2016-05-07 11:52:00

የጳጳሳዊው የስዊዘርላንድ የክብር ዘብ አባላት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚልካ በተካሄደው ስርዓተ ቅድሴ ላይ ዓመታዊ መሀላቸውን ማደሳቸው ተገለጸ።


በትላንትናው እለት ማለትም በሚያዝያ 28,2008  የጳጳሳዊው የስዊዘርላንድ  የክብር ዘብ አባላት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚልካ በተካሄደው ስርዓተ ቅድሴ ላይ ዓመታዊ መሀላቸውን ማደሳቸው ተገለጸ።

እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በ1527 ዓመተ ምሕረት የስዊዘርላንድ የክብር ዘብ አባላት በወቅቱ ክሌሜንቶስ 7ኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስት በነበሩበት ወቅት በሮም ከተማ ጦርነት ተቀስቅሶ ስለነበር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ክሌሜንቶስ 7ኛን ከጥቃት ለመከላከል በማሰብ የስዊዘርላንድ የክብር ዘብ አባላት ወደ ቫቲካን ተልከው እንደ ነበር የሚታወስ ሲሆን በዚያን ወቅትም በተካሄደው ጦርነት 147 የስዊዘርላንድ የክብር ዘብ አባላት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመከላከል ባደረጉት ጥረት ነብሳቸውን በጦርነቱ ማጣታቸውን ለማሰብ እና ለመዘከር በየዓመቱ በሚያዝያ 28 ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ያላቸውን ታማኝነት ለመግለጽ የሚያድሱት ቃለ መሀላ መሆኑ ይታወቃል።

በእለቱ በተደረገው ስርዐተ ቅድሴ ላይ የተገኙት የቫቲካን የቅድስት መንበር ዋና ጸሓፊ ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን ባሰሙት ስብከታቸው እንደ ገለጹት “የተከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት ሕይወት ሰጪ በሆነው ጌታ ላይ እምነታቸውን ባያደርጉ ኖሮ የማይሞከር መሆኑን” ገልጸው “ከሙታን በተነሳው ኢየሱስ ድጋፍ እና ሙሉ የሆነ ሕይወት ሰጭ በሆነው በጌታ ስም እናንተን የክብር ዘብ አባላት ማሳሰብ የምፈልገው ምንም እንኳን ሥራችሁ አስቸጋሪ ቢሆንም ይህንን ችግር ተቋቁማችሁ ለዓለም ሁሉ ይህንን እውነታ እንድትመሰክሩ አደራ እላለው” ብለዋል።

“ወደ ሀገራችሁም ስዊዘርላንድ በምትመለሱበት ወቅትም ቢሆን በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ለሕይወታቸው ትርጉም ላጡ ሁሉ እና ስኬትን ለሚሹ ሁሉ ክርስቶስን ልትመሰክሩላቸው ያስፈልጋል” ያሉት የቫቲካን የቅድስት መንበር ዋን ጸሓፊ ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን “ብርሃን እና ሕይወትን በሚመኘው ዓለማችን ተስፋን እና ብርታትን ለማምጣት ቁርጠኝነት፣ ውሳኔ ማድረግን እና ከፍተኛ ጥረትን የሚጠይቅ ቢሆንም መልካም እና ማራኪ የሆኑ ነገሮችን ለማሳየት መጣር ይኖርባችዋል” ማለታቸውም ተወስቱዋል።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.