብቻ መሆኑን እና ከእዚያ ባሻገር ስለ መንፈስ ቅዱስ ምንም ዓይነት ተጨማሪ እውቀት እና እየፈጸመ የሚገኘውን ተዓምር እንኳን እንደ ማያውቁ” አስረድተዋል።

“መንፈስ ቅዱስ ነው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እና በልባችን ያለውን ሥራ በማከናወን ቤተ ክርስቲያን ወደ ፊት እንድትራመድ እና እንድትንቀሳቀስ  የሚያደርጋት” ያሉት ቅዱስነታቸው እያንዳንዱ ክርስቲያን ለየት ባለ መልኩ የሚያንቀሳቅስ ነገር ግን ሕብረት እንዲኖር የሚያደርገውም መንፈስ ቅዱስ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

“መንፈስ ቅዱስ የተዘጉ በሮችን በመክፈት የኢየሱስ መስካሪዎች እንድንሆን ይረዳናል” በማለት ስብከተ ወንጌላቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “በስርዓት ቅዳሴ መግቢያ ላይ መንፈስ ቅዱስን ትቀበላላችሁ ከእዚያም በዓለም ውስጥ የእኔ መስካሪዎች ትሆናላችሁ የሚለውን ቃል ሰምተን ነበር” ብለው “መንፈስ ቅዱስ ነው እግዚአብሔርን እንድናመስግን፣ ወደ ጌታ እንድንጸልይ የሚረዳን እና እግዚአብሔርን አባት ብለን እንድንጠራው የሚያስተምረን በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ ነው እንደ ‘ወላጅ አልባ’ ሰው ከሚሰማን ስሜት ነጻ የሚያወጣን ብለዋል።

“መንፈስ ቅዱስ ነው ቤተ ክርስቲያን ቁማ እንድትሄድ የሚያስችላትን ዋነኛውን ገጸ ባሕሪ የሚጫወተው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በእርሱ መሪነት የማትመራ ቤተ ክርስቲያን የሞራል እና የስነ-ምግባር ችግሮች እንደ ሚያጋጥማትም ጨምረው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ትዕዛዛትን ብቻ ተግባርዊ ማድረግ እና እጃችንን አጣጥፎ መቀመጥ በቂ አይደለም ብለው የክርስትና ሕይወት በስነ-ምግባር ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን ከኢየሱስ ጋር ግላዊ ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመጨረሻም “መንፈስ ቅዱስን ልክ እንደ አንድ 'የቅንጦት እስረኛ’ አድርገን በልባችን እናስቀምጠዋለን፣ መንፈስ ቅዱስ ወደ ፊት እንዲያንቀሳቅሰን ብዙን ጊዜ አንፈቅድለትም፣ መንፈስ ቅዱስ ነው ሁሉንም የሚሠራው፣ ሁሉንም የሚያውቀው ብለው በአጠቃላይ መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው ትክክለኛ ክርስቲያን እንድንሆን የሚያደርገን ካሉ ቡኋላ የእዚህ የያዝነው ሳምንት ዋነኛው ተግባራችን ሊሆን የሚገባው ስለ መንፈስ ቅዱስ ማሰብ ሊሆን ይገባል ብለው ስብከተ ወንጌላቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.